የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኦሮምኛ እንደ ሁለተኛ ቋንቋ በትምህርት ቤቶች እንዲሰጥ ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, city addis ababa
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በከተማዋ ስር በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ኦሮምኛ ቋንቋ ከአማርኛ ጋር እንደ ሁለተኛ ቋንቋ እንዲሰጥ ውሳኔ አሳለፈ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከብዝሃ ቋንቋ ሥርዓተ ትምህርት ጋር በተያያዘ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አማርኛ ለሆኑ ተማሪዎች፣ ኦሮምኛ እንደ ተጨማሪ ሁለተኛ ቋንቋ እንዲሰጥ ሲል ውሳኔ አሳለፏል።
የከተማ አስተዳደሩ ዛሬ ሐሙስ ጥር 04/2015 ዓ.ም. ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት፣ በከተማዋ በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች አማርኛ ቋንቋን እንደተጨማሪ ቋንቋ እንዲሰጥ ሲል ወስኗል።
በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ከተማ ከኦሮሚያ ክልል ለኦሮምኛ ቋንቋ ማስተማርያነት በውሰት ተወስዶ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው ሥርዓተ ትምህርት በአዲሱ ሥርዐት ትምህርት እንደሚተካ በዚሁ ስብሰባ ላይ ተገልጿል።
በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ ተማሪዎች ከሰባተኛ ክፍል ጀምሮ ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በእንግሊዝኛ እንዲማሩ መወሰኑን በዚሁ ውሳኔ ላይ ተመልክቷል
ዛሬ ካቢኔው ባሳለፈው ውሳኔ ወቅት የብዝሃ ቋንቋ ሥርዓተ ትምህርትን አስመልክቶ በኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርስቲ ሲያስጠና መቆየቱን በማስታወስ፣ በጥናቱ ውጤት ላይ ውይይት ሲያካሂድ መቆየቱን ገልጿል።
ካቢኔው ፈረንሳይኛ እና አረብኛ በሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል ተማሪዎች አማራጭ የቋንቋ ትምህርት ሆኖ አንዲቀጥል መወሰኑ ተመልክቷል።
ከጥቂት ወራት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የኦሮሚያ ክልል መዝሙር እና ሰንደቅ ዓላማ ጋር በተያያዘ ውዝግብ እና ተቃውሞ መከሰቱ ይታወሳል።
በዚህም ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች ለእስር መዳረጋቸው እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ የንብረት ውድመት ማጋጠሙ ተዘግቦ ነበር።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከተከሰተው ውዝግብ ጋር በተያያዘ በርካታ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ተማሪዎች ለእስር የመዳረጋቸውን ባወጣው መግለጫ አሳውቆ ነበር።












