ኮንጎ እና ሩዋንዳ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረውን የሰላም ስምምነት በዋሽንግተን ተፈራረሙ

የኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የሩዋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, AFP

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን አስከፊ ግጭት ለማስቆም የሚያስችል የሰላም ስምምነት በዋሽንግተን ተፈራረሙ።

በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አማካኝነት የተፈረመው ይህ የሰላም ስምምነት አሜሪካ ከኮንጎ ብርቅዬ ማዕድናት ተጠቃሚ እንድትሆን ሊያደርጋት እንደሚችል ተገልጿል።

በሁለቱ ጎረቤት አገራት የተደረሰው የሰላም ስምምነት በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊከ ኮንጎ የሚዋጉ ታጣቂ ቡድኖች "ውጊያ ማቆም፣ ትጥቅ መፍታት እና ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስን ያለመ" ነው።

ስምምነቱን በተመለከተ ዝርዝር መረጃዎች አልወጡም።

በቀጠናው አሸማጋይነት የተጀመሩ የሰላም ስምምነቶች ከዚህ ቀደም ቢከሽፉም የአሜሪካ እና የኮንጎ መሪዎች ስምምነቱን ከአሁኑ "ትልቅ ድል" ሲሉ አሞካሽተውታል።

"ዛሬ ግጭቱ እና ውድመቱ ተቋጭቷል።መላው ቀጠና አዲስ የተስፋ እና የእድል ምዕራፍ ጀምሯል" ሲሉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት ተናግረዋል።

ትራምፕ፤ ምክትል ፕሬዚዳንታቻው ጄዲ ቫንስ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ማርኮ ሩቢዮ እንዲሁም ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ የተውጣጡ ልዑካን በተገኙበት ቢሯቸው በሰጡት መግለጫ የሰላም ስምምነቱን "አስደናቂ ድል" ብለውታል።

ስምምነቱ የተፈረመው በአገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አማካኝነት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢሮ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ ከዚያ በኋላ በስምምነቱ ላይ ፊርማቸውን ባኖሩበት ወቅት "ትልቅ ስኬት ነው" ብለዋል።

የኮንጎ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤትም "ለፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ በ30 ዓመት ከታዩት የበለጠ ሌላ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት " ሲል የሰላም ስምምነቱ ከመፈረሙ በፊት መግለጫ አውጥቷል።

ምንም እንኳን ቀኑ ባይገለጽም የኮንጎው ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ እና የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ወደ ዋሽንግተን አቅንተው ከትራምፕ ጋር እንደሚገናኙ ተነግሯል።

በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ኳታር ይህንን ለማርገብ ከጥቂት ወራት በፊት የሽምግልና ጥረት መጀመሯን ስለ ድርድሩ የሚያውቁ ዲፕሎማት ተናግረዋል።

ኳታር ወደ ሁለቱም አገራት ልዑካን የላከች ሲሆን፤ የኮንጎ እና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንቶች ዶሃ ላይ ከተገናኙ በኋላ በአሜሪካ የሚደገፍ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሟል ሲሉ ይኝሁ ዲፕሎማት አክለዋል።

ከጥቂት ወራት በፊት የኤም 23 አማጺያን የምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መዲና ጎማ፣ የቡካቩ ከተማ እና ሁለት አየር ማረፊያዎችን ጨምሮ ሰፊ ግዛት መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ለአስርት ዓመታት የዘለቀው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦርነት የበለጠ እንዲባባስ አድርጎታል።

በቅርቡም በተደረጉ ውጊያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ እንዲሁም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

ግዛቶቹን ያጣው የኮንጎ ማዕከላዊ መንግሥት አሜሪካ እርዳታ እንድትሰጠው ጠይቋል።

በዚህም አሜሪካ የደህንነት ዋስትና የምትሰጠው ከሆነ በምላሹ ወሳኝ የሆኑ ማዕድናትን ለመስጠት መጠየቁ ተዘግቧል።

የምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ግዛት ኮልታን ጨምሮ በአለም አቀፉ የኤሌክትሪክ ኢንዱስትሪ አስፈላጊ የሆኑ የማዕድን ግብዓቶች የበለጸገ ነው።

ሩዋንዳ ኤም23 የተሰኘውን ታጣቂ ቡድን እንደምትደግፍ በርካታ መረጃ የቀረበባትን ክስ አትቀበለውም።

ሩዋንዳ፤ በኮንጎ ወታደሮቿን ያስገባችው በአብዛኛው ከሁቱ ብሔር የተውጣጣና በአውሮፖውያኑ 1994 የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ ግንኙነት ያለው ኤፍዲኤልአር (Democratic Forces for the Liberation of Rwanda) የተባለው ታጣቂ ቡድን የጋረጠውን ስጋት ለመከላከል ነው ትላለች።

ሩዋንዳ በበኩሏ ኤፍዲኤልአር የተሰኘውን ቡድን ኮንጎ ትደግፋለች ስትል የምትከስ ሲሆን ኮንጎ ይህንን አትቀበለውም።

የኮንጎ ተደራዳሪዎች የሩዋንዳ ወታደሮች ከኮንጎ በአስቸኳይ መውጣታቸው በስምምነቱ እንዲካተት ጫና ማድረጋቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

በኮንጎ ምድር 7 ሺህ ወታደር ያላት ሩዋንዳ ይህንን ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆነች ተገልጿል።

የሩዋንዳ ወታደሮች ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለቆ መውጣት ለሁለቱ አገራት አከራካሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ነው።

ስምምነቱ ሊፈረም ጥቂት ሰዓታት ሲቀረው የትሽሴኬዲ ጽሕፈት ቤት ስምምነቱ የሩዋንዳ ወታደሮች ለቀው እንዲወጡ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ሆኖም የተፈረመው ስምምነት ሙሉ ዝርዝር ይፋ እስካልሆነ ድረስ በርካታ መሰረታዊ ጥያቄዎች ምላሽ አያገኙም።