ቢቢሲ በአማራ ክልል በተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ የሠራው ዘገባ ሽልማት አሸነፈ

ቢቢሲ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ጦርነት የተፈጸሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን በሚመለከት በሠራው ጥልቅ የምርመራ ዘገባ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ዩኬ የመገናኛ ብዙኃን ሽልማት (ሚዲያ አዋርድ) አሸነፈ።
ሽልማቱ በምርጥ የፊቸር ዘገባ (Best Written Feature) ምድብ የተሠጠ ሲሆን፣ "ቢገድሉኝ ይሻል ነበር"፡ የሴቶችን ሕይወት እያበላሸ ያለው የተዘነጋው የአማራ ክልል ጦርነት በሚል ርዕስ የቀረበ ነው።
ዘገባውን ለመሥራት ለስድስት ወር ያህል ጥልቅ ምርመራ ማድረግ፣ የጥቃት ሰለባዎችን በማነጋገር እማኝነት መቀበል፣ እንዲሁም የሕክምና ማስረጃዎች መመልከት ጠይቋል።
ዘገባው ላለፉት ሦስት ዓመታት በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት የተፈጸሙ እና ከመገናኛ ብዙኃን ዕይታ ተሰውረው የቆዩ ወሲባዊ ጥቃቶችን አደባባይ ያወጣ ነበር።
ቢቢሲ ለዘገባው ያነጋገራቸው ተመራማሪዎች እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎች የደኅንነት ስጋት ባለባቸው እና ወደ አካባቢው ጋዜጠኞች መግባት በማይችሉባቸው የክልሉ አካባቢዎች እያንዣበበ ያለውን የማኅበረሰብ ጤና ቀውስ በመጥቀስ አስጠንቅቀዋል።
የምርመራ ዘገባው በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት ቢቋጭም ግጭቶች በአማራ ክለል መቀጠላቸውን ያሳየ ነው።
የአማራ ክልል የትጥቅ ግጭት መንግሥት ለሁለት ዓመታት በነበረው የትግራይ ጦርነት የተሳተፉትን ኃይሎች ጨምሮ የክልል ልዩ ኃይሎችን ለመበተን ሲሞክር ነበር የፈነዳው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወሲባዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨመራቸውን ተናግረዋል።
ቢቢቢ በአማራ ክልል ስለተፈጠረው ቀውስ መረጃ ለማግኘት 4 በመቶ ከሆኑት የክልሉ 43 ጤና ጣቢያዎች እና የሕክምና ምንጮች መረጃዎችን ሰብስቧል።
በእነዚህ ተቋማት ከሐምሌ 18/2015 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ድረስ 2,697 ሰዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርት አድርገዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 45 በመቶ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው።
ከተጎጂዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በደረሰባቸው ጥቃት በአባላዘር በሽታ ሲያዙ፤ በርካቶች ደግሞ ለእርግዝና እና ለከባድ የሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርቡበትን ውንጀላዎች እና ክሶች በተደጋጋሚ ያስተባብላል።
ነገር ግን ቢቢሲ ለዚህ ሽልማት ላገኘበት ዘገባው የመከላከያ ሠራዊትን እንዲሁም የአማራ ክልል ባለሥልጣናትን አስተያየት ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ቢደያርግም ምላሽ አላገኘም።
ምንም እንኳ መንግሥት በአማራ ክልል በግጭቱ ምክንያት የወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ላይ ምርመራ ማድረጉን እና ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ቢገልጽም እስካሁን የተሰማ ነገር የለም።
የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዩኬ ሚዲያ አዋርድ በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ ዘገባዎችን በ11 ዘርፎች በማወዳደር ይሸልማል።
ቢቢሲ እንደ ሲኤንኤን፣ ዘ ጋርዲያን እና ዘታይምስ ካሉ መገናኛ ብዙኃን ጋር በተመሳሳይ ዘርፍ ታጭቶ ማሸነፍ ችሏል።
ሌሎች ለሽልማት የታጩ ዘገባዎችም በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች የደረሱ ወሲባዊ ጥቃቶች ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ፣ ዘገባዎቹ የተጠያቂነት አለመኖር እና የፍትሕ መስፈን አሳሳቢነትትን የሚያጎሉ ናቸው።
የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ረቡዕ ዕለት ለንደን በሚገኘው በብሪታኒያ የፊልም ኢንስቲትዩት የተካሄደ ሲሆን፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያጋለጡ ዘገባዎች የቀረቡበት እና ጋዜጠኞች የተገኙበት ነበር።














