ፌስቡክ “ከጥላቻ ትርፍ እያገኘ ነው”

ፌስቡክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አንድ የቀድሞ የፌስቡክ ባልደረባ ድርጅቱ “ከጥላቻ ትርፍ እያገኘ ነው” በሚል የድርጅቱ አካል መሆን አልሻም ሲል በገዛ ፍቃዱ ከስራው ተሰናብቷል።

በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ የፌስቡክ ሰራተኞ ድርጅቱ የጥላቻ ንግግርን ለማስወገድ በቂ እርምጃ አልተጓዘም በሚል ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀዋል።

የቀድሞ የፌስቡክ ቅጥረኛ የነበረው ኢንጅነሩ አሾክ ቻንደዋይን “የተሳሳተው የታሪክ አካል መሆን አልሻም” ብሏል። ፌስቡክ በሌሎች ጉዳዮች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስድ አስታውሶ ከጥላቻ ንግግሮች ጋር በተያያዘ ግን ጠንከር ያለ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቧል ብሏል።

ፌስቡክ በበኩሉ ከጥላቻ ንግግር ጋር የተያያዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ፖስቶችን ከገጹ ስለማጥፋቱ አስታውቋል።

ቻንደዋይን እንደሚለው ከሆነ ግን የፌስቡክ መተግበሪያን ፍጥነት የሚቀንስ አንዳች እክል ሪፖርት ከተደረገ፤ ችግሩ በአስደናቂ ፍጥነት ይቀረፋል። ከጥላቻ ጋር የተያያዙ መልዕክቶች ላይ ግን ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ፍላጎት የለም ብሏል።

በወረሃ ሐምሌ ላይ ፕሬዝደንት ትራምፕ ከ “ብላክ ላይቭስ ማተር” የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩትን መልዕክት ፌስቡክ እንዲያጠፋው በርካቶች ጠይቀው ነበር።

ትዊተር በወቅቱ ይህንኑ ተመሳሳይ የፕሬዝደንቱ መልዕክት እውነተኝነቱ ያልተረጋገጠ ስለሆነ ተጠቃሚዎች እውነታ እንዲያመሳክሩ ምልክት አኑሮ ነበር።

ፌስቡክ ግን በፕሬዝደንቱ መልዕክት ላይ ምንም አይነት እርምጃ ባለመውሰዱ በርካታ የድርጅቱ ሠራተኞች ስራቸውን በግል ፍቃዳቸው ለቀዋል። ተቃውሟቸውን ለማሰማትም በርካታ ሰራተኞች ከመስሪያ ወንበራቸው ተነስተው ወደ ደጅ በመውጣት ድምጻቸውን አሰምተዋል።

ትራምፕ በወቅቱ ለጥፈውት የነበረው የትዊተር መልዕክት ተቃውሞን ለመቆጣጠር ተጨማሪ የፖሊስ ኃይል እንደሚልኩ እና “ዘረፋ ሲጀመር፤ ተኩስ ይከፈታል” የሚል ነበር።