2012 ፡ ኮሮናቫይረስ ያጠላበት የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብ፡ “አርቲስቶች ቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸዋል”

የአዲስ ዓመት ልዩ ጥንቅር
የተለያዩ የጥበብ ሥራዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty/BBC

ነሐሴ 17 ቀን 2012 ዓ. ም ከሰዓት “ንጋት” የተሰኘ ኮንሰርት ነበር።

ዘሪቱ ከበደ፣ ኃይሌ ሩትስ፣ ፍቅርአዲስ ነቃዓጥበብ፣ ጌቴ አንለይ፣ ሔኖክ መሐሪ፣ ቤቲ ጂ እና ሌሎችም ድምጻውያን ያለ ታዳሚ ሙዚቃቸውን አቅርበው በኢቢሲ፣ በዋልታና በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ተላልፏል።

ታዳሚዎች ቤታቸው ሆነው ኮንሰርቱን በቴሌቭዥን እየተከታተሉ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሐሳብ ሲለዋወጡ ነበር።

የኮሮናቫይረስ ባስከተለው ተጽእኖ በበርካታ አገሮች ኮንሰርቶችና የአደባባይ ፌስቲቫሎች ቆመዋል። በኢትዮጵያም ቴአትር፣ የሙዚቃ መሰናዶ፣ ዓውደ ርዕይ ወዘተ. . . ከተገቱ ከአምስት ወራት በላይ ተቆጥረዋል።

የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ለወትሮው እንደሚያደርጉት በመቶዎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ሥራቸውን እንዲያዩ መጋበዝ አልቻሉም።

በበይነ መረብ ኮንሰርት እንዲሁም የሥዕል ዓውደ ርዕይ ያካሄዱ ጥቂት ሙዚቀኞችና ሠዓሊዎች አሉ። ሆኖም ግን አጠቃላይ የሥነ ጥበብ ዘርፉ 2012 ላይ እጅግ ተቀዛቅዞ ከርሟል።

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ሥነ ጥበብ ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደረ? የጥበብ ሰዎችስ ዓመቱን እንዴት አሳለፉ? ስንል ወደኋላ መለስ ብለን ቃኝተናል።

መስመር

ሙዚቃ

"ሙሉ በሙሉ የመድረክ ሥራ ላይ ለተመረኮዘ ሙዚቀኛ በጣም ከባድ ነው" ሔኖክ መሐሪ

"ንጋት" በዓመቱ ከወጡ አልበሞች አንዱ ነው። ከአልበሙ የሚገኘውን ገቢ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ለሚያደርው ጥረት እንዲውለው በሙዚቀኞቹ ተሰጥቷል።

አልበሙ ከወጣ በኋላ ደግሞ "ንጋት" የተባለው ታዳሚ አልባ ኮንሰርት ተካሂዷል።

ሙዚቀኛ ሔኖክ መሐሪ እንደሚለው፤ ኮንሰርቱ የተዘጋጀው ሕዝቡ ቤቱ ሆኖ መዝናናት እንደሚችል ለማሳየትና ቫይረሱ ያስከተለውን ድብርት ለመቀነስ ነው።

"ሙዚቃ የሚሰማው በድግስ ብቻ ሳይሆን በሀዘን፣ በድብርት ወቅትም ነው" የሚለው ሔኖክ፤ ሙዚቃ አንዳች መጽናኛ እንደሚሆን ያስረዳል።

በሌላ በኩል ሙዚቀኞችን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በገንዘብ ለመደገፍ ተሞክሯል። ከተለያዩ ከተሞች በተወጣጡ ሙዚቀኞች ሌሎች ተመሳሳይ ኮንሰርቶች የማዘጋጀት እቅድም አላቸው።

"በኮንሰርቱ አማካይነት ወደ 24 የሚሆኑ በህመምና በሌላም ምክንያት ችግር ውስጥ ያሉ ሙዚቀኞች ቤተሰቦችን ደግፈናል" ይላል።

ኮንሰርቶችና ፌስቲቫሎች እንዲሁም ሌሎችም ሙዚቃን ያማከሉ መሰናዶዎች በመሰረዛቸው ድምጻውያን፣ የመድረክ ግብዓት አቅራቢዎች፣ አዘጋጆች ወዘተ. . . ተጎድተዋል።

መደበኛ ተቀጣሪ ያልሆኑና ገቢያቸውን ከሙዚቃ ዝግጅቶች የሚያገኙ ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ እንደገጠማቸው እሙን ነው።

ሙዚቀኛ ሄኖክ

የፎቶው ባለመብት, DUDU

እንዲሁም የቅጂ መብት ጥሰት ጫና ያሳደረበት ሙዚቃው፤ ኮሮናቫይረስ ሲጨመርበት ለባለሙያዎች ፈታኝ እንደሆነ ሔኖክ ይናገራል።

"ኮንሰርት፣ የምሽት ክለብ ሥራና ሌላ መሰናዶ ቆሟል። ሙሉ በሙሉ የመድረክ ሥራ ላይ ለተመረኮዘ ሙዚቀኛ በጣም ከባድ ነው። ተቀማጭ፣ ጡረታ የለውም። ዘፋኙ ስቱድዮ ሲሄድም በኪስ ገንዘቡ ነው የሚሠራው።”

ወረርሽኙ ካመጣው የምጣኔ ሀብት ጫና ባሻገር ግን ለፈጠራ ሰዎች የጽሞና ጊዜ መስጠቱ አይካድም። ሔኖክም የመጀመሪያዎቹን አራት ወራት ከቤተሰብ ጋር ዘለግ ያለ ጊዜ በመቆየት፣ ሙዚቃ በመሥራት አሳልፏል።

ወራት በወራት ላይ እየተደራረቡ ሲመጡ አብዛኛው ሰው ድብርት እየተጫጫነው መምጣቱንም፤ "ሰዋዊ የሆነውን ሰላምታ፣ መተቃቀፍና በነጻነት መተንፈስ ቀማን" በማለት ይገልጻል።

በሌሎች አገራት ሙዚቀኞች ሥራቸውን በተለያዩ መተግበሪያዎች ያቀርባሉ፣ ይሸጣሉም። ይህ ግን የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሙዚቀኛ እውነታ አይደለም።

ገቢያቸውን በምሽት ክለቦች፣ በኮንሰርቶችና በፌስቲቫሎች የሚያገኙ ሙዚቀኞች ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደወደቁ የሰላም ኢትዮጵያ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሲሳይ መንግሥቴ ያስረዳል።

አዝማሪዎች በየዕለቱ ይሠሩባቸው የነበሩ የባህል ቤቶችና የምሽት ክበቦች አሁን ላይ ተቀዛቅዘዋል።

አሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል ሲከበር በአማራ እንዲሁም በትግራይ ክልል ድምጻውያን ያለ ታዳሚ ተቀርጸው በአማራ ቴሌቭዥንና በድምጺ ወያነ እንዲሰራጭ ማድረጋቸውን ሲሳይ ይናገራል።

"አርቲስቱ ያለበት ሁኔታ አሳዛኝ ነው። ለምሳሌ በአማራ ክልል ወደ ዶሮ እርባታ የገቡ አርቲስቶች አሉ" ሲል ሁኔታውን ይገልጻል።

ኮሮናቫይረስ ያሳደረውን የምጣኔ ሀብት ቀውስ በመጠኑም ለማቃለል ለአዲስ ዓመት ሙዚቀኞችን ያለ ታዳሚ ቀርጾ የማስተላለፍ እቅድ አላቸው።

"በቴሌቭዥን የሚተላለፈው መንግሥትም አርቲስቶቹን እንዲደግፍ ለማነሳሳት ነው።"

ሲሳይ እንደሚለው፤ ቨርችዋል ኮንሰርት [የበይነ መረብ ኮንሰርት] ሲዘጋጅ ለመድረክ፣ ለመብራት፣ ለባንድ የሚወጣው ወጪ ከመደበኛ ኮንሰርት እኩል ነው። ሙዚቀኞቹ ግን የሚከፈላቸው እንደሌላው ኮንሰርት አይደለም።

"አርቲስቶቹ ቁጭ ከሚሉ፣ ከሚቸገሩ፣ ከሚጨነቁ በሚል ነው እንጂ ገቢው ያን ያህል አይደለም። መሠረታዊን ወጪ ከመሸፈን አያልፍም። ማሳተፍ የሚቻለውም ጥቂት አርቲስቶች ብቻ ነው። ይህ በድርጅት ብቻ የሚሸፈን አይደለም" በማለትም ድጋፍ ሰጪ እንደሚያሻ ይጠቁማል።

መስመር

ሥነ ጥበብ

"ገበያው ዜሮ ሆኗል" ኑሩ አበጋዝ

ላፍቶ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ጋለሪ በወራት ልዩነት ዓውደ ርዕዮችን የሚያስተናግድ፣ የሥነ ጥበቡን ማኅበረሰብም የሚያስተሳስር ነበር። ላለፉት ስድስት ወራት ግን እንቅስቃሴው ተገቷል።

ሠዓሊና የጋለሪው ኪውሬተር ኑሩ አበጋዝ እንደሚለው፤ ዓውደ ርዕዮች መቆማቸው ሠዓሊዎች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መቋረጣቸው እንዲሁም ሆቴሎች ኪሳራ ውስጥ መግባታቸው የሥነ ጥበብ ገበያውን አዳክሞታል።

"የጋለሪ ሥራ ጥበቡን ወደ ገበያ ማውጣት ነው። አሁን ግን ገበያው ዜሮ ሆኗል። ዓውደ ርዕይ ማካሄድ ስላልተቻለ ግን ቨርችዋል ኤግዚብሽን [የበይነ መረብ ዓውደ ርዕይ] አዘጋጅተናል።"

ጋለሪው በድረ ገጹ ላይ 'ስታግናንት ታይም' የተባለ ዓውደ ርዕይ ያሳያል። የዳዊት አድነው፣ የሰይፉ አበበና ሌሎችም ሠዓሊዎች ሥራዎች ስብስብ በተንቀሳቃሽ ምስል ይታያል።

ኑሩ አበጋዝ

የፎቶው ባለመብት, Nuru Abegaz

"ዓውደ ርዕይ እንደማሳየት አይሆንም። ግን ያሉትን ሥራዎችን ያስተዋውቃል። በድረ ገጹ ስልክ ቁጥር አስቀምጠናል። ሥዕሎች ሲሸጡ በዲኤችኤል መላክም ይቻላል" ይላል።

ዓውደ ርዕይ፤ ባለሙያዎች የሚገናኙበት፣ አንዳቸው ሌላቸውን የሚያነሳሱበት፣ ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ ሥራቸውን የሚሸጡበት፣ እርስ በእርስ የሚወያዩበትም ነው።

"ይህ ሲቀር ብዙ ነገር እንዳጣን ይሰማናል። ብዙ ሠዓሊ ራሱን ነው የሚያስተዋውቀው። ሰው አለማግኘት ትስስሩን መስበር ማለት ነው። ተጓዳኝ ሥራ የሌለውና ሥዕሉ ላይ ብቻ ለሚያተኩር ባለሙያ ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል።”

ሠዓሊዋ ሮሻን ሁኒሀንኒም የኑሩን ሐሳብ ትጋራለች። ሥዕል አልፎ አልፎ ካልሆነ እንደማይሸጥና ተጓዳኝ ሥራ ከሌለ ነገሮች ከባድ መሆናቸውን ትናገራለች።

"ወቅቱ ለሁሉም ሰው አዲስ ነው። ዓለምን ሁሉ በጥብጦ ኑሯችንን የቀየረው ነገር ምንድን ነው? በቀጣይስ ወዴት እንሄዳለን? የሚለው ያሳስበኛል። ከሌሎች አርቲስቶች ጋር መገናኘት የሚቻለው በኢንተርኔት ብቻ ሆኗል" ትላለች።

መስመር

ቴአትር

"ቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው ወደ ዘመድ ቤት የሄዱ አሉ" ማንያዘዋል እንደሻው

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤትን ጨምሮ ሌሎችም ሰው የሚሰበሰብባቸው አዳራሾች ሥራ ያቆሙት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ነበር።

የብሔራዊ ቴአትር ተቀጣሪዎች ደሞዝ አልተቋረጠም። ሆኖም ደሞዙ ትንሽ ነው። ተዋንያን፣ ሙዚቀኞች፣ ተወዛዋዦች የሚተዳደሩባቸውን ተጨማሪ ሥራዎች በማጣታቸው ከፍተኛ ችግር እንደገጠማቸው የቴአትር ቤቱ ሥራ አስኪያጅ ማንያዘዋል እንደሻው ይናገራል።

"የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው ወደ ዘመድ ቤት የሄዱ አሉ። በተጋባዥነት የሚሠሩ፣ ሁለት ሦስት መድረክ የሚሠሩ ተቸግረዋል። በኢ መደበኛ ሁኔታ ከውጪ ገንዘብ አሰባስቤ ባከፋፍልም በቂ አይደለም" ሲል ችግሩን ይገልጻል።

ማስወቂያና ፊልም በመሥራት ራሳቸውን የሚደግፉ ተዋንያን እንዲሁም በምሽት ክለቦችና ኮንሰርቶች ላይ የሚሠሩ ድምጻውያንና ተወዛዋዦች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር "የማገገሚያ ስልት" የሚል የዘርፉን ባለሙያዎች ሊደግፍ የሚችል ሐሳብ ቢያቀርብም ገና እንዳልተተገበረ ይናገራል።

"በጣም ዘግይቷል። ቶሎ መድረስ አለበት። የቴአትር ባለሙያዎችና ሙዚቀኞችም ደሞዛቸው ትንሽ ነው። ድጋፍ ይፈልጋሉ። አሁን ባሉበት ሁኔታ ከቀጠሉ አስጊ ነው። የእኛ ሐሳብ ከመስከረም ወዲያ ተዋንያንም ተመልካቾችም ርቀታቸውን ጠብቀው ሥራ መጀመር ነው።"

ሌላው አማራጭ ሐሳብ ተመልካች በሌለበት ተውኔቶችን መድረክ ላይ ቀርጾ በቴሌቭዥን እያስተላለፉ ሙያተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው።

ማንያዘዋል እንደሻው

የፎቶው ባለመብት, Adeyabeba

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ሥነ ጥበብን በዚህ ወረርሽኝ ወቅት እንዴት ይቀጥል ብሎ ያቀረበውን በመውሰድ በዙም [የኢንተርኔት መድረክ] ውይይት መደረጉን ማንያዘዋል ያስታውሳል።

ከሐሳቦች በዘለለ ለባለሙያዎች አፋጣኝና ተጨባጭ መፍትሔ የሚሰጥ ነገር አለ ለማለት ግን ይቸገራል።

"በሕይወቴ እንዲህ ያለ ነገር ገጥሞኝ አያውቅም። ለብዙዎቻችን አዲስ ነው። መፍትሔው እየተሞከረ ያለው ችግሩ ጉዳት እያደረሰ ሳለ ነው” ይላል።

ማንያዘዋል ከኮቪድ-19 ጋር ሚገናኝ "የእሳት አደጋ" የተባለ ቴአትር ወደ አማርኛ ተርጉሟል። በቴሌቭዥን ለማስተላለፍ ያነጋገራቸው ጣቢያዎች እንዳሉም ይናገራል።

መስመር

ሥነ ጽሑፍ

"የሰው ትንፋሽ ሕይወቱ የነበረ ከያኒ ተቋርጦበታል" እንዳለጌታ ከበደ

በ2012 ዓ. ም ላይ ለንባብ ከበቁ መጻሕፍት መካከል የሕይወት ተፈራ "ምንትዋብ" የዓለማየሁ ገላጋይ "ሐሰተኛው፡ በእውነት ስም"፣ የዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ "የራስ ምስል"፣ የታደለች ኃይለሚካኤል "ዳኛው ማነው" እና የእንዳለጌታ ከበደ "መክሊት" ይገኙበታል።

በእርግጥ የመጻሕፍት ህትመት ባይቋረጥም፤ የመጽሐፍ ምርቃቶችና የሥነ ጽሑፍ መሰናዶዎችም ከቆሙ ወራት ተቆጥረዋል።

ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ እንደሚለው፤ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞችም ተበራክተው የነበሩ የሥነ ጽሑፍ መድረኮች መቋረጣቸው እንደ ክፍተት ይነሳል።

ከሥነ ጽሑፉ በተጨማሪ በሐይማኖት፣ በፖለቲካና በሌሎችም ዘርፎች የሚታወቁ ሰዎች ሐሳባቸውን የሚያንጸባርቁባቸው የግጥምና የዲስኩር መድረኮች በርካታ ታዳሚ ያስተናግዱም ነበር።

"የሥነ ጽሑፍ ምሽቶቹ ቋሚ ደንበኛ ነበራቸው። አዳራሾች ይሞሉ ነበር። ኮሮናቫይረስ ሲመጣ ግን እነዚህ መድረኮች ተዘጉ። አዘጋጆቹ፣ አቅራቢዎቹ፣ አጃቢ ሙዚቀኞቹ፣ መድረክ አጋፋሪዎቹ ባጠቃላይ ገቢያቸው ተቋርጧል።"

መጻሕፍት ምርቃት መቅረቱም ዘርፉ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም።

በእርግጥ ወረርሽኙ ሌሎች የጥበብ ዘርፎች ላይ ያሳደረው ጫናን ያህል ሥነ ጽሑፉ አልተጎዳም።

እንዳለጌታ ወቅቱን የሚገልጸው ከገቢ አንጻር ብቻ ሳይሆን ከተፈጠረው ድባብም ጭምር ነው።

"የሰው ትንፋሽ ሕይወቱ የነበረ ከያኒ ተቋርጦበታል። የመድረክ ሰው የሰው ጭብጨባ ሲቋረጥበት ሥነ ልቦናዊ ጫና ያድርበታል። መስመር ላይ ያለነው ሰዎች ምንም ባንሆንም አንጋፋ ባለሙያዎች ቤት ኪራይ የሚከፍሉት ሲያጡ፣ የእለት ጉርስ ሲያጡ ይታያል። መንግሥት ድምጻውያንን እና ተወዛዋዦችን በዓል ማድመቂያ አድርጎ ጓዳችሁ እንዴት ነው? አይልም" ይላል።

ታዳሚ አልባ መሰናዶዎች፣ ኢቡክ [በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ መጻሕፍት የሚገኝባቸው] እና ሌሎችም ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ አማራጮች መጠቀም የግድ እንደሆነም ያሰምርበታል።

በሌላ በኩል ወቅቱ ለጸሐፍት እና ለአንባቢውም ፋታ፣ የጽሞና ጊዜ እንደሰጠ ያምናል። ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ ጭንቀት መጻሕፍት እፎይታ የሰጧቸውም ጥቂት አይደሉም።

በአዳራሽ ይካሄዱ ከነበሩ የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች ብዙዎቹ ሲቋረጡ፤ መሰናዷቸውን በቴሌቭዥን ማሰራጨት የጀመሩም አሉ። እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው ሰምና ወርቅ የሥነ ጽሑፍ ምሽት ነው።

የሥነ ጽሑፍ ምሽቱ ባለቤትና የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የሬድዮ መሰናዶ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ዓለሙ እንደሚለው፤ ታዳሚ አልባ መሰናዶዎችን በቴሌቭዥን ከማስተላለፍ ውጪ አማራጭ የለም።

"መጻሕፍት ቢታተሙም የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች፣ የመጻሕፍት ውይይቶችም እየተካሄዱ አይደለም። አንድ ሁለት ደራሲያን ዩቲዩብ ላይ ቻናል በመክፈት ሥራቸውን ሲያቀርቡ አይቻለሁ" ሲል ያስረዳል።

መስመር

ፊልም

"በነፃ የሚሠራው የጥበብ ሰው ሆኖ ድጋፍ ያጣውም የጥበብ ሰው ነው" ደሳለኝ ኃይሉ

ሲኒማውም እንደ ሌሎች የጥበብ ዘርፎች በኮቪድ-19 ሳቢያ ተጎድቷል። ፊልሞች በብዛት እየወጡ አይደለም። ሲኒማ ቤቶች ከተዘጉም ሰነባብተዋል።

ካለፉት ዓመታት አንጻር በ2012 ዓ. ም የወጡት ፊልሞች ውስን እንደሆኑ የኢትዮጵያ ፊልም ሠሪዎች ማኅበር ፕሬዘዳንት ደሳለኝ ኃይሉ ይናገራል።

"ፊቸር ፊልም ብቻ ሳይሆን ከተለያዩ ተቋሞች ጋር የሚሠሩ ዘጋቢ ፊልሞችም ቆመዋል። ተዋንያን፣ አዘጋጆች፣ ፕሮዲውሰሮች ወዘተ. . . ሥራቸውን አቋርጠዋል። ስንቶች ቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸዋል። ዘርፉ አሳዛኝ የኢኮኖሚ ድቀት ገጥሞታል። ባለሙያዎች ከዚህ ተርፈው ላይወጡም ይችላሉ።"

አንዳንዶች ሥራቸውን በዩቲዩብ ቢለቁም ያን ያህል ገቢ ያስገኛል ብሎ ለመናገር አያስደፍርም።

ደሳለኝ ኃይሉ

የፎቶው ባለመብት, Beakuwolde

የፊልም ሠሪዎች ማኅበርና ሌሎችም የኪነ ጥበብ ማኅበራት ከባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ጋር እንዴት ባለሙያዎች ማገገም ይችላሉ? በሚለው ዙርያ ተነጋግረው፤ እቅድ ቢነደፍም "እስከአሁን በተጨባጭ የአርቲስቱ ችግር ተፈቶ አላየንም" ይላል ደሳለኝ።

"ለሆቴልና ቱሪዝም የገንዘብ ድጋፍ ሲሰጥ በሚያሳዝን ሁኔታ የባህልና ጥበብ ዘርፉ ተረስቷል። መድሏዊ ነው። ይሄ አርቲስቱን አስከፍቶታል፤ አማሮታል።"

ስለ ኮቪድ-19 ግንዛቤ የሚሰጡ የኪነ ጥበብ ዝግጅቶች፣ የቴሌቭዥን እና የራድዮ ድራማዎች በነፃ ለሚያዘጋጁ ባለሙያዎች አንዳችም ድጋፍ አለመደረጉ እንደሚያሳዝን "ሕይወቱን አደጋ ውስጥ ከቶ በነፃ የሚሠራው የጥበብ ሰው ሆኖ ድጋፍ ያጣውም የጥበብ ሰው ነው" በማለት ይገልጻል።

በቀጣይ ወራት ሲኒማ ቤቶች እና ቴአትር ቤቶች ተከፍተው፤ ባለሙያዎችና ታዳሚዎችም አካላዊ ርቀት ጠብቀው፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አድርገው ሥራ የሚጀምሩበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት ደሳለኝ ይናገራል።

"ማንም ስድስቱን ወር መቋቋም አልቻለም። አርቲስቱ የሚበላው እየተቸገረ ነው። ከዚህ በላይ መቆየት ስለማይቻል ከጤና ሚንስትር እና ከጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ጋር እየተነጋገርን ነው። ጥንቃቄ እየተደረገ ሥራ መጀመር አለበት።"

የአዲስ ዓመት ልዩ ጥንቅር