የኢራን የኒውክሌር ምሽጎችን ሊያወድም ይችላል የተባለው ብቸኛው የአሜሪካ ኃያል ቦምብ

ቢ-2 ስፒሪት የተሰኘችው ቦምፕ ጣይ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, US Air Force

የምስሉ መግለጫ, ዩኤስ ቢ-2 ስፒሪት አውሮፕላን ብቻ ጂቢዩ-57 ኤ/ቢ ቦምብም መሸከም እና መጣል እንዲችል ተደርጎ የተሠራ ነው

የኢራንን ከምድር በታች የተገነቡ የኒውክሌር ተቋማትን ለመምታት የሚችለው መሳሪያ አንድ ብቻ ነው።

ይህ እስካሁን ጥቅም ላይ ያልዋለው ቦምብ ደግሞ የሚገኘው በአሜሪካ እጅ ብቻ ነው። እስራኤልም ይህንን መሳሪያ እንድትጠቀም እስካሁን የአሜሪካን ይሁንታ አላገኘችም።

ይህ ጂቢዩ-57ኤ/ቢ (GBU-57A/B) የተባለው መሬት ሰርስሮ የሚገባ፣ የዓለማችን ትልቁ ኒውክሌር ያልሆነ "ምሽግ ደርማሽ" ቦምብ በአሜሪካ ባለቤትነት የተያዘ ነው።

ዒላማውን አነጣጥሮ መምታት የሚችል፣ 13,600 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ይህ ቦምብ የኢራን የምድር ውስጥ የኒውክሌር ኃይል ማበልጸጊያን የሆነውን ፎዶርን ደርምሶ ሊገባ ይችላል። ፎርዶ የኒውክሌር ተቋም ከተራሮች ሥር ከመሬት በታች የተገነባ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ማምረቻ ነው።

ከመሬት በታች ዘልቆ የሚያወድመው ይህ ኃያል ቦምብ ምንድን ነው? ያሉት ተግዳሮቶችስ ምንድን ናቸው? ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል?

የአሜሪካ መንግሥት እንደሚለው ጂቢዩ-57ኤ/ቢ (GBU-57A/B) "በጥልቀት የተቀበሩ እና የተጠናከሩ ጉድጓዶችን እና ዋሻዎችን ሰርስሮ በመግባት የማጥቃት አቅም ያለው መሳሪያ" ነው።

ስድስት ሜትሮች ርዝመት ያለው ይህ ቦምብ ከመፈንዳቱ በፊት በግምት 61 ሜትሮች ወደ ውስጥ ዘልቆ መግባት ይችላል ተብሎ ይታመናል።

ከዚህ በተጨማሪም ብዙ ቦምቦችን መበተን የሚችል ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ፍንዳታም ተጨማሪ ጥልቀትን እየሰረሰረ ይገባል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በቦይንግ የተሠራው ይህ ኤምኦፒ (MOP) ቦምብ ለውጊያ ጥቅም ላይ ውሎ አያውቅም። ነገር ግን በኒው ሜክሲኮ ግዛት የአሜሪካ ወታደራዊ መሳሪያዎች መሞከሪያ ላይ ተፈትሿል።

በአውሮፓውያኑ 2017 በአፍጋኒስታን ለጦርነት ጥቅም ላይ ከዋለው እና "የቦምቦች ሁሉ እናት" ተብሎ ከተንቆለጳጰሰው፣ 9,800 ኪሎ ግራም ከሚመዝነው ማሲቭ ኦርዲናንስ ኤር ብላስት (MOAB) ቦምብ የበለጠ ኃይለኛ ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም ብራድፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ፖል ሮጀርስ "የአሜሪካ አየር ኃይል ከኤምኦኤቢ (MOAB) ጋር ተመሳሳይ መጠን ያላቸውን የጦር መሳሪያዎችን ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።

ነገር ግን ፈንጂው በጣም ጠንካራ በሆነ የብረት መያዣ ውስጥ የታቀፈ ነው። ውጤቱም ጂቢዩ-57ኤ/ቢ (GBU-57A/B) ሆነ" ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ዩኤስ ቢ-2 ስፒሪት ወይንም ስቲልዝ ቦምበር ተብሎ የሚታወቀው አውሮፕላን ብቻ ኤምኦፒን ለመሸከም ፕሮግራም ተደርጓል።

ይህ አውሮፕላን ብዙ ጊዜ ቢ-2 እየተባለ የሚጠራው በኖርዝሮፕ ግሩማን የተመረተ ሲሆን፣ በአሜሪካ አየር ኃይል የጦር መሳሪያዎች ውስጥ ካሉት እጅግ የላቁ የጦር አውሮፕላኖች መካከል አንዱ ነው።

እንደ አምራቹ ገለጻ፣ ቢ-2 እስከ 18,000 ኪሎ ግራም ድረስ ሊሸከም ይችላል።

ሆኖም የአሜሪካ አየር ኃይል ቢ-2 አጠቃላይ ክብደታቸው 27,200 ኪሎ ግራም የሆነ ሁለት ጂቢዩ-57ኤ/ቢ ምሽግ አፍራሽ (GBU-57A/B) ቦምቦችን ተሸክሞ በተሳካ ሁኔታ መብረር እንደሚችል እንደሞከረ ተናግሯል።

ይህ ከባድ ቦምብ ተሸካሚ አውሮፕላን ነዳጅ ሳይሞላ ወደ 11,000 ኪሎ ሜትሮች መጓዝ የሚችል ሲሆን፣ በበረራ ላይ በ18,500 ኪሎ ሜትሮች ርቀት አንድ ጊዜ ነዳጅ መሙላት ይችላል።

እንደ ኖርዝሮፕ ግሩማን ከሆነ አውሮፕላኑ በሰዓታት ውስጥ በዓለም ላይ የትኛውም ስፍራ ለመድረስ ይችላል።

ፕሮፌሰር ሮጀርስ እንዳሉት ኤምኦፒ (MOP) እንደ ኢራን ዘመናዊ የአየር መከላከያ ሥርዓት ካለው ጠላት ጋር ጥቅም ላይ የሚውል ከሆነ፣ ቢ-2 ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ከሌሎች አውሮፕላኖች ጋር ሊጣመሩ ይችላሉ።

ለምሳሌ ኤፍ-22 ስቲልዝ ስትራይከር አውሮፕላኖች የጠላትን የመከላከል አቅም ለመገደብ፣ ከኋላ ደግሞ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በመከተል ጉዳቱን ለመገምገም እና ተጨማሪ ጥቃቶች ያስፈልግ እንደሆነ ለማወቅ ጥቅም ላይ ይውላሉ።

አሜሪካ የእነዚህ ኤምኦፒ (MOP) ቦምቦች ክምችት ያላት የተወሰነ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።

በአጠቃላይ "ምናልባትም 10 ወይንም ደግሞ 20 ቦምቦች ሊኖራቸው ይችላል" ብለዋል።

የአሜሪካ ወታደር ቦምብ ከባድ መኪና ላይ ሲጭን

የፎቶው ባለመብት, Whiteman Air Force Base

የምስሉ መግለጫ, ኤምኦፒ ከመፈንዳቱ በፊት 61 ሜትሮችን መሬትን ሰርስሮ የመግባት አቅም አለው

ኢራን ላይ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል?

ፎርዶ ከናታንዝ ቀጥሎ የኢራን ሁለተኛው የኒውክሌር ማበልፀጊያ ተቋም ነው።

ከቴህራን በስተደቡብ ምዕራብ 95 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በቆም ከተማ አቅራቢያ ካለ ተራራ በታች ተገንብቷል።

ግንባታው እአአ በ2006 አካባቢ እንደተጀመረ ይታመናል፣።

ተቋሙ በ2009 ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት ቴህራን መኖሩን በይፋ ተናግራለች።

ፎርዶ 80 ሜትሮች ጥልቀት ላይ በአፈር እና በድንጋይ ተሸፍኖ የተገነባ እንደሆነ የሚገመት ሲሆን፣ በተጨማሪ በኢራን እና በሩሲያ ከምድር ወደ አየር በሚወነጨፍ ሚሳዔል እንደሚጠበቅ ተነግሯል።

በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2023፣ ዓለም አቀፉ የአውቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) ወደ 83.7 በመቶ ጥራት ያላቸው የበለፀጉ የዩራኒየም ቅንጣቶችን በቦታው አግኝቷል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በኢራን ላይ የከፈቱት ጥቃት ዓላማ "ለእስራኤል የኅልውና ስጋት ናቸው" ያሏቸውን የሚሳዔል እና የኒውክሌር መርሃ ግብሯን ማስወገድ ነው ሲሉ ብለዋል።

እስራኤል ባለሥልጣናትም ፎርዶ የዚያ ዓላማ አካል እንደሆነ ተናግረዋል።

በአሜሪካ የእስራኤል አምባሳደር ይቼይል ሌይተር አርብ ዕለት ለፎክስ ኒውስ "ይህ አጠቃላይ ኦፕሬሽን ፎርዶን በማጥፋት መጠናቀቅ አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን እስራኤል ኤምኦፒ ቦምብን በራሷ የመጠቀም አቅም የላትም። ዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ያለ ቀጥተኛ ተሳትፎዋ እንድትጠቀም ልትፈቅድላት አትችልም ብለዋል ፕሮፌሰር ሮጀርስ።

"በእርግጥ እስራኤላውያን ራሳቸው እንዲያደርጉት አይፈቅዱም። እስራኤልም ደግሞ ይህን ያህል ሰርጎ መግባት የሚችል መሳሪያ የላትም።"

ዩናይትድ ስቴትስ ይህን ቦምብ የምትጠቀም ከሆነ በአብዛኛው የሚወሰነው የትራምፕ አስተዳደር ተሳትፎውን ለማሳደግ ባለው ፍላጎት ላይ ነው።

ፕሮፌሰር ሮጀርስ አክለውም "በእርግጥም ትራምፕ እስራኤላውያንን ለመርዳት ሙሉ በሙሉ በሚየሳዩት ድጋፍ ላይ ነው የሚወሰነው" ብለዋል።

በካናዳ በተካሄደው የቡድን ሰባት ስብሰባ ላይ ትራምፕ ዋሽንግተን ወታደራዊ ተሳትፎ ለማድረግ ምን እንደሚያስፈልጋት ተጠይቀው "ስለዚያ ማውራት አልፈልግም" ብለዋል።

አምባሳደር ሌይተር በቅርቡ ከኤቢሲ ዜና ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ አሜሪካ በፎርዶ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ልትሳተፍ እንደሆን ተጠይቀው፣ እስራኤል የመከላከያ እርዳታ ብቻ አሜሪካን እንደጠየቀች ተናግረዋል።

አክለውም "ፎርዶን ለመመከት የሚያስችለን በርካታ መጠባበቂያዎች አሉን" ብለዋል።

ኢራን ሁልጊዜ የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ሙሉ በሙሉ ለሰላማዊ አገልግሎት እንደሆነ ስትገልጽ የቆየች ሲሆን፣ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ለማምረት ፍላጎት እንደሌላት ትናገራለች።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት የዓለም አቀፉ የኒውክሌር ተቆጣጣሪ ድርጅት ኢራንን ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የገባችውን ግዴታ መጣሷን በይፋ አውጇል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በቡድን ሰባት አገራት ስብሰባ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'ማርሽ ቀያሪው'

በቅርቡ እስራኤል በኢራን የኒውክሌር ተቋማት ላይ የአየር ጥቃት ብትፈጽምም፣ ፕሮፌሰር ሮጀርስ "በማንኛውም መንገድ እስራኤል ከመሬት በታች በጥልቀት የተቀበሩትን የኢራን የኒውክሌር ተቋማትን ማውደም ችላለች" የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ።

"በመሠረቱ ራሳቸው ማድረግ የማይችሉትን ለማድረግ እንደ ኤምኦፒ (MOP) ያለ ነገር ይፈልጋሉ።"

በአሜሪካ በሚገኘው የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ማኅበር የፖሊሲ ዳይሬክተር የሆኑት ኬልሲ ዳቬንፖርት እንዳሉት "ፎርዶ በሥራ ላይ እስካለ ድረስ ኢራን አሁንም በቅርብ ጊዜ ዩራኒየም ልታበለጽግ ትችላለች። ቴህራን በዚህ ተቋም ኒውክሌር ወደ ጦር መሳሪያ ደረጃ የማበልጸግ ወይም ዩራኒየም ወደ ማይታወቅ ቦታ የመውሰድ ዕድል አላት" ብለዋል።

ነገር ግን ምንም እንኳን ኤምኦፒ ጥቅም ላይ ቢውልም የኢራን ጣቢያዎች ጥልቀት እና ጥበቃ ስለማይታወቅ ስኬታማ መሆኑን ማረጋገጥ አይቻልም ይላሉ ፕሮፌሰር ሮጀርስ።

"ይህ ልዩ መሣሪያ በአሁኑ ጊዜ ካሉት ከማንኛውም መሳሪያዎች ይልቅ የኢራንን የኒውክሌር አቅም የማውደም ምርጥ ዕድል አለው። ነገር ግን ይህንን ማድረግ ይችል እንደሆነ ገና አልታወቀም።"