ዩፎዎችን አይተናል የሚሉ የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር እየተበራከተ ነው

የፎቶው ባለመብት, AVAL AIR SYSTEMS COMMAND
ሰማይ ላይ በራሪ የሆኑ ምንነታቸው የማይታወቁ ዩፎዎችን አይተናል ብለው ሪፖርት ያደረጉ የአሜሪካ ወታደሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አንድ ሰነድ አመለከተ።
በአሜሪካ የከፍተኛ ምሥጢር ዶሴ ውስጥ የወጣ እና ለሕዝብ ይፋ የሆነ አንድ ሰነድ እንዳመለከተው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ዩፎዎችን አይተናል ያሉ የአሜሪካ የአየር እና የባሕር ኃይል ወታደሮች ቁጥር ወደ 500 አሻቅቧል።
በምህጻር ዩፎ (UFO) የሚባሉት እነዚህ ምንነታቸው በውል የማይታወቁ ባዕድ በራሪ አካላት፣ በተለያየ ጊዜ ሰዎች አይተናል የሚል ሪፖርት ስለሚያቀርቡ ምናልባት ከሰው ልጅ ሌላ ይህን ምድር የሚጋሩ ፍጡራን ሳይኖሩ አይቀርም የሚሉ መላምቶች ሲነገሩ ኖረዋል።
ሆሊውድም ይህን ጭብጥ በመያዝ በርካታ ፊልሞችን ለዕይታ አቅርቧል።
የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ ቀደም በራሪ ባዕድ ፍጡራን የሉም ብሎ መደምደም እንደማይፈልግ ገልጾ ነበር። ሆኖም በማስረጃ የተደረገ ነገር ለጊዜው አልተገኘም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሰማይ ላይ እነዚህን ባዕድ በራሪዎችን አየን የሚሉ ሪፖርቶች ከአሜሪካ ወታደሮች መቀበሉን አረጋግጧል።
የአሁኑ ለየት የሚያደርገው እነዚህን በራሪ አካለትን አይተናል የሚሉ ወታደሮች ቁጥር ማሻቀቡ ነው።
ይህ 500 አልፏል የተባለው አሐዝ በ20121 ከነበረው ቁጥር በ144 ከፍ ይላል።
ከእነዚህ ሪፖርቶች መካከል ግን በኋላ ላይ በተደረጉ ምርመራዎች አንዳንዶቹ ድሮኖች ስለመሆናቸው ተደርሶበታል። ሌሎች ደግሞ ተንሳፋፊ ግዙፍ ፊኛዎች (balloons) እንደሆኑ ታውቋል።
ሪፖርት ከተደረጉት ግን ወደ መቶ የሚጠጉት እንደሚጠረጠረው ባዕድ በራሪ ፍጡራን ይሁኑ ወይም ሌላ ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።
የአሜሪካ የበረራ ወታደሮች እነዚህን ባዕዳን ተመለከትናቸው የሚሉት ለወታደራዊ በረራዎች በተከለሉ የአሜሪካ የአየር ክልሎች ባለፉበት ጊዜ ነው።
ወታደሮች ባዕድ በራሪ ፍጡራንን አይተናል ካሏቸው ውስጥ በትንሹ 171 ሪፖርቶች ምርመራ ተደርጎባቸው ድምድሜ ላይ ለመድረስ በቂ መረጃ እንዳልተገኘ ይህ ምሥጢራዊ የነበረው ሰነድ ይፋ አድርጓል።
“ከእነዚህ አንዳንዶቹ ያልተለመደ የበረራ አቅጣጫ ስላላቸው ምን እንደሆኑ ለመለየት ተቸግረናል” ይላል ሪፖርቱ።
ባለፈው ወር የአሜሪካ መከላከያ መሥሪያ ቤት፣ ፔንታገን የደኅንነት እና መከላከያ ጉዳዮች አንድ ከፍተኛ መኮንን ለሚዲያ እንደተናገሩት እስከ አሁን ድረስ ዩፎ የምንላቸው ባዕድ ፍጡራን አሉ ለማለት የሚያበቃ አንዳችም አሳማኝ መረጃ አልተገኘም ብለዋል።
ይሁንና ማረጋገጫ አልተገኘም በሚል የዩፎዎች ጉዳይ ቸል የሚባል እንዳልሆነና ምርመራውና ጥናቱ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በአሜሪካ የአየር ክልል የሚያልፉ አብራሪዎች አንዳች ልዩ ፍጡራንን ሰማይ ላይ አይተናል፤ እመኑን ማለት ከጀመሩ ረዥም ዘመን ተቆጥሯል።












