ፌስቡክ በኢትዮጵያ ግጭት በማነሳሳት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ክስ ተመሠረተበት

ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

መጠሪያውን ወደ ሜታ የቀየረው ግዙፉ ማሕበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ኢትዮጵያ ውስጥ ግጭት በማነሳሳት ክስ ተመሠረተበት።

በሰሜኑ ኢትዮጵያ የርስ በርስ ጦርነት ፌስቡክ በገጹ ጥላቻ የሚነዙ እና ግጭት የሚያነሳሱ መልዕክቶችን አሰራጭቷል ተብሎ ነው ክስ የተመሠረተበት።

ሜታን ከከሰሱት መካከል አባቱ ፌስቡክ ላይ በተለጠፈ ጽሑፍ ምክንያት የተገደለበት አብርሃም ማዕረግ አንዱ ነው። በፌስቡክ ጽሑፍ ምክንያት አባቱ ጥቃት ደርሶበታል፣ በጥይትም ተገድሏል።

ከሳሾቹ በፌስቡክ ላይ ከተሰራጨው ጥላቻ ጋር በተያያዘ ለደረሰባቸው ጉዳት የሁለት ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲሁም የፌስቡክ አልጎሪዝም ላይ ለውጥ እንዲደረግም ይሻሉ።

ሜታ በበኩሉ በገጹ የሚንሸራሸሩ መልዕክቶችን ለማጥራትና ጥላቻ አዘል የሆኑትን ለማስወገድ በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት እንዳደረገ ይናገራል።

የሜታ ወኪል እንዳሉት፣ የጥላቻ ንግግር እና ግጭት አነሳሽ መልዕክቶች ከገጹ መርህ ጋር ይጣረሳሉ።

ክሱ የተመሠረተው በኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው። ፎክስግሎቭ የተባለ የመብት አቀንቃኝ ቡድንም ይደግፈዋል።

ሜታ በኬንያ፣ ናይሮቢ ይዘት የሚፈትሽ ቡድን አለው።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ረሃብ በሚመስል ሀኔታ ውስጥ እንደገቡ ሲነገር ቆይቷል።

“ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሩን ቢያስቆም አባቴ አይሞትም ነበር”

ባለፈው ወር በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙ አይዘነጋም።

በሌላ በኩል ከሰሞኑ የአማራ እና ኦሮሞ ተወላጆች ላይ ያነጣጠሩ (ብሔር ተኮር) ግድያዎች በተደጋጋሚ እየተዘገቡ ይገኛሉ።

አምና ኅዳር ላይ የአብርሃም አባት ፕ/ር ማዕረግ አማረ አብርሃ ከሚያስተምሩበት ዩኒቨርስቲ ወጥተው ወደ ቤታቸው እየተጓዙ ሳለ በሞተር የመጡ ታጣቂዎች ተኩሰው ገድለዋቸዋል።

ጥቃቱን የፈጸሙት ግለሰቦች በአካባቢው የሚተላለፉ ሰዎች ፕ/ር ማዕረግን እንዳይረዷቸው ስላስጠነቀቁ ማንም ሰው ሊያተርፋቸው አልሞከረም። ከተተኮሰባቸው ከሰባት ሰዓታት በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።

ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ፌስቡክ ላይ ስለ ፕ/ር ማዕረግ መረጃዎች እየተለጠፉ እንደነበር አብርሃም ይናገራል።

ለፌስቡክ በተደጋጋሚ ስለእነዚህ ጽሑፎች ጥቆማ ቢያደርጉም “ፌስቡክ ግን እነዚህን ጽሑፎች በፍጥነት አላጠፋም” ሲል ያክላል።

አንድ ጽሑፍ አባቱ ከተገደሉ በኋላ ጠፍቷል።

አብርሃም

የፎቶው ባለመብት, FOXGLOVE

የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት ፌስቡክ ላይ ስለ ፕ/ር ማዕረግ መረጃዎች እየተለጠፉ እንደነበር አብርሃም ይናገራል።

ሌላ ፌስቡክ አጠፋዋለሁ ያለው ጽሑፍ ግን እስከ ታሕሳስ ድረስ ሳይነሳ ቆይቷል።

“ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሩን ቢያስቆም እና በገጹ የሚለጠፉ ጽሑፎችን በአግባቡ ቢያጣራ ኖሮ አባቴ አይሞትም ነበር” ይላል አብርሃም።

የእሱ ቤተሰብ ላይ የደረሰው ማንም ላይ እንዳይደርስ እንደሚታገል ገልጾ ፌስቡክ “በቀጥታ ይቅርታ እንዲጠይቀኝ እፈልጋለሁ” ሲል ያክላል።

አብርሃም ለፍርድ ቤት በሰጠው ምስክርነት፣ የፌስቡክ አልጎሪዝም “ጥላቻ አዘልና ግጭት አነሳሽ” መልዕክቶች እንደሚያስተዋውቅ ተናግሯል። መሰል ይዘቶች የተጠቃሚዎችን ተሳትፎ ስለሚጨምሩ እንደማይወገዱም አክሏል።

አብረሃም ምስክርነት ሲሰጥ ፌስቡክ በአፍሪካ ያለው የይዘት ቁጥጥር (content moderation) “አናሳ” እንደሆነም ገልጿል። በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ይዘቶች የሚፈትሹ ባለሙያዎች ጥቂት ናቸው ይላል።

ሜታ በበኩሉ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ “ስለ አገሩ ዐውድ የሚያውቁ ባለሙያዎችን እንቀጥራለን። አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማሊ እና ትግርኛን ጨምሮ በአገሪቱ በሚነገሩ ቋንቋዎች ከፌስቡክ መርሕ ጋር የሚጻረሩ ይዘቶች ሲለጠፉ ለማስወገድ ጥረታችን ይቀጥላል” ብሏል።

በኢትዮጵያ ፌስቡክ የሚጠቀመው ከ10% ያነሰ ሰው ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ በተቋሙ ቅድሚያ እንደሚሰጣት ገልጿል።

ፍራንሲስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ ሴኔት ቀርባ ፍራንሲስ በሰጠችው ምስክርነት፣ “የፌስቡክ አልጎሪዝም የብሔር ግጭትን ያጋግላል። ጽንፈኛ ይዘቶችን አብዝቶ ያሰራጫል” ብላለች።

ፌስቡክ እና የይዘት ቁጥጥር

ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋም ወደ ፍርድ ቤት መወሰዱ ትልቅ የሚባል እርምጃ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት፣ ሜታ እና ሌሎችም ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሐሰተኛ መረጃ፣ የጥላቻ ንግግር እና ግጭት የሚያነሳሳ ይዘትን ከገጻቸው ለማስወገድ በቂ ጥረት ሲያደርጉ አይስተዋልም።

የገጾቹ ተጠቃሚዎች ይዘቶቹ ላይ ጥቆማ ካደረጉ በኋላ የሚወገዱበት ጊዜ አለ።

በሌላ በኩል አንድ ቋንቋ ላይ አተኩሮ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ይዘቶችን የማስወገድ አካሄድ እንዳለ የሚተቹም አሉ።

በአገሪቱ በስፋት በሚነገሩ ቋንቋዎች ላይ በማተኮርና ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ ግጭት አነሳሽ ይዘቶችን ለማስወገድ እንደሚሠራ ሜታ በተደጋጋሚ አሳውቋል።

በዋነኛነት ሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፍሻል ኢንተለጀንስ) በመጠቀም የይዘት ቁጥጥር ሲያደርግ፣ አገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ አጋር ድርጅቶቹ ጥቆማ እንዲሰጡም ያበረታታል።

በሜታ ተቀጥረው በኢትዮጵያ ቋንቋዎች የይዘት ቁጥጥር የሚያደርጉት ምን ያህል ሠራተኞች እንደሆኑ እስካሁን ግልጽ መረጃ አልወጣም።

ባለፈው ዓመት የቀድሞ የፌስቡክ ሠራተኛ የነበረችው ፍራንሲስ ሀውገን ባወጣችው መረጃ፣ ፌስቡክ የጥላቻ ንግግሮችና ግጭት አነሳሽ ይዘቶችን ቸል ይላል።

በአሜሪካ ሴኔት ቀርባ ፍራንሲስ በሰጠችው ምስክርነት፣ “የፌስቡክ አልጎሪዝም የብሔር ግጭትን ያጋግላል። ጽንፈኛ ይዘቶችን አብዝቶ ያሰራጫል” ብላለች።

እነዚህ ይዘቶች የገጹን ተጠቃሚዎች ስለሚያነጋግሩ ነው በአፋጣኝ ከገጹ የማይጠፉት።

የክሱ ጭብጥ

ሜታ በአግባቡ አደገኛ ይዘቶችን እንደማይለይና በኢትዮጵያ ቋንቋዎች ይዘት የሚፈትሹ በቂ ባለሙያዎች እንደሌሉት ተንታኞች ከዚህ ቀደም ተችተዋል።

አሁን በድርጅቱ ላይ በተመሠረተው ክስ ከተካተቱ መካከል ካቲባ ኢንስቲትዮት እና ፍስሐ ተክሌ ይገኙበታል። ፍስሐ እንዳለው፣ ፌስቡክ የይዘት ቁጥጥር አለማድረጉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በግጭቱ ስለደረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚሠራቸውን ሪፖርቶች ከማደናቀፉም ባሻገር የቤተሰቡን ሕይወትም አደጋ ላይ ጥሏል።

ከሳሾቹ ፌስቡክ እንዲወስዳቸው ከጠየቋቸው የማሻሻያ እርምጃዎች አንዱ፣ በጥላቻ ንግግርና በግጭት አነሳሽ ይዘቶች ሳቢያ ጉዳት ለደረሰባቸው ካሳ የሚሆን 1.6 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እና ተጨማሪ 410 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ካሳ ደግሞ ፌስቡክ ስፖንሰር ባደረጋቸው ይዘቶች ለደረሱ ጉዳቶች የሚውል ነው።

ፌስቡክ አልጎሪዝሙ “ጥላቻ የሚነዙና አደገኛ ይዘቶችን” ከማሰራጨት እንዲቆጠብ እንዲደረግም በክሱ ተጠይቋል። በተጨማሪም በአገር ውስጥ ቋንቋዎች የይዘት ቁጥጥር የሚያደርጉ ተጨማሪ ሠራተኞች እንዲቀጠሩም ክሱ ይጠይቃል።