ፌስቡክ በኢትዮጵያ ግጭትን በማባባስ ተጠያቂ ነው?

ኪቦርድና ቦንብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ፌስቡክ ከወሰዳቸው እርምጃዎች ምናልባትም ዋናው ሊባል የሚችለው የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሑፍ ማጥፋቱ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሕዝቡ "የህወሓት ኃይሎችን ለመቅበር መሣሪያ እንዲያነሳ" የጠየቁበት ጽሑፍ የፌስቡክን መርሕ ጥሷል ተብሎ ነው የተሰረዘው።

ስሙን ወደ ሜታ የቀየረው ፌስቡክ ስለ ውሳኔው በቢቢሲ ተጠይቆ፤ ግጭትን የሚያነሳሱ ወይም ነውጥን የሚደግፉ ጽሑፎች "በማንም ይጻፉ በማን ከገጻችን እናወርዳልን" ብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የፌስቡክን እርምጃ ተቃውሞታል።

አምና ሰኔ ላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (INSA) ፌስቡክ በኢትዮጵያ ይዘቶች እና ገጾች እየሰረዘ "የኢትዮጵያን እውነታ አዛብቷል" ብሎ መተቸቱም ይታወሳል።

አያይዞም አገር በቀል የፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዋትስአፕ እና ዙም መተግበሪያዎች እንደሚሠራ ይፋ አድርጓል።

ፌስቡክ በበኩሉ ከኢንሳ ጋር ይገናኛሉ ያላቸውን ሐሰተኛ ገጾች አጥፍቷል። በዋነኛነት በአማርኛ የሚጻፍባቸው 65 ገጾች እና 72 ቡድኖች ከተሰረዙት መካከል ናቸው።

ጦርነቱ መፋፋሙን ተከትሎ ፌስቡክ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ግዙፍ የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋሞችም ኢትዮጵያ-ተኮር እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።

ትዊተር በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ የሆኑ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚጠቁመው አሠራሩን (Trends) ከኢትዮጵያ በጊዜያዊነት አግዷል።

"ሰዎች ለአሁናዊ አደጋ ተጋልጠዋል። ሰብአዊ ክብር መንሳትን እና ግጭት መቀስቀስን እንቃወማለን" ሲል ውሳኔውን አብራርቷል።

ባለፉት ሳምንታት አደባባይ ሚዲያ የተባለውን ድረ ገጽ ጨምሮ ሌሎችም ገጾች ከዩቲዩብ ታግደዋል። አደባባይ ሚዲያ ሲገለገልበት የነበረው የዩቲዩብ ገጽ እንደታገደ እና ሌላ ገጽ እየተጠቀመ እንደሆነ በትዊተር ገጹ አስታውቋል።

የኦሮሞ ነጻነት ጦር ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ መታገዱም አይዘነጋም።

ፌስቡክ፤ ባለፉት ስድስት ወራት በኢትዮጵያ ከ92 ሺህ በላይ ይዘቶችን ከፌስቡክ እና ከኢንስታግራም ማንሳቱን አስታውቋል።

ይዘቶቹ የጥላቻ ንግግርን ለመገደብ የወጣውን መርሕ እንደጣሱ እና ከተሰረዙት መካከል 98 በመቶው ጥቆማ ሳይደረግ በፊት ፌስቡክ የደረሰባቸው መሆናቸው ተገልጿል።

ፌስቡክ ኢትዮጵያን በጊዜያዊነት "ለከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ" አገሮች ዝርዝር ውስጥ ከቷል።

'መሣሪያ ይዛችሁ ሂዱ'፣ 'የበቀል እርምጃ ውሰዱ'፣ 'ይህን ቡድን አጥቁ' የሚሉ ጽሑፎችን እያጠፋ እንደሆነ እና ሰዎችን 'ሰላይ' ወይም 'ከሀዲ' የሚሉ አገላለጾችን እየሰረዘ እንደሚገኝም ተናግሯል።

ነውጥ የሚቀሰቅሱ፣ ጦርነት የሚያበረታቱ፣ ብሔርን ከብሔር ጋር የሚያጋጩ ወይም አንድን ማኅበረሰብ በሌላው ላይ የሚያነሳሱ የፌስቡክ፣ የትዊተር እና የዩቲዩብ ገጾችን የማዘጋት ዘመቻ ከመቼውም በላይ ተጧጡፏል።

መሰል ጽሑፎች፣ ምስሎች ወይም ተንቀሳቃሽ ምስሎች የሚሰራጩት በግለሰቦች ብቻ አይደለም። የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ተቃዋሚዎች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ንቅናቄ ፈጣሪዎች፣ የሲቪል ማኅበር ወኪሎች እና ሌሎችም ይገኙበታል።

በእርግጥ ጽሑፎች ላይ ጥቆማ ሲደረግ 'የዚህ ቡድን ደጋፊ' ወይም 'የዚያ አካል ተቃዋሚ' የሚሉ ውዝግቦች መነሳታቸው አይቀርም።

ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ በፌደራል መንግሥቱም ይሁን በህወሓት ወገን ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያን እንደ አንድ የውጊያ መድረክ በመውሰድ ታምተዋል። የፕሮፓጋንዳ ጦርነት ሜዳውም ፌስቡክ ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ በተጠቃሚዎች ብዛት ቀዳሚነቱን የሚይዘው ማኅበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ስለሆነ የዚህ ዘገባ ዋነኛ ትኩረት ፌስቡክ ነው። ፌስቡክ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ቀውስ ምን ያህል ተጠያቂ ነው? ግጭትን የሚያነሳሱ ይዘቶችን እና የጥላቻ ንግግሮችን ከገጹ በማውረድ ረገድ ምን ያህል ኃላፊነቱን ተወጥቷል? የሚሉትን ጥያቄዎች እንዳስሳለን።

line

ፌስቡክ ኢትዮጵያላለው ቀውስ ተጠያቂ ነው?

ናፖሊዮንካት ድረ ገጽ እንደሚለው፤ እአአ እስከ ጥር 2021 ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ 6,808,000 የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አሉ። ቁጥሩን ወደ 8 ሚሊዮን የሚያስጠጉም አሉ።

ከአጠቃላይ ሕዝቡ ፌስቡክ ያለው ወደ 5.8 በመቶ ገደማው ነው። ሴቶች 33 በመቶ ወንዶች ደግሞ 67 በመቶ ድርሻውን ይይዛሉ። አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ደግሞ ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 34 ያሉት ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ቀውስ ፌስቡክ ምን ያህል ተጠያቂ ነው? ስንል ሁለት ባለሙያዎችን አነጋግረናል።

ለፍትሐዊ ቴክኖሎጂ የምትታገለው ትምኒት ገብሩ (ዶ/ር) እና የቴክኖሎጂና ማኅበራዊ ጉዳዮች ባለሙያዋ ብርሃን ታዬ፤ መሬት ላይ ጦርነቱ ሲፋፋም ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሰራጨው መልዕክትም እንደሚጠለሽ ያስረዳሉ።

በአማራ ክልል፣ ደቡብ ወሎ ዞን፣ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በህወሓት አማጺያን መያዛቸው ከተነገረ ወዲህ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተሰራጩ ጽሑፎችን እንደ ማሳያ ይጠቀሳሉ።

ማኅበረሰቡ ለዘመናት አብረውት በኖሩ ጎረቤቶቹ፣ በማኅበራዊ ኹነቶች በተጋመዱት ወዳጆቹ ላይ እንዲነሳ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎች ተለቀዋል።

"መሬት ላይ ጦርነቱ ሲፋፋም ወይም አንድ ማኅበረሰብ ሌላውን ሲያጠቃ፤ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይም ይንጸባረቃል" ትላለች ብርሃን።

የሐሰት ዜና፣ የጥላቻ ንግግር እና ብጥብጥ የሚያስነሱ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በውጪ አገራት በሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጭምር እንደሚሰራጩ ትናገራለች።

ይህም ባለፉት ሦስት ዓመታት እየተባባሰ መምጣቱን አስተውላለች።

ትምኒት፤ በኢትዮጵያ ላለው ነውጥ የፌስቡክ ተጠያቂነት "ጥያቄ የለውም" ትላለች።

በርካታ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የሚኖሩት ከአሜሪካ ውጭ ቢሆንም፤ ፌስቡክ ግን ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ይዘት ፍተሻ (Content Moderation) የሚያካሂደው በአሜሪካ ነው።

ይህ ማለት ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ በገቡ አገሮች በተለያዩ ቋንቋዎች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮች ያለ ሀይ ባይ የሚስፋፉበት ዕድል ሰፊ ነው።

"ፌስቡክ አብዛኛውን ገቢ የሚሰበስበው ከአሜሪካ ውጪ ቢሆንም ዋና ትኩረቱን ለአሜሪካ ሰጥቷል። 115 ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ በሚኖርባት እና ብዙ ቋንቋ በሚነገርባት ኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት ከመጀመራቸው በፊት ስለ ይዘት ፍተሻ ማሰብ ነበረባቸው" ትላለች።

ባለፉት ሳምንታት በፌስቡክ የተለቀቁ ነውጥ ቀስቃሽ ጽሑፎችን ለፌስቡክ ከጠቆሙ አንዷ ትምኒት ናት።

የቅርብ ወዳጅ የሚባሉ ሰዎችን ሳይቀር ለማጥቃት አድራሻቸውን እስከመለጠፍ የደረሰው የጅምላ ግድያ ጥሪ ከ18 ሰዓት በላይ ፌስቡክ ላይ ቆይቷል ትላለች።

ጽሑፎቹ ሲጠቆሙ፤ የመጀመሪያው የፌስቡክ ምላሽ "ከፖሊሲያችን ጋር አይጻረርም" የሚል ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ጽሑፎቹ እንዲሰረዙ ተወስኗል።

ትምኒት እንደምትገልጸው፤ ጽሑፎቹ በበርካታ ሰዎች ከተጠቆሙ ከዚያም አሜሪካ ባሉ ጋዜጠኞች ድርጅቱ ጥያቄ ከተነሳበት በኋላ ነው የወረዱት።

"ጽሑፎቹን ካወረዱ በኋላም የጻፉት ሰዎች ገጽ ላይ እርምጃ አልተወሰደም። ሰዎቹ ከፈለጉ በቀጣይም እንደዚህ ዓይነት ነገር ሊሉ ይቻላሉ" ስትል ስጋቷን ታስረዳለች።

መጠሪያውን ወደ ሜታ የቀየረው የፌስቡክ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጠችው ምላሽ፤ ፌስቡክ በኢትዮጵያ ጤናማ አገልግሎት እንዲሰጥ ባለፉት ሁለት ዓመታት የይዘት ፍተሻ ሠራተኞቹን ቁጥር ጨምሯል።

አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ እና ሶማልኛ የሚናገሩት ሠራተኞቹ የድርጅቱን መርህ የሚጥስ ይዘት "በፍጥነት አግኝተው ይጠቁሙናል" ትላለች።

በይዘት ፍተሻ በኩል ከዓለም አቀፍ እና አገር አቀፍ አጋሮች ጋር በጥምረት እንደሚሠሩም ታክላለች።

ሠራተኞቹ ስለ ቀጠናው ፖለቲካ የሚያውቁ እንዲሁም የኢትዮጵያን ዐውድ የሚረዱ ኢትዮጵያውያን እና በኢትዮጵያ ረዥም ጊዜ የኖሩ እንደሆኑ ቃል አቀባዩዋ ተናግራለች።

"ኢትዮጵያ ካሉ የሲቪል ማኅበሮች ጋር በመነጋገር ስለ ወቅታዊ ጉዳይ ግንዛቤ ለመጨበጥ እንሞክራለን። ፖሊሲያችንን የሚጥስ ይዘትም እንሰርዛለን።"

ፌስቡክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

line

ፌስቡክ ግጭት ያጭራል?

በፌስቡክ የሚለጠፍ የጥላቻ ንግግር ወይም ግጭት አነሳሽ ይዘት ሥነ ልቦናዊ ጫና በመፍጠር ለእኩይ ተግባር ያነሳሳል? ምናልባትም የሚባለው ነገር 'ቅቡልነት' እንዳገኘ ያስመስላል?

በተለይም በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በታዋቂ ሰዎች እና በማኅበራዊ ሚዲያ አንቂዎች አንዳች ነገር ሲባል 'እውነት ነው' የሚል ዕሳቤ ለምን ይጎላል?

እነዚህ ጥያቄዎች የሥነ ልቦና፣ የማኅበረሰብ ጥናት እና የቴክኖሎጂ አጥኚዎች ዘንድ መወያያ ከሆኑ ሰነባብቷል።

ኤምአይቲ ከሁለት ዓመት በፊት ጀርመን ውስጥ የተሠራ ጥናትን አጣቅሶ እንደጻፈው፤ በፌስቡክ የሚለቀቁ የጥላቻ ንግግሮች ስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በእጥፍ ጨምረዋል።

ወደ 3,000 የሚጠጉ ጥቃቶች በሁለት ዓመታት ተመዝግበው የተሠራው ጥናት፤ በፌስቡክ ጽሑፎች እና በጥቃት መካከል ትስስርን አግኝቷል።

ጀርመን ውስጥ ጥናቱ ሲሠራ ጦርነት ወይም ነውጥ አለመኖሩን ልብ ይሏል። ጦርነት ባለበት አገር ነገሮች የበለጠ ስሱ ይሆናሉ።

ኒው ዮርክ ታይምስ ባስነበበው ዘገባ ፌስቡክን በፊሊፒንስ፣ በሊቢያ፣ በሕንድ፣ በሚያንማር እና በጀርመን ከደረሱ ጥቃቶች ጋር አያይዟል።

በሚያንማር ለደረሰውና ለበርካታ የሮሂንጋ ሙስሊሞች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት ለሆነው ጥቃት ፌስቡክን ተጠያቂ ይደረጋል።

ጥቃቱ በተጀመረበት ወር ብቻ 730 ሕፃናትን ጨምሮ 6,700 ሙስሊሞች ሲገደሉ፤ በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ ወደ ጎረቤት አገር ባንግላዲሽ ተሰደዋል።

ፌስቡክ በሚያንማር የጥላቻ ንግግር እና ግጭት አነሳሽ ጽሑፍ በበቂ ሁኔታ ባለማገዱ ጥቃቱን እንዳባባሰ አምኗል። መስራቹ ማርክ ዙከርበርግ በይፋ ይቅርታ መጠየቁም አይዘነጋም።

ብርሃን እንደምትለው፤ ኢትዮጵያ ሰላማዊ አገር ብትሆን ኖሮ አንድ ሰው ተነስቶ "ትግራዋይ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ ወይም የሌላ ብሔር ተወላጆችን ግደሉ" ቢል የተቀረው ማኅበረሰብ ከመከተል ይልቅ ሊተቸው ይችላል።

ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በግጭት እየተናጠች ስለምትገኝ ከስልክ እና ከኮምፒውተር ጀርባ ያለ ነውጠኛ ጽሑፍ በቀላሉ ክፉ ድርጊት ያስከትላል።

"ደኅና ሰው ነው፤ እንዲህ አያስብም የሚባለው ሁሉ የጥላቻ ንግግር ሲጽፍ ጎረቤቴስ ማነው? ብለሽ እንድታስቢ ያደርጋል" ትላለች።

በብርሃን አስተያየት "ግደሏቸው፣ እሰሯቸው" የሚሉ ጽሑፎች ጥቃት እንዲባባስ ያደርጋሉ። ነገ ደኅና እንደማይሆን እንዲሰማን የማድረግ ጉልበትም አላቸው።

ትምኒት፤ ይፋዊ የጥላቻ ዘመቻዎች ሕዝብን እንደሚያጫርሱ ስትናገር ምሳሌ የምትሰጠው እአአ በ1994 በሩዋንዳ የተፈጸመውን የዘር ጭፍጨፋ ነው።

በ100 ቀናት ውስጥ ወደ 800,000 ቱትሲዎች በሁቱ አክራሪዎች የተጨፈጨፉበት አሳዛኝ ክስተት ነው። የያኔው ሁቱ የሩዋንዳ ፕሬዘዳንት ጁቬናል ሀቢያሪማና የተሳፈሩበት አውሮፕላን ተመትቶ ከወደቀ በኋላ "ቱትሲዎችን እናጥፋ" የሚል ንቅናቄ በራድዮ እና በአደባባይም ተጀመረ። ብዙም ሳይቆይ ግድያው ከቁጥጥር ውጭ ሆነ።

"ሰዎች በፌስቡክ የሚያዩት ነገር ይፋዊ (Official) ይመስላቸዋል። በተደጋጋሚ ሲያዩት ጥላቻን ያሳድራሉ። ሰብአዊነታቸው ይጠፋል። ሌላው ሰው ምን ዓይነት ስቃይ እየገጠመው እንደሆነ ማየት ያቆማሉ" ስትል ትምኒት ታስረዳለች።

በፌስቡክ የሚተላለፍ ይዘት ማስረጃ ሳይጠየቅበት፣ እውነት ነው ወይስ ውሸት የሚለው ሳይጣራ በርካቶች ዘንድ ይደርሳል።

አንድን ቡድን ወይም ብሔር የሚያጥላሉ ንግግሮች፣ ጽሑፎች ወይም ምስሎች በስፋት ከተሰራጩ በኋላ "አሁን ጥቃት ሰንዝሩባቸው" ሲባል ሰብአዊነትን የሚያስረሳ በስሜት መነዳት ይከሰታል።

የጥላቻ ንግግሮች ሲደጋገሙ አንዳች የደቦ ስሜት የመፍጠር ኃይል እንዳላቸውም ትምኒት ትናገራለች።

የሜታ (ፌስቡክ) ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጠችው ምላሽ፤ ድርጅቱ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ከፍተኛ ነውጥ ባለባቸው አገሮች ገጹ ያላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል እየሠራ ነው።

"በሰብአዊ መብት እና በግጭት ቅነሳ ላይ የሚሠሩ አጋሮቻችን አክራሪነትን፣ የጥላቻ ንግግርን እንዲሁም የሐሰት መረጃን ይቀንሳሉ" ትላለች።

line

ፌስቡክ ከጥላቻ ንግግር ምን ያተርፋል?

በአሜሪካ ኮንግረስ ቀርባ ምስክርነት የሰጠችው የቀድሞዋ የፌስቡክ ሠራተኛ ፍራንሲስ ሐውገን እንዳለችው፤ ኢትዮጵያ በፌስቡክ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸው ዝርዝር ውስጥ ብትካተትም፤ የይዘት ፍተሻው በኢትዮጵያ ካሉት ግጭትን የሚያባብሱ ጽሑፎች ጋር ተመጣጣኝ አይደለም።

የድርጅቱ ሠራተኞች ፌስቡክ "መንግሥት እና የውጭ ድርጅቶችን ጨምሮ በሌሎችም ኃይሎች ያላግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ" እንደሆነ ለፌስቡክ አመራር እንዳስጠነቀቁ ከድርጅቱ ሾልኮ የወጣ ሰነድ ይጠቁማል።

ሰነዱ ፌስቡክ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎችም ታዳጊ አገሮች ግጭትን ለማስቆም በእነዚህ አገሮች የሚነገሩ ቋንቋዎችን የሚችሉ ሠራተኞችን ቁጥር አልጨመረም ይላል።

አምና መጋቢት ላይ የወጣ ሪፖርት እንደሚያትተው ደግሞ፤ በኢትዮጵያ የታጠቁ ቡድኖች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔሮች ላይ ጥቃት ለማነሳሳት ፌስቡክን ተጠቅመዋል።

በሪፖርቱ ጥቆማ ከተደረገባቸው ቡድኖች አንዱ "ፋኖ" ነው። ከዚህ ቡድን ጋር ግንኙነት ካላቸው የፌስቡክ ገጾች የተወሰኑት መነሻቸው ሱዳን ነው።

የፌስቡክ ሠራተኞች "ከፋኖ ቡድን ጋር ተያያዥ የሆኑ ገጾች የግጭት መልዕክትን አስተላልፈዋል። ከፌስቡክ ይነሱ" ብለው ለፌስቡክ አመራሮች መጠቆማቸውን ሪፖርቱ ይገልጻል።

ከኦሮሞ ዳያስፖራ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉና በብዛት መነሻቸውን ግብፅ ያደረጉ ገጾችም ተጠቁመዋል።

እነዚህ ገጾች "በሌሎች ብሔሮች ላይ እና የመንግሥት ባለሥልጣኖች ላይ ጥቃት እንዲሰነዘር በግልጽ ሲያነሳሱ ነበር" ተብለው ከፌስቡክ እንዲሰረዙ ተወስኗል።

ፍራንሲስ ሐውገን እንደተናገረችው፤ ፌስቡክ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሚሠራበት መንገድ ያሰጋል። ብዙዎችን የሚያነጋግሩ ይዘቶችን ወደ ገጹ አናት ማምጣት (Engagement Based Ranking) የብሔር ግጭትን እያፋፋመ ነው።

"በቀጣይ 5 እና 10 ወይም 20 ዓመታት ብዙ ሰዎች ይሞታሉ ብዬ እሰጋለሁ። ምክንያቱም የይዘት ፍተሻ አለመሠራቱ ነው። ኢትዮጵያ እና ሚያንማር ገና መነሻው ናቸው። ለወደፊት ብዙ ጥፋት ይጠብቀናል።"

ባለፉት ሁለት ዓመታት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞች ፌስቡክ ለግጭት መባባስ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ ነበር። በተለይም በሚያንማር የተከሰተውን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ልዑካንን ጨምሮ ኢትዮጵያ በፌስቡክ ትኩረት እንዲሰጣት ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ብርሃን፤ ፌስቡክ ከተጠቃሚዎቹ ደኅንነት ገቢውን እንደሚያስቀድም ታስረዳለች።

"ፌስቡክን በነጻ ብንጠቀምም በገጹ የምንሸጠው ግን እኛ ነን። ፌስቡክ ገንዘብ የሚያገኘው ከማስታወቂያ ነው። በኢትዮጵያ ብዙ የፌስቡክ ተጠቃሚ ሲኖር ፌስቡክ ላይ የሚያስተዋውቁ ድርጅቶች ብዙ ገንዘብ ይከፍሉታል። ፌስቡክ ይህንን የንግድ ትስስር ማዛባት አይፈልግም።"

በኢትዮጵያ ያለው የፌስቡክ ተጠቃሚ ቁጥር ከአውሮፓ እና ከእስያ አንጻር ውስን ስለሆነ ኢትዮጵያ ላይ ማተኮር አይፈልግም።

ይዘት ለመፈተሽ ሰው ሠራሽ ልህቀት (Artificial Intelligence) ይጠቀማል። ማሽኑ በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ እና በሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ካልሠለጠነ ግን ይዘቶች በአግባቡ አይፈትሹም።

ብርሃን የፌስቡክ እና የኢትዮጵያን ጉዳይ አታካች አዙሪት (Vicious Circle) ትለዋለች። አዙሪቱም እንዲህ ይገለጻል . . .

»»»ፌስቡክ በኢትዮጵያ ብዙ ተጠቃሚ የለውም »»» ብዙ ተጠቃሚ ስለሌለ ብዙ ገንዘብ ከኢትዮጵያ አይገኝም »»» ብዙ ተጠቃሚ ከሌለ እና ገንዘብ ካልተገኘ ለይዘት ፍተሻ ትኩረት አይሰጥም »»» ለይዘት ፍተሻ ትኩረት ካልተሰጠ ግጭት ይፋፋማል »»» ፌስቡክ ለኢትዮጵያ ትኩረት እንዲሰጥ የተጠቃሚ ቁጥር ቢጨምር የዚያኑ ያህል ችግሩ ይንራል»»»

ትምኒት በዋነኛነት የምትተቸው ፌስቡክ ለመረጃዎች ቅደም ተከተል የሚሰጥበትን አሠራር (Ranking Algorithm) ነው።

ሁሉም የፌስቡክ ተጠቃሚ የሚለጥፈው እኩል በገጹ አይታይም። በፌስቡክ ምዘና ነው ቅደም ተከተሉ የሚወጣው። ምዘናው ግን የተዛባ እንደሆነ ትምኒት ታስረዳለች።

ሰውን የሚያበሳጭ ይዘት ወደፊት እንዲመጣ ቅድሚያ ይሰጠዋል። ምክንያቱም የሚያናድድ ይዘት በገጹ ተጠቃሚዎች ንቅናቄ (Engagement) ይፈጥራል። ማለትም ሰዎች እንዲያጋሩ (Share)፣ እንዲወዱ (Like)፣ አስተያየት እንዲሰጡ (Comment) ያነሳሳል።

ብዙዎች ሼር፣ ላይክ እና ኮመንት ሲያደርጉ ፌስቡክ ላይ ዘለግ ያለ ጊዜ ስለሚያጠፉ ማስታወቂያ ያያሉ። ፌስቡክም ገንዘብ ያተርፋል።

"ፌስቡክ ቅድሚያ የሚሰጠው ለገንዘቡ ስለሆነ ለይዘት ፍተሻ ተጨማሪ ወጪ አያወጣም። ፌስቡክ ለደኅንነት ቅድሚያ ይስጥ የሚል አስገዳጅ ሕግም የለም።"

line

ጥቆማ የተደረገባቸው ይዘቶች ለምን ቶሎ አይሰረዙም?

አምነስቲ ከሰሞኑ ባወጣው ሪፖርት፤ ከጦርነቱ መባባስ ጋር በተያያዘ የብሔር ግጭትን የሚቀሰቅሱ ጽሑፎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መበራከታቸው አስግቶኛል ብሏል።

የተቋሙ የምሥራቅ አፍሪካ እና ደቡብ አፍሪካ ኃላፊ ዴፕሮሴ ሙቺና፤ "የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ግጭት የሚያመሩ የጥላቻ ንግግሮችን የመገደብ ኃላፊነት አለበት። ይዘቶቹን ሊያወግዛቸው ይገባል። የማኅበራዊ ሚዲያ ተቋሞችም የይዘት ፍተሻ አሠራራቸውን በአፋጣኝ ያጠናክሩ" ብለዋል።

በፌስቡክ የሚለጠፉ የጥላቻ ንግግሮች ወይም ግጭት የሚያነሳሱ ይዘቶች ጥቆማ (Report) ሲደረግባቸው የሚወርዱበት ፍጥነት አከራካሪ ነው።

ጦርነቱን ከግምት በማስገባት ፌስቡክ ለኢትዮጵያ ጠንካራ የይዘት ፍተሻ አሠራር መዘርጋት ነበረበት ትላለች ትምኒት።

በእሷ አስተያየት፤ አንድ ይዘት ጥቆማ ከተደረገበት በኋላ ፌስቡክ እስኪጣራው ድረስ ይዘቱን ብዙዎች እንዳያዩት መገደብ አለበት።

ፌስቡክ ላይ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ ወይም ብዙ ተከታይ ያላቸው ሰዎች ገጻቸው ፍተሻ ሊደረግበት እንደሚገባ ታምናለች።

በተያያዥም፤ ይዘቶችን በአፋጣኝ ከማውረድ ባሻገር፤ ይዘቱን ያጋራው ገጽ ባለቤት ሌላ መጥፎ ይዘት እንዳይለጥፍ እርምጃ እንዲወሰድ ትመክራለች።

አንዳንዴ ብዙ ሰው ስለጠቆመ ብቻ ጤናማ ይዘቶች በስህተት ይወርዳሉ። ይህም የይዘት ፍተሻ ክፍተት ተጨማሪ ማሳያ ነው።

በሌላ በኩል ፌስቡክ ከሰብአዊ መብት፣ የዘር ማጥፋት ተከላካይ እና የማኅበረሰብ ባለሙያዎች ጋር ተጣምሮ እንዲሠራ ታሳስባለች።

በሰው ሠራሽ ክህሎት የሚተረጎሙ ይዘቶች ከዐውድ የሚወጡበት አጋጣሚ አለ። ትምኒት እንደ ምሳሌ የምትጠቅሰው 'እናጽዳ' የሚለውን ቃል ነው።

ቃሉ ጥቅም ላይ የዋለው ሰዎችን ለማጥፋት እንደሆነ ካልታወቀ፤ እንደ በጎ ንግግር ተወስዶ ችላ ሊባል ይችላል። ከማሽን ጎን ለጎን የኢትዮጵያን ዐውድ የሚገነዘቡ በርካታ ሠራተኞች መቅጠር የሚመከረውም ለዚህ ነው።

ብርሃንም የትምኒትን ሐሳብ ትጋራለች።

"ለምሳሌ 100 ግደለው፣ ደብድበው፣ አውድመው የሚሉ መልዕክቶች ላይ ጥቆማ ቢደረግ 80 በመቶው ከመርሐችን ጋር አይጻሩም ተብለው አይሰረዙም" ትላለች።

ብርሃን እንደምትገልጸው፤ ፌስቡክ ባደረገው ዳሰሳ የሰው ሠራሽ ክህሎት ቴክኖሎጂው እንደ አማርኛ እና ኦሮምኛ ባሉ ቋንቋዎች የማጣራት ክፍተት እንዳለበት ደርሶበታል።

"ችግሩ ዘርፈ ብዙ ነው። ዐውድ አለመረዳት እና ግድ የለሽነትን ያካትታል። ባለፈው የትግራይ ተወላጆች 'ተሰብስበው የግዳጅ ማቆያ (Concentration Camp) ውስጥ ይግቡ' የሚል ለአሁናዊ አደጋ የሚያጋልጥ ጽሑፍ ጥቆማ ቢደግበትም ከ24 ሰዓት በላይ አልተነሳም። አምና ሰኔ ላይ 'ሰው በዚህ መንገድ ይገደል' የሚል ምስል ተጠቁሞ እስካሁን አልተነሳም" ትላለች።

የአውሮፓ ሕብረት እና ሌሎችም ሀብታም አገሮች እንደ ፌስቡክ ያሉ የቴክኖሎጂ ተቋሞች በግዛታቸው የሚሠሩበትን መርሕ ያወጣሉ።

ኢትዮጵያ ግን አሁን ላይ ይህንን የማድረግ ኃይል ስለሌላት የመጨረሻ መፍትሔው በተጠቃሚዎች እና በፌስቡክ እጅ ይወድቃል።

የሜታ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ በሰጠችው ምላሽ፤ ፌስቡክ በኢትዮጵያ የጥቆማ መስጫ መንገድ ቀላል እና ፈጣን እንዲሆን ማሻሻያ አድርጓል።

"የተጠቆሙትን እንመረምራለን። ፖሊሲዎቻችን በአማርኛ እና በኦሮምኛ ተተርጉመዋል። የአገር ውስጥ እና የውጭ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና የሲቪል ማኅበራት የሚጠቁሙበት አሠራር አለን። እነሱ ጎጂ ናቸው የሚሏቸውን ይዘቶች ቅድሚያ ሰጥተን እንመረምራለን።"

ፌስቡክ የይዘት ፍተሻ የሚያከናውነው ከገለልተኛ፣ ሦስተኛ ወገን ጋር ተጣምሮ ነው። የኢትዮጵያ ይዘት ፍተሻ በፔሳ ቼክ እና በኤኤፍፒ ፋክት ቼክ ተቋሞች በኩል ይከናወናል።

አንድ መረጃ ሐሰተኛ ነው ተብሎ ሲጠቆም ይዘቱን የሚያዩ ሰዎች ቁጥር እንደሚገደብ እና የማስጠንቀቂያ ጽሑፍ እንደሚለጠፍበት ቃል አቀባዩዋ ታስረዳለች።

በተጨማሪም የጥላቻ ንግግሮች ወይም ግጭት ቀስቃሽ ይዘቶች በሰው ሠራሽ ክህሎት ሲጠቆሙ፤ እስኪጣሩ ድረስ ስርጭታቸው ይገደባል ትላለች።

"በተደጋጋሚ ከፌስቡክ ፖሊሲ ጋር የሚጻረር ጽሑፍ የተገኘባቸው ሰዎች የሚጽፏቸው ጽሑፎች በአጠቀላይ የሚደርሷቸው ተመልካቾች ቁጥር እንዲገደብ እናደርጋለን።"

ፌስቡክ ይህን ቢልም አሁንም ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ ስሙ እየተብጠለጠለ ነው። በየደቂቃው የሚሰራጩ ነውጠኛ ይዘቶች በዜጎች ላይ የሚያስከትሉት ጉዳትም ስጋት እንደሆነ ቀጥሏል።

የሚያንማር ቀውስ ካለፈ በኋላ ፌስቡክ 'ይቅርታ' እንደጠየቀው ሳይዘገይ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ባለሙያዎቹ ብርሃን እና ትምኒት ያሳስባሉ።