የኮንጎ አማጽያን ቁልፍ ከተማ መቆጣጠራቸውን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማጽያን በምስራቃዊ ክፍል የምትገኘውን ቁልፍ የሆነችውን የጎማ ከተማን መቆጣጠራቸውን ሲናገሩ የአገሪቱ መንግሥት ይህንን አስተባብሏል።
ኤም23 የተሰኙት የኮንጎ አማጺያን መብረቃዊ በሚባል ግስጋሴ እሁድ፣ የካቲት 18/ 2017 ዓ.ም የጎማ ዋና ጎዳናዎችን መክበባቸውን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ነዋሪዎች አጋርተዋል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ አጎራባች ከተሞች ሸሽተዋል።
ከሰዓታት የተኩስ ልውውጥ እና ፍንዳታዎች በኋላ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችን የያዘችው ጎማ ጎዳናዎች ጸጥታ እንደሰፈነባት የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጎረቤት አገር ሩዋንዳ አማጺያኑን ለመደገፍ ወታደሮቿን ወደ ድንበር በመላክ ጦርነት አውጃለች በማለት ከከሰሰ ከሰዓታት በኋላ ነው ይህ የተሰማው።
ሩዋንዳ ኤም 23ን መደገፏን የማትክድ ሲሆን የኮንጎ ባለስልጣናት በኪጋሊ መንግሥትን ለመጣል የሚሞክሩ ሚሊሻዎችን ይደግፋሉ በማለት ትከሳለች።
ኬንያ የተኩስ አቁም ጥሪ ያደረገች ሲሆን የሁለቱም የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና የሩዋንዳ ፕሬዚዳንቶች በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ በሚካሄደው ቀጣናዊ ጉባኤ ላይ እንደሚገኙ አስታውቃለች።
የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ሊቀመንበር የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የቀጠናው መሪዎች ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
ኤም23 የተሰኘው ታጣቂ ቡድን በማዕድን የበለጸገውን ምስራቃዊ የአገሪቱን ክፍል ከአውሮፓውያኑ 2021 ጀምሮ ተቆጣጥሮ ይገኛል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት የተደረገውን ከፍተኛ ውጊያ ተከትሎ አማጺያኑ ወደ ጎማ በፍጥነት እየገሰገሱ ነበር። በባለፈው ወር ብቻ ከ400 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከሩዋንዳ አዋሳኝ አቅራቢያ በሚገኘው በሰሜን እና ደቡብ ኪቩ ግዛቶች ከመኖሪያ ቤታቸው እንደተፈናቀሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል።
በጎማ ዙሪያ ያሉ ቁልፍ መንገዶች መዘጋታቸውን እና የከተማዋ አየር ማረፊያም ነዋሪዎችን ለማስወጣትም ሆነ ለሰብዓዊ እርዳታ አገልግሎት መስጠት እንዳቆመ የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
ሰኞ ማለዳ ላይ የአገሪቱ መንግሥት በሰጠው መግለጫ ጦሩ አሁንም አውሮፕላን ማረፊያውን ጨምሮ የከተማዋን ስትራቴጂካዊ ክፍሎች እንደተቆጣጠረ ነው ብሎ ነበር።
"በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከሚሰራጩት ሃሰተኛ መልዕክቶች በተቃራኒ የኮንጎ ጦር የጎማ አውሮፕላን ማረፊያን እና የሰሜን ኪቩ ግዛት መዲናን ስትራቴጂካዊ ስፍራዎች እንደተቆጣጠረ ነው " ብሏል
ጦሩ ከፍተኛ መስዋዕትነት በሚያስከፍልበት ሁኔታ አገሩን ለመከላከል ቆርጦ ተነስቷል ሲልም መግለጫው አክሏል።
አንድ የጎማ ነዋሪ "በከተማዋ ውስጥ ግራ መጋባት አለ። እዚህ አየር ማረፊያ አካባቢ ወታደሮችን እናያለን። የኤም23 ታጣቂዎችን እስካሁን አላየሁም" ሲሉ ለሮይተርስ የተናገሩ ሲሆን አንዳንድ ሱቆችም ተዘርፈዋል ብለዋል።












