በካቶሊክ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ተብሎ ይሰየማል የተባለው እና ጉቦ ባለመቀበሉ የተገደለው የጉምሩክ ሠራተኛ

የፎቶው ባለመብት, AP
በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2007 ታፍኖ ከተወሰደ ከሁለት ቀናት በኋላ ተደብድቦ በደም የተነከረው የፍሎሪበርት ብዋና ቹይ ቢን ኮሲቲ አስከሬን በምሥራቅ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጎማ ከተማ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውጪ ተጥሎ ተገኘ።
አዲስ ምሩቅ የሆነው የ26 ዓመቱ እና አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የጉምሩክ ሠራተኛ ሆኖ ሥራ ከጀመረ ገና ሦስት ወር ብቻ ነበር።
ሥራውን የጀመረው ደግሞ ጉቦ ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆን እና በተለመደው ቅንነት ነበር።
ከጎረቤት ሩዋንዳ የተበላሸ እና ለምግብነት ቢውል ሊመርዝ የሚችል ሩዝ በድብቅ ማጓጓዝ ከሚፈልጉ ሰዎች በተቃራኒ ቆመ፤ ሩዙ ወደ ኮንጎ አይገባም ብሎ አሻፈረኝ አለ።
ከግድያው ጋር በተያያዘ የታሰረ ማንም የለም።
አባ ፍራንቸስኮ ቴደስቺ ኮሲቲ ከካቶሊክ ቅዱሳን መካከል አንዱ እንዲሆን ዘመቻ ሲያካሂዱ የነበሩ ሲሆን፣ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተፈፀመው "የማፍያ ዓይነት" ግድያ ሙስናን ለሚቃወሙ ለማንም ማስጠንቀቂያ ለመስጠት ታስቦ ነው።
በተለይ ጠብመንጃ በሕግ የበላይነት ላይ ሥልጣን በሚይዝበት የዓለማችን ክፍል መልዕክቱ ግልጽ ነው።
ጎማ የሰሜን ኪቩ ግዛት ዋና ከተማ ነች፤ ለዓለም የሞባይል ስልክ ምርት ወሳኝ በሆነ ማዕድን የበለፀገች ናት፤ እንዲሁም አማፂያን እና ሚሊሻ ቡድኖች በብዛት ይገኙባታል።
አባ ቴደስቺ ግን ማስጠንቀቂያው ሙሉ በሙሉ የከሸፈው በኮሲቲ የፍቅር እና የፍትሕ ትሩፋት ምክንያት እንደሆነ ያምናሉ፤ በአጭር ሕይወቱ ያሳየው ደግነት ዛሬም ይኖራል።
ድርጊቱ ሙስና የተለመደ በሆነበት ቦታ፣ ጠንካራ እምነቱን እንደ ጋሻ ተጠቅሟል።
በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በተደጋጋሚ የሚቀርብለትን መደለያ ለመቋቋም የሚያስችል ጠንካራም አድርጎታል።
አባል በነበሩበት የካቶሊክ ሳንትኤጊዲዮ ማኅበረሰብ መሠረት፣ ኮሲቲ በመጀመሪያ 1 ሺህ ዶላር ከዚያም 2 ሺህ ዶላር "እና ከዚህም በላይ" ተሰጥቷታል፤ ግን ያለማቋረጥ አሻፈረኝ ብሏል።
የሳንትኤጊዲዮ ማኅበረሰብ "ሁሉም እንደሚያደርገው አይቶ እንዳላየ እንዲሆን እና ክፍያውን እንዲወስድ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ሳይቀር የስልክ ጥሪ ደርሶት ነበር" ብሏል።
ባለፈው ዓመት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሰማዕት ብላ አውጃለች፤ ይህም የቅድስና አንዱ ደረጃ ሲሆን የእርሱ ሞት ክርስቲያናዊ እሴቶቹን ለገንዘብ ለመሠዋት ፈቃደኛ ባለመሆኑ የተነሳ እንደሆነ ተሰምቷታል።
በካቶሊክ ወግ ውስጥ አንድ ቅዱስ እንደ የክርስትና ሕይወት ሞዴል ሆኖ የሚገለግል ሲሆን፣ ልዩ የብርታት ተግባሩ እንደ የእምነት ጀግና ያስቆጥረዋል።
ኮሲቲ ባለፈው ወር በሮም በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ባርኮትን ተቀብሏል፤ ይህ ማለት አንድ ጊዜ በስሙ ጸልየው ተአምር የሚከናወን ከሆነ በኋላ ቅዱስ ተብሎ ይሰየማል።
እስካሁን ድረስ ይህ በአስደናቂ ሁኔታ ፈጣን ጉዞ ነው፣ ምክንያቱም በቤተክርስቲያኒቱ ቀኖና መሠረት፣ ወደ ቅድስና የሚደረገው ሂደት፣ አንዳንድ ጊዜ አሥርተ ዓመታት ወይም ክፍለ ዘመናት ሊወስድ ይችላል።
ቤተክርስቲያኒቱ አንድ ሰው ለእምነቱ ሲል እንደሞተ ከወሰነች ግን ሂደቱ ይፋጠናል።
እአአ በ1981 በጎማ የተወለደው ኮሲቲ ለሦስት እህቶቹ እና ለስምንት ወንድሞቹ ትልቁ ነበር።
በሳንትኤጊዲዮ የፃፈው የሕይወት ታሪኩ "ከጥሩ ቤተሰብ" እንደተገኘ ይገልፃል። አባቱ የባንክ ባለሙያ፣ እናቱ ደግሞ የድንበር ጠባቂ ፖሊስ ነበሩ።
እናቱ ገርትሩድ ካማራ ንታዊሃ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድጋፍ ለሚደረግለት ሬድዮ ኦካፒ ባለፈው ወር ለልጇ ሰማዕትነት በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ ለመገኘት ወደ ሮም ከመጓዟ በፊት ስለልጇ ተናግራ ነበር።
"ፍሎሪበርት ብዋና ቹይ ከተወለደ ጀምሮ አስተዋይ እና አንደበተ ርቱዕ ልጅ ነበር። እኛን፣ ወላጆቹን የሚያከብር ጨዋ ልጅ ነበር። በእርሱ ውስጥ ብሩህ የወደፊት ተስፋ አይቻለሁ። የሚያገባ ልጆች የሚወልድ እንዲሆን እጠብቅ ነበር" ብላለች።

የፎቶው ባለመብት, AP
በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የመኖር ተግዳሮቶች ቢኖሩም ኮሲቲ ሁልጊዜ ስለ ዓለም ለማወቅ ጉጉት እንዲሁም በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ነበረው እና በዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት አጥንቷል።
ተማሪ እያለ እአአ በ2001 በሩዋንዳ በተካሄደ የቀጣናው የተማሪዎች ኮንፈረንስ ላይ በተሳተፈበት ወቅት ነበር የሕይወቱን አቅጣጫ የተለወጠው።
በግሬት ሌክስ አካባቢ ሰላምን ስለማግኘት፣ በሰላም ለመኖር በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመወያየት ሰዎች በተሰበሰቡበት አንድ ጣሊያናዊ ቄስ ንግግር አደረጉ።
ቄሱ ንግግር ያደረጉት ለማኅበራዊ አገልግሎት ቁርጠኛ የሆነው እና የምእመናን እና የሃይማኖት አባቶች ንቅናቄ የሆነው የሳንትኤጊዲዮ ማኀበረሰብን በመወከል ነው፤ ካህኑ ተማሪዎቹ የመጋቢነት ተልዕኮ እንዲቀበሉ እያበረታቷቸው ነበር።
አባ ቴደስቺ በደቡባዊ ሩዋንዳ የዩንቨርሲቲ ከተማ ቡታሬ በሚገኘው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ንግግራቸውን ብዙም ሳይጨርሱ ነበር ኮሲቲ ወደ እርሳቸው የቀረበው።
"ይህ ንግግር ፍሎሪበርትን እና ከጎማ የመጡትን ሌሎች ጓደኞቹን በጣም ነክቷል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"በጎማ ውስጥ የሳንትኤጊዲዮን ማኅበረሰብ መፍጠር ፈልጎ ነበር። [እሱ] በዙሪያው ያየውን የማይሠራውን ለመለወጥ ፍላጎት ያለው፣ ለዓለም ጠቃሚ የመሆን ፍላጎት ያለው፣ በደስታ የተሞላ ወጣት ነበር።"
ኮሲቲ ተልዕኮውን ወሰደ። በተለይም ጥረቱ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በመርዳት ላይ ያተኮረ ነበር ብለዋል አባ ቴደስቺ።
በጎማ ዙሪያ ያለው ክልል ለበርካታ አስርት ዓመታት በዘለቀው ግጭት የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ በአመጽ መሃል ላይ የሚገኝ አማፂ ቡድን ከተማዋን እና በዙሪያዋ ያሉትን ግዛቶች ተቆጣጠሯል።
በተከታታይ ጉዳቶች ያልሻረ ጠባሳ ባላቸው ሕጻናት ዕጣ ፈንታ "በጣም የተጎዳው" ኮሲቲ፣ የሴንት ኤጊዲዮን "የሰላም ትምህርት ቤቶች" አንዱን አቋቋመ፤ ምግብ እና ሌሎች ልጆችን ትምህርት ለማግኘት የሚረዱ ድጋፎችን ያቀርባል።
ዛሬ የጎማ ሰላም ትምህርት ቤት ለእርሱ ክብር ተሰይሞ መደበኛ ትምህርት ቤት ሆኗል።
ነገር ግን እአአ በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወጣቱ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ፣ ብዙውን ጊዜ የጎዳና ተዳዳሪዎችን በገንዘብ፣ በትምህርት ቤት ክፍያ ወይም በምግብ ሁሉም የዕለት ጉርሱን ለማግኘት በሚታገልበት ከተማ ውስጥ ራሳቸውን እንዲችሉ ይረዳቸው ነበር።
"እኔን የገረመኝ ነገር ቢኖር"" ይላሉ አባ ፍሎሪበርት "የሌሎችን ሕይወት በቁም ነገር የሚወስድ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የድህነት ምንጭ ምን እንደሆነ ለመረዳት ራሱን ብዙ ጥያቄዎችን ይጠይቅ ነበር። እነዚህን ችግሮች ለመጋፈጥ ማውራት ይወድ ነበር።"

የፎቶው ባለመብት, Sant'Egidio
የኮሲቲ በጎ ሥራ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ድንበር አልፏል። ከጎማ በስተምሥራቅ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ ውስጥ የሳንትኤጊዲዮ ባልደረባ የሆነው በርናርድ ሙሳና ሴጋታጋራም ያስታውሰዋል።
"አፍሪካን መለወጥ እና ሰላምን መገንባት የጋራ ህልማችን ነበር። እያደገ ያለውን የወዳጅነት መረብ ስናይ በውጥረት ውስጥ መኖር ጓደኝነታችንን የበለጠ ልዩ የሚያደርገው ይመስለኛል" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
እአአ በ2006 ከተመረቀ በኋላ ኮሲቲ በሩዋንዳ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ድንበር በሚያዝያ 2007 ከፍተኛ ቦታ ከመያዙ በፊት በዋና ከተማዋ ኪንሻሳ የጉምሩክ ባለሥልጣን ውስጥ ሥልጠና ጀመረ።
የአደገኛው ሩዝ ውዝግብ ወደ አራት ወይም አምስት ቶን የሚጠጋ ዕቃን ያካተተ ነው። እሱ ስለ ሩዝ ደኅንነት ስጋት ስላደረበት ምርመራ አድርጎ ከዚያም እንዲወድም አዘዘ።
"መጀመሪያ ላይ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች አባበሉት፤ በኋላ ላይ ደግሞ አስፈራሩት። እና ፍሎሪበርት ሁልጊዜ እምቢ ይላቸው ነበር" ብለዋል አባ ቴደስቺ።
"በክርስትና መርሆቹ መሠረት እምቢ አለ። በአንድ ወቅት በጎማ ውስጥ የምትሠራ እና ጓደኛው የነበረች መነኩሲት ዶክተርን ስለሩዙ ጠይቋታል፤ ስለዚህ ይህ ሩዝ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ሊያመጣ የሚችለውን አደጋ በትክክል ሊረዳው ይችላል።
"ይህ ነው 'ስለዚህ እኔ ክርስቲያን እንደመሆኔ መጠን ገንዘብ መቀበል አልችልም ወይም እነዚህ ሰዎች በሙስና ምክንያት በዚህ የተመረዘ ምግብ ምክንያት ሊሞቱ ይችላሉ' ብሎ እንዲያስብ ያደረገው።"
ለካህኑ "ለወንጌል ታማኝነቱን፣ ለጎረቤት ያለውን ፍቅር ክርስቲያናዊ እሴቶችን" ያሳየ ነው።
በጎማ ዩኒቨርሲቲ ከኮሲቲ ጋር የተማሩት እና በከተማዋ ከሚገኙት የሳንትኤጊዲዮ መሪዎች አንዱ የነበሩት ጠበቃ ዣን ዣክ ባኪናሄ በዚህ ይስማማሉ።
ለሩዋንዳ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን የቴሌቪዥን ጣቢያ ጓደኛው "የሰላምን ወንጌል በጥልቅ ይከታተል ነበር… [ይህም] ያንን የሙስና ተግባር በፍፁም እንዲቃወም ረድቶታል" ሲል ተናግሯል።
ግን በመጨረሻ ይህ አሻፈረኝ ባይነቱ ወደ ሞት አመራው።
"[ኮንትሮባንዲስቶቹ] መልዕክት ለመላክ ፈልገዋል… የማፊያ ዓይነት ማስጠንቀቂያ" ብለዋል አባ ቴደስቺ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በወቅቱ አንዳንድ የጉምሩክ ባለሥልጣናትን ሊያስፈራቸው እንደሚችል አምኗል ነገር ግን "[ሰዎችን] ፍሎሪበርት የሰጠንን እነዚህን የፍቅር እና የፍትሕ ምስክርነቶች እንዲረሱ ለማድረግ አልተሳካም" ብሏል።
ሟቹ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በእአአ የካቲት 2023 ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን ሲጎበኙ በኪንሻሳ ዋና ስታዲየም ወጣቶችን ባነጋገሩበት ወቅት የኮሲቲን አርአያ እንዲከተሉ አሳስበል።
"እንደ እናንተ ሁሉ ወጣት የነበረው ፍሎሪበርት ብዋና ቹይ… በ26 ዓመቱ በጎማ ውስጥ በሰዎች ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የተበላሹ ምግቦች እንዲገቡ ባለመፍቀዱ ተገድሏል" ብለዋል።
"ክርስቲያን ስለሆነ ይጸልይ ነበር፤ ስለሌሎች ያስባል እና ታማኝ መሆንን መረጧል፤ ቆሻሻ የሆነውን ሙስና ተጸይፏል፤ አንድ ሰው ጉቦ ቢሰጣችሁ፣ ውለታ እና ብዙ ገንዘብ ለመስጠት ቃል ቢገባላችሁ ለዚህ ወጥመድ አትሸነፉ። አትታለሉ፤ ወደ ክፉት አትግቡ !" በማለት ተናግረዋል።
በሰኔ ወር የቅዱስ ጳውሎስ ጳጳስ ባዚሊካ የሰማዕትነት ሥነ ሥርዓትን የመሩት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ፣ ለዲሞክራቲክ ኮንጎ ወጣቶች የወደፊት ተስፋ ሰጪ እንደሚሆን ይስማማሉ።
"ይህ አፍሪካዊ ሰማዕት በወጣቶች በበለጸገች አህጉር ውስጥ፣ ወጣቶች እንዴት ሰላም መፍጠር እንደሚችሉ ያሳያል" ብለዋል።
አሁን ሰማዕቱ ከስሙ በፊት "የተባረከ" የሚል ማዕረግ በማግኘቱ፣ በቤተክርስቲያን ውስጥ በደስታ የተሞሉ የኮንጎ ምዕመናን ባንዲራቸውን እያውለበለቡ እልልታቸውን አቅልጠውታል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ "በኪቩ፣ በኮንጎ እና በመላው አፍሪካ በጉጉት የሚጠበቀው ሰላም በቅርቡ፤ በድንግል ማሪያም እና በብፁዕ ፍሎሪበርት አማላጅነት ይምጣ" ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ ሁለት የጋራ የሰላም ስምምነቶች ተፈርመው ባሉባት ጎማ ሰላም ቢወርድ በእርግጥም ቅዱስ የሚለው ስም የሚገባው ተአምር ነው፤ እንዲሁም ለአካባቢው ሁሉ ተስፋ ይሰጣል።















