አሜሪካ ዓይኗን በጣለችበት የኮንጎ የማዕድን ማውጫ ውስጥ ምን እየተካሄደ ነው?

በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘው ኤም23 አማፂ ቡድን በቁጥጥሩ ስር የሚገኘውን ለዓለም የሞባይል ስልክ ምርት ወሳኝ ግብዓት የሚመረትበት የማዕድን ማውጫን ቢሲሲ እንዲጎበኝ ፈቅዷል።
በዚህ ግዙፍ ማዕድን ማውጫ አንድም ሰው ሥራ ፈትቶ አይታይም።
በጉድጓድ እና ዋሻዎች የተሞላውን መልክዓ ምድር በሺህዎች የሚቆጠሩ ማዕድን ቆፋሪዎች ሞልተውታል።
አንዳንዶች ከመሬት ስር ገብተው በአካፋ ማዕድኑን እየዛቁ ያወጣሉ። ሌሎቹ ደግሞ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችን ለመሥራት ጥቅም ላይ የሚውለውን ኮልተን የተባለውን ድንጋይ በጆንያ ሞልተው በትከሻቸው ተሸክመው ይታያሉ።
በመቀጠልም ሌሎች በእጃቸው እና በአካፋ አጠባ እና ልየታ ወደ ሚያደርጉበት የፍተሻ ስፍራ ይወስዳሉ።
አማፂያኑ ካለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ የተቆጣጠሩት የሩባያ ማዕድን ማውጫ ኃላፊ የሆኑት ፓትሪክ ሙሳፊሪ "እዚህ በየቀኑ የሚሠሩ10 ሺህ እና ከዚያ በላይ ሰዎች አሉ" ይላሉ።
በአካባቢው ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው። ላለመውደቅ የቢቢሲ ቡድን ምርኩዞችን መጠቀም እንዲሁም የሙሳፋሪ እገዛ አስፈልጎታል።
ሆኖም ለአብዛኞቹ ሰዎች ይህ የሚያውቁት ብቸኛ ሕይወታቸው ነው። ከባድ ወይም አደገኛ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አነስተኛም ቢሆን ኑሮን ለመመሥረት አስችሏቸዋል።
"በማዕድን ጉድጓዱ ውስጥ በጥልቀት ስንገባ ሙቀቱ በጣም ከፍተኛ ነው፤ ማዕድናቱን መቆፈርም በጣም ከባድ ነው። በተጨማሪም ሌሎች ጎጂ ጋዞች ይኖራሉ" ያለው የማዕድን ቁፋሮ ሠራተኛ የሆነው ፒተር ኦሲአሲ ነው።
"አንዳንዴ ሥራችንን እንድንቀጥል ቀዝቃዛ አየር በውስጥ እንዲደርሰን ይደረጋል" ይላል።
ነገር ግን ወጣቱ ከአምስት ዓመት በፊት ማዕድን የማውጣት ሥራ ከጀመረ በኋላ ጋብቻ ለመመሥረት የጥሎሽ ገንዘብ መቆጠብ እንደቻለ እና አሁን ባለ ትዳር እና የልጆች አባት እንደሆነም ተናግሯል።
"ሕይወቴ በእውነት ተለውጧል። ማዕድን መቆፈሬ አግዞኛል።"
በወርቅ የተለበጠው መሬት ከጎማ ከተማ 60 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በሰሜን ኪቩ ግዛት በማሳሲ ተራራማ ስፍራ ይገኛል።
አካባቢው 15 በመቶ የዓለም የኮልተንን አቅርቦት እና ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አጠቃላይ ክምችት ግማሹን የሚይዝ ነው።
የዓለም ባለሀብቶች በአካባቢው ዓይናቸውን ቢጡሉ አያስገርምም።
ባለፉት ዓመታት የአገሪቱን ጦር ጨምሮ በቁጥጥራቸው ስር ላደረጉት የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ግዙፍ ሃብት አስገኝቷል።

በአካባቢው ለሦስት አስርት ዓመታት የዘለቀውን አለመረጋጋት ለመቋጨት የሰላም ሂደት አካል የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት በዋሽንግተን አሸማጋይነት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ መካከል ከተደረሰ ከቀናት በኋላ ከሩባያ ከተማ 10 ኪ.ሜ. የሚርቀውን ማዕድን ማውጫ የቢቢሲ ዘጋቢዎች ተመልክተዋል።
በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያለው የግጭት ስረ መሠረት ውስብስብ ነው።
የጎሳ መልክ ያለው ሲሆን፣ አብዛኞቹ አማፂዎች ከሩዋንዳ የ1994ቱ የዘር ማጥፋት ጋር የሚያያዙ እና ኪጋሊ በኮንጎ ይደገፋሉ ብላ የምታምነው የሁቱ ታጣቂ ኃይልን ጨምሮ ሌሎችም በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ።
ባለፈው ሰኔ መጨረሻ በዋሽንግተን ሁለቱም ወገኖች ትጥቅ እንዲፈቱ እና ይደግፏቸዋል ከሚባሉት ወኪሎቻቸው ጋር ግንኙነታቸውን እንዲያቋርጡ ተስማምተዋል። ምንም እንኳ ወኪሎች እንደሌላቸው ቢያስተባብሉም።
ኤም23 የስምምነቱ አባል አልነበረም። በአብዛኛው በቱትሲ ጎሳ የሚመራው ቡድኑ የምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አብዛኛውን ክፍል ይቆጣጠራል። ካለፈው ጥር ጀምሮ ደግሞ ጎማ፣ ቡካቩ ከተማን እና ሁለት አየር ማረፊያዎችን ይዟል።
ሩዋንዳ የመንግሥታቱ ድርጅትን ጨምሮ በአብዛኞቹ ኤም23ን ትደግፋለች በሚል ትከሰሳለች። ነገር ግን የሩዋንዳ ሹማምንት ወታደራዊም ይሁን የገንዘብ ድጋፍ አድርገን አናውቅም ሲሉ ክሱን ያስተባብላሉ።
በተኩስ አቁም ስምምነቱ ምንም እንኳ እስካሁን የተገለፀ ነገር ባይኖርም የአሜሪካ ተሳትፎ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የማዕድን ሃብት ለማግኘት መንጠላጠያ ተደርጎ ታይቷል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፊርማ ሥነ ሥርዓቱ አስቀድሞ "[ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ለዩናይትድ ስቴት በርካታ የማዕድን መብት እያገኘን ነው" ብለዋል።

ቢቢሲ ለ45 ደቂቃ የቆየ አጭር የጉብኝት ፈቃድ ያገኘ ሲሆን፤ በቆይታው የመሪ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ፍንጭ አላየም።
በኤም23 የተሾሙት ተቆጣጣሪ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ማዕድን ማውጫው እንዴት እንደተደራጀ እና አማፂ ቡድኑ ማዕድን አውጪዎች ያለ ፍርሃት ሥራቸውን እንዲሠሩ በአካባቢው መረጋጋት እንዴት እንደፈጠሩ አብራርተዋል። መሳሪያ የታጠቀ ሰው ወደ ማውጫ ጣቢያው እንደማይገባም ጠቁመዋል።
"እስካሁን በርካታ ችግሮችን ፈትተናል" ይላሉ።
"የደኅንነት ጉዳዮችን የሚቆጣጠር እና በማዕድን አውጪዎች መካከል ግጭት ሲፈጠር የሚፈታ ክፍል አሁን አለን። አንድ ዋሻ አደጋ ላይ የሚሆን ከሆነ አደጋን ለማስቀረት ሠራተኞች እንዲወጡ ይነገራቸዋል።
"ከተለያየ ቡድኖች ሰዎች ማዕድን ለማውጣት፤ ሌሎች ደግሞ ማዕድኖችን ለመግዛት በየቀኑ ይመጣሉ። እና አሁን በጎማ ሰዎች የገዙትን መልሰው የሚሸጡበት ትልቅ ገበያ አለን" ብለዋል።

ባለፈው ታኅሣሥ የመንግሥታቱ ድርጅት ባለሙያዎች ኤም23 እንዴት በየወሩ ከኮልተን ታክስ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠር ዶላር ገቢ እንደሚያገኝ የሚዘረዝር ሪፖርት አውጥተዋል።
አብዛኛው ማዕድን የሚላከው በቀጥታ ወደ ሩዋንዳ ነው ቢባልም ኤም23 እና ኪጋሊ ግን ያስተባብላሉ።
ሥራ ለመሥራት ፈቃድ በገዙ ባልደረቦቹ የተከበበው ኦሲአሲ ሁኔታዎች ከዚህ የተሻሉ እንደነበር ይስማማል።
"ሥራው በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው። ምክንያቱም ቢያንስ የሚታይ ሰላም አለ። ነገር ግን ክፍያው በጣም ዝቅተኛ ነው። ትንሽ ገንዘብ ነው የሚከፈለን" ይላል።
የትራምፕ ሁለተኛ የሥራ ዘመን ኤም23 አብዛኛውን ሰሜን እና ደቡብ ኪቩ ግዛቶች መያዝ እና የኮንጎ ጦር ማፈግፈግ ካደረገበት ጊዜ ጋር የተገጣጠመ ነው።
የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት አክራም ቱሚሲፉ ለወራት ወታደራዊ ድጋፍ ስትሻ የቆየችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአሜሪካን እርዳታ ለማግኘት የከበሩ የማዕድን ክምችቷን መሳቢያ አድርጋ ተጠቅማለች ይላሉ።
ጊዜያዊ የሰላም ስምምነት በተደረሰበት በዚህ ወቅት የኮንጎ ባለሥልጣናት ትልቁ ተስፋ በቻይና ኩባንያዎች በበላይነት በተያዘው የማዕድን ዘርፍ የአሜሪካ ግዙፍ ኩባንያዎች ሃብታቸውን ፈሰስ ያደርጋሉ የሚል ነው ሲሉም ያክላሉ።
የአሜሪካ ባለሃብቶች በሩባያ ማዕድን ላይ ገንዘባቸውን ለማፍሰስ እያማተሩ እንደሆነ እየተዘገበ ነው።
የሩባያ ተቆጣጣሪ መዋዕለ ነዋይ ለመቀበል ፈቃደኛ እንደሆኑ ጠቁመው፤ የአካባቢውን ምጣኔ ሃብት በሥራ፣ ትምህርት ቤት እና ሆስፒታል ለማሳደግ የሚንቀሳቀሱት ብቻ ይፈቀድላቸዋል ብለዋል።
"ማንኛውም የውጭ አልሚ እዚህ መምጣት ይችላል። ለሕዝባችን ልማት ብለው እስከመጡ እና የማዕድን ቆፋሪዎችን ውሎ አበል እስከጨመሩ ድረስ" ሲሉ ሙሳፊሪ ተናግረዋል።
ምንም እንኳ አገሪቱ ግዙፍ የተፈጥሮ ሃብት ቢኖራትም፤ አብዛኞቹ የማዕድን ማውጫ አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች አነስተኛ መሠረተ ልማት አላቸው። ሃብቱ ወደሚዛቅበት ማዕድን ማውጫዎች የሚወስዱ መንገዶች እንኳ ዝቅተኛ ናቸው።
የፖለቲካ ተንታኙ የአሜሪካ ባለሃብቶች ወደ አካባቢው መምጣት "ግጭት እንዳይቀሳቀስ እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች እንዳያንሰራሩ ማስጠንቀቂያ" ይሆናል የሚል እምነት አላቸው።
ነገር ግን ምሥራቁን ክፍል በቁጥጥር ስር ያዋለው ኤም23 እያለ እንዴት እና ከማን ጋር መዋለ ነዋይ ፈሰስ ይደረጋል የሚለው እስካሁን ግልፅ አይደለም።
ጎን ለጎን በኳታር አሸማጋይነት በቀጥታ በታጣቂ ቡድኑ እና በኮንጎ መንግሥት መካከል የሚካሄደው ድርድር በመጪዎቹ ወራት ተጨማሪ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።
የኮንጎ ወንዝ ትብብር አባል የሆነው ኤም23 የዋሽንግተኑ ስምምነት ትልቁን የግጭቱን መነሻ ለመፍታት ውስንነት ያለበት ነው ብሏል። ነፍጥ ያነሳሁት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ህዳጣን የሆኑትን የቱትሲ ሕዝቦችን መብት ለመጠበቅ ነው በሚለው አቋሙ እንደፀና ነው።
ተዋጊዎች ለሰላም መውጫ መንገዳቸውን እስከሚያበጁ ድረስ በሩባያ ማዕድን ማውጫ ያሉ እና በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚኖሩ ሰዎች በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ያደረገው ግጭቱ እና ደም መፋሰሱን እንዲቆም ይሻሉ።
ማዕድን ቆፋሪው ኦሲአሲ ". . . ለመሪዎቻችን የማቀርበው ውትወታ በአካባቢያችን ሰላምን እንዲያፀኑ ነው" ይላል።
ለሰዓታት ወደ ሚዘልቀው ቁፋሮ ከመመለሱ በፊት "ለማዕድን ማውጫ ባለቤቶች ደሞዛችንን እንዲጨምሩ እጠይቃለሁ፤ ምክንያቱም በጣም አነስተኛ ነው" ሲል አክሏል።















