ተጨማሪ ቋንቋዎችን በአዲስ አበባ ለማስተማር ያስቻለው ጥናት ግኝቶች ምን ነበሩ?

ተማሪዎች በአንድ መቀመጫ ላይ ተቀምጠው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በከተማዋ ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ኦሮምኛ ቋንቋ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ እንዲሰጥ ወስኗል።

በተመሳሳይ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በሆነው ኦሮምኛ እየተማሩ የነበሩ ተማሪዎችም አማርኛን በሁለተኛ ቋንቋነት ይማራሉ።

ከኢትዮጵያ ቋንቋዎች ውጭም አረብኛ እና ፈረንሳይኛ በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ እንዲካተቱ ተወስኗል።

የከተማ አስተዳደሩ ከዚህ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል በኮተቤ ዩኒቨርስቲ ምሁራን አማካይነት ጥናት ሲያስደርግ እንደነበር ተነግሯል።

የጥናት ቡድኑ አስተባባሪ የሆኑት ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር) በጥናቱ ከአገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ የውጭ ቋንቋዎች ፍላጎትም መዳሰሱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት ዮሴፍ (ዶ/ር)፣ በአዲስ አበባ በዋናነት ሁለት ዓይነት የትምህርት አተገባበር መኖሩን በቀዳሚነት ያነሳሉ።

በአፍሪካ ቋንቋዎች እና ሥነ ጽሑፍ ተመራማሪ የሆኑት ዮሴፍ (ዶ/ር) ቀዳሚው በስፋት በአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጥባቸው ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ሲሆን፣ ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ደግሞ በኦሮምኛ ቋንቋ የሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች መኖራቸውን አንስተዋል።

በዚህ ጥናት የብዝሃ ቋንቋ ባለቤት በሆነችው ኢትዮጵያ በትምህርት ቤቶች የሚኖረው አተገባበር፣ የሚኖሩ ፋይዳዎች እና ተግዳሮቶች በጥናቱ ተዳስሰዋል።

እንደ ምሑሩ ገለጻ የብዝሃ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆን፣ አንዱ የአንዱን ባህል በማወቅ ማኅበራዊ መስተጋብርን ማጠናከር፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማስፈን እንደሚቻል ያስረዳሉ።

አክለውም ከግጭት ይልቅ ሰላምን፣ ከመጠራጠር ይልቅ መተማመንን፣ ከእንግድነት ይልቅ ቤተሰባዊነት ማስፈንም እንደሚቻል የጥናት ቡድኑ አስተባባሪ አስረድተዋል።

ዮሴፍ (ዶ/ር) ተማሪዎች አፋቸውን ከፈቱበት ቋንቋ በተጨማሪ ሌላ ቋንቋ ሲማሩ “ተጨማሪ ዓለም እንደመተዋወቅ” ይላሉ።

ቋንቋን አለማወቅ በርካታ ውስንነቶችን እንደፈጥር የሚናገሩት ተመራማሪው፣ ለተማሪዎች ያለውን ጥቅም ሲያብራሩ “ሌላ ዕድልን አንደማደን፣ እንደማግኘት ምናልባት ውስን ከሆኑበት አካባቢያዊ፣ ቤተሰባዊ ሁኔታ አልፈው ሌላ አድማስን እንደ መለማመድ ነው” ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ተጨማሪ ቋንቋዎች እንዲካተቱ ማድረጉ አማርኛንም ሆነ ኦሮምኛን በሁለተኛ ቋነንቋነት ለሚማሩ “ተጨማሪ ዕድል እንደማግኘት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር) በጥናታቸው በቅድመ መደበኛ የሚማሩ ሕጻናት፣ ከአፍ መፍቻ ውጪ ሌላ ቋንቋ እንዲማሩ እንደማይመከር እና እነርሱም ይህንን በግልጽ አስቀምጠዋል።

ታዳጊዎች ሁለተኛ ቋንቋን መማር መጀመር ያለባቸው ወደ አንደኛ ክፍል ከተሸጋገሩ በኋላ (ከሰባት ዓመት ጀምሮ) መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ባይተዋር የሆነ ትውልድ እንዳይፈጠር

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያ ውስጥ በትምህርት ዓይነትነት የሚሰጡ ቋንቋዎችን በተመለከተ እንግሊዝኛን እንደ ዓለም አቀፋዊ መግባቢያነት፣ አማርኛ ደግሞ የፌደራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ በመሆኑ በሁሉም ክልሎች ይሰጣሉ።

ከእነዚህ ሁለት ቋንቋዎች በተጨማሪ ደግሞ ክልሎች የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ያስተምራሉ።

ይህ ግን አማርኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ያልሆነ ክልሎች ላይ ብቻ የሚሰራ ነው።

በዚህም መሰረት ከአማራ እና አዲስ አበባ ክልሎች በስተቀር ሌሎች ክልሎች በአጠቃላይ ሦስት ቋንቋዎችን ያስተምሩ ነበር።

ይህ የአሁኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ውሳኔ እንደ አብዛኞቹ ክልሎች ሁሉ አዲስ አበባም ቢያንስ ሦስት ቋንቋዎችን በትምህርትነት የምትሰጥ ከተማ ያደርጋታል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ አንድ ሰው ሁለት እና ከዚያ በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆን የብዝሃ ቋንቋ ባለቤት ይባላል።

አንድ ተማሪ ሁለት እና ከዚያ በላይ ቋንቋዎችን መናገር ሲችል ከሥነ ልቦናው፣ ከእድገቱ እንዲሁም ከትምህርት አቀባበል ጋር የተገናኙ ትሩፋቶች እንደሚኖሩት ተመራማሪው ያነሳሉ።

ተማሪዎች ከአንድ በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆኑ “ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን ማሻሻል፣ ብሔራዊ ማንነታቸውን ማጎልበት” ይችላሉ።

ከዚህም ባሻገር “ከግጭት ነጻ መሆን፣ ለሌላ ማኅበረሰብረ እንግዳ ከመሆን ይልቅ ቤተሰባዊነትን የመለማመድ እንዲሁም በሥነ ልቦና ረገድ እና በትምህርት ስኬታቸውም የተሻሉ እንደሚሆኑ” ጥናቶች እንደሚያሳዩ ዮሴፍ (ዶ/ር) ይጠቅሳሉ።

“ከስሜት፣ ከሥነ ልቦና ባለፈ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እውን ያደርጋል” የሚለው በጥናታቸው ውስጥ መታየቱን አክለው ገልጸዋል።

ተጨማሪ ቋንቋ የሚማሩ ተማሪዎች “አንዱ አንዱን የሚጠራጠርበት፣ እንግዳ የሚሆንበት ሳይሆን ቤተሰብ የሚሆንበት ነው።”

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ፈረንሳይኛ እና አረብኛ በሁለተኛ ደረጃ፣ ለዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል ተማሪዎች አማራጭ የቋንቋ ትምህርት ሆኖ እንዲቀጥል መወሰኑ ተመልክቷል።

ዮሴፍ ቤኮ በበኩላቸው በጥናታችን በርካታ ቋንቋዎችን መዳሰሳቸውን በማንሳት፣ የከተማ አስተዳደሩም በዚህ ውሳኔው ብቻ እንደማይቆም ያላቸውን እምነት ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በጥናታቸው ከእንግሊዝኛ በተጨማሪ አረብኛ የተመረጠበት ምክንያት ቅርበት፣ ተደራሽነት፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበረሰባዊ ተጠቃሚነት ከግምት ውስጥ ተገብቶ መሆኑ ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ ከአረብ አገራት ጋር ታሪካዊ እና ባህላዊ ግንኙነት እንዳላት፣ እንዲሁም ከእምነት እና ከቅርበት አንጻር ተመራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከአረብኛ በመቀጠል በሁለተኛነት ግን ቻይንኛ እንዲሁም ፈረንሳይኛን በጥናታቸው መመልከታቸው ዶ/ር ዮሴፍ ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ውስጥ አማርኛ፣ ኦሮምኛ በመቀጠል ደግሞ ትግርኛም የኅብረተሰቡ ምርጫ መሆኑን የጥናታቸው ግኝት ጠቁሟል።

በአዲስ አበባ ካለው አሰፋፈር አንጻር ሌሎች ቋንቋዎችን ለመማር ፍላጎት መኖሩን በጥናታቸው መመልከታቸውንም ገልፀዋል።

ታዳጊ ሕጻን በመማርያ ክፍል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሌሎች አገራት ልምድ ምን ያሳያል?

አፍሪካ በርካታ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሉባት አህጉር ናት።

በናይጄሪያ ከ500 በላይ ቋንቋዎች ይነገራሉ። ደቡብ አፍሪካ 11 የሥራ ቋንቋዎች አሏት። በኢትዮጵያም ቢትሆን ከ80 በላይ ቋንቋዎች ይነገራሉ።

እሲያዊቷ ሕንድ ደግሞ 23 ቋንቋዎችን የሥራ ቋንቋ አድርጋለች።

በሕንድ ሂንዱ እና እንግሊዝኛ በማንኛውም የአገሪቱ ግዛት በትምህርት ቤት የሚሰጡ ሲሆን፣ እድሜው ለትምህርት የደረሰ አንድ ታዳጊ ከእነዚህ ሁለት ቋንቋዎች በተጨማሪ በሚኖርበትን አካባቢ የሚነገር አንድ ቋንቋን መርጦ ይማራል።

ይህም በሕንድ ቀለም የቆጠረ ማንኛውም ዜጋ ሦስት ቋንቋዎችን እንዲናገር አስችሎታል።

ይህ በረከት ግን የአውሮፓ አገራትን ደጃፍን አልረገጠም። ቢሆንም ግን ይላሉ ተመራማሪው ዮሴፍ ቤኮ (ዶ/ር)፣ በትምህርት ሥርዓታቸው ውስጥ ከዚህ በተቃራኒው የብዝሃ ቋንቋ ሥርዓተ ትምህረትን አካትተዋል።

ይህንንም በማድረጋቸው አንድ ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ ከመፍጠራቸው በፊት አንድ ሥነ ልቦና ያለው ሕብረተሰብ ለመመስረት ችለዋል ሲሉ ያስረዳሉ።

በአውሮፓ አገራት በየትምህርት ቤቶቻቸው ከአንድ ቋንቋ ባሻገር ሌሎች ተጨማሪ ሁለት ቋንቋዎችን መማር እንደ ግዴታ ተቀምጦ እንዲማሩ እንደሚደረግ በጥናታቸው ወቅት ተመልክተዋል።

የአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት በትምህረት ቤቶቻቸው ውስጥ ሦስት ቋንቋ መማርን እንደ አነስተኛ መስፈርት እንደሚያዩት ይናገራሉ።

“በቋንቋ አንድ አካታች ማኅበረሰብ ይፈጠራል፤ ይህ ማኅበረሰብ ደግሞ በብዛት ኢኮኖሚያዊ ነው” የሚሉት ምሑሩ፣ ብዝሃ ቋንቋ በባህሪው ማኅበረሰቡን የማቀራረብ፣ ሰፊ ማኅበረሰብ የመፍጠር እና አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ሕብረተሰቦችን የማቀራረብ ባህሪ እንዳለው ጨምረው ያስረዳሉ።

እነዚህ አገራት ይህንን ብዝሃ ቋንቋን በመጠቀማቸው አንድ የአውሮፓ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የሚል መፍጠር መቻላቸውን በጥናታቸው ወቅት ተገንዝበዋል።

እነዚህ የአውሮፓ አገራት የትምህርትን አተገባባር ዕውን የሚያደርጉ በሚል ካስቀመጧቸው ስምንት አእማዶች መካከል ብዝሃ ቋንቋን በአንድ መስፈርትነት ማስቀመጣቸውንም ይናገራሉ።

በዚህም የተነሳ እነዚህ አገራት ድንበር ሳይገድባቸው የሚኖሩ፣ የሚገበያዩ እና የሚተባበሩ ሕዝቦችን ፈጥረዋል።

በአፍሪካም ቢሆን በተመሳሳይ ልምድ መታየቱን ዮሴፍ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።

በኢትዮጵያም ቢሆን ኦሮሚያ ክልል ከሚዋሰንባቸው ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል፣ ሲዳማ እና ጋምቤላ አካባቢዎች፣ አማራ ክልል ውስጥ ከሚኖሩ የአርጎባ እንዲሁም የኦሮሞ ማኅበረሰቦች ዘንድ እንዲሁም በደቡብ ክልል ከአንድ ቋንቋ በተጨማሪ በማስተማር በጎ ልምዶች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።

አዲስ አበባ የበርካታ ባህሎች፣ ብሔሮች መኖሪያ ሆኖ በአንድ ቋንቋ ተወስኖ መኖር እየመጡ ያሉ ገፊ ምክንያቶችን እንዴት መቋቋም ይቻላል ሲሉ ይጠይቃሉ።

እነዚህ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የሆኑ ገፊ ምክንያቶችን ለመቋቋም ተጨማሪ ቋንቋዎችን በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ማካተት አስፈላጊ መሆኑን በጥናቱ ማመልከታቸውን ዮሴፍ ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ የሚያድጉ ተማሪዎች ከሁለት በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ሆነው ለሚኖሩባት ዓለም እና አገር ባይተዋር ያልሆኑ ማደግ ይኖርባቸዋል ሲሉ ከሌላ አገር ልምድ ተነስተው ይመክራሉ።

ዮሴፍ (ዶ/ር) ከዚህ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ ውሳኔ በኋላ አተገባበር ላይ ጥንቃቄ አንደሚያስፈልግም ይመክራሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከዚህ ውሳኔው ቀጥሎ ተገቢውን የመምህራን ሥልጠና፣ የመማርያ መጻህፍት ዝግጅት ማድረግ ያስፈልገዋል።

አተገባበሩ ላይ በተለያዩ አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎችን ያማከለ እና ተጠቃሚ ባደረገ መልኩ፣ ነጻነት በተሞላበት ከሆነ ስኬታማ መሆን አንደሚቻል ያምናሉ።