የሩሲያ፣ ቻይና እና የኢራን መረጃ በርባሪዎች የአሜሪካ ምርጫ ላይ ኢላማ አድርገዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩሲያ፣ ቻይና እና የኢራን መረጃ በርባሪዎች ቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ላይ ኢላማ አድርገዋል ሲል ማይክሮሶፍት አስታወቀ።
ከሩሲያ፣ ቻይና እና ኢራን ጋር ቁርኝነት ያላቸው የኢንተርኔት መረጃ በርባሪዎች ከቀጣዩ የአሜሪካ ምርጫ ጋር በአንድም ሆነ በሌላ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ላይ ስለላ እያከናወኑ ነው ሲል ማይክሮሶፍት ገልጿል።
የፕሬዝደንት ትራምፕ እና የዲሞክራቶች እጩ ጆ ባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን አባላትም ኢላማ ተደርገዋል።
በ2016ቱ የአሜሪካ ምርጫ ወቅት የተሳተፉ የሩሲያ መረጃ በርባሪዎች አሁንም በዚህ ተግራባቸው ተሳታፊ መሆናቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል ማይክሮሶፍት። ማይክሮሶፍት ከሪፓብሊካን እና ዲሞክራት ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት ያላቸው 200 ድርጅቶች ኢላማ ተደርገዋል ብሏል።
ማይክሮሶፍት ጨምሮ እንዳለው ዚኮሪየም የተሰኘው የቻይና መረጃ መንታፊዎች ቡድን የጆ ባይደን የምርጫ ቅስቀሳ አካል የሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል።
ፎስፈረስ የተሰኘው የኢራን መረጃ በርባሪዎች ቡድን ደግሞ ኢላማቸው ያደረጉት የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ አባላት ላይ ነው። ማይክሮሶፍት እንዳለው ይህ ቡድን የዋይት ሃውስ ኃላፊዎችን እና የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ አባላት ላይ ግንቦት እና ሰኔ ወራት ላይ አካውንት ሰብሮ ለመግባት ያደረጉት ጥረት ሳይሳካላቸው ቀርቷል።
ማይክሮሶፍት የእነዚህ ሶስት ቡድኖች ዓላማ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም ይላል። ጉግል በተመሳሳይ ከወራት በፊት ተመሳሳይ የሆኑ የሳይበር ጥቃቶች ከቻይና እና ኢራን ስለመመዝገቡ አስታውቆ ነበር።
የትራምፕ እና የጆ ባይደን የምርጫ ቅስቀሳ ኃላፊዎች ይህ መሰል ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል ስለምናውቅ ቀድመን ተዘጋጅተናል ብለዋል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደህንነት ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት ክርቶፈር ክሬብስ የማይክሮሶፍት ማስጠንቀቂያ ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት ያሉትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ከቀናት በፊትም የትራምፕ አስተዳደር በምርጫው እጁን አስገብቷል የተባለ የሩሲያ ዜጋ ላይ ክስ መስርቷል።
ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የደህንነት አካላት ሶስቱ አገራት በምርጫው ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር እየሰሩ ነው ብለው ነበር።
እንደ የአሜሪካ የደህንነት ተቋማት ከሆነ ሩሲያ ጆ ባይደንን “ለማሳጣት” እየሰራች ሲሆን ቻይና እና ኢራን ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን እንዲያሸንፉ አይፈልጉም።












