ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ ክብረ ወሰን በሰበረ ዋጋ ለቼልሲ ፈረመች

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የአሜሪካ ተከላካይ መስመር ተጫዋቿ ናኦሚ ግርማ በሴቶች እግር ኳስ ክብረ ወሰን በሆነ ዋጋ ለቼልሲ ፈርማለች።
የ24 ዓመቷ ተከላካይ በአውሮፓውያኑ እስከ 2029 ከሰሜን ለንደኑ ክለብ ጋር የሚያቆያትን ፊርማ አኑራለች።
የሴቶች ሱፐር ሊግ መሪው ቼልሲ ለአሜሪካው ሳን ዲዬጎ 900 ሺህ ፓውንድ በመክፈል ነው ናኦሚን ያስፈረማት።
"በጣም ደስተኛ ነኝ። ወደዚህ በመምጣቴ ደስ ብሎኛል። እውነት መሆኑን ማመን ተስኖኛል" ስትል ናኦሚ ተናግራለች።
የሊጉ መሪ ቼልሲ አዲስ ፈራሚዋን ለደጋፊዎች ካስተዋወቀች በኋላ አርሰናልን 1 ለምንም አሸንፋለች።
"ወደ ቼልሲ እንድመጣ ያደረጉኝ ብዙ ነገሮች አሉ። ባሕሉ፣ ለማሸነፍ ያለው ጉጉት፣ ሠራተኞቹ እና ተጫዋቾቹ። ለመማር እና ለማደግ ትልቅ ቦታ ነው። አሁን ማድረግ የምፈልገው እሱን ነው" ብላለች።
ከዚህ ቀደም በሴቶች እግር ኳስ ከፍተኛው የነበረው ዋጋ 685 ሺህ ፓውንድ ነበር። ባለፈው የካቲት ቤይ ኤፍሲ ሬቸል ኩንዳናንጂን ስታስፈርም የከፈለችው ገንዘብ መጠን ነው።
ቼልሲ ባለፈው ዓመት ጥር ማይራ ራሚሪዜን ስታስፈርም 384 ሺህ በመክፈል የእንግሊዝን ክብረ ወሰን ይዛ ነበር።
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ናኦሚ ግርማ "ከሚሊ ብራይት ጋር ለመጫወት በጣም ጓጉቻለሁ" ስትል ለቢቢሲ ስፖርት ተናግራለች። ሚሊ ብራይት በበኩሏ ናኦሚ ወደ ቼልሲ በመምጣቷ ደስተኛ መሆናን አሳውቃለች።
ከኢትዮጵያውያን እናት እና አባት የተወለደችው የ24 ዓመቷ ናኦሚ የአሜሪካ ምርጥ ተጫዋች ተብላ የተመረጠች የመጀመሪያዋ ተከላካይ ናት።
የዩናይትድ ስቴትስ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን የኦሊምፒክ ወርቅ ባለቤት ሲሆን እያንዳንዱን ደቂቃ ተጫውታለች። የኋላ ደጀን የምትባለው ናኦሚ ኳስ በመቆጣጠር እና በመሪነት ችሎታዋ አድናቆት ይጎርፍላታል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በ2024 የፓሪስ ወርቅ፣ ኮንካካፍ ጎልድ ዋንጫ እና ሺ ቢሊቭስ የተባለው ዋንጫ ባለቤት መሆን ችላለች።
ናኦሚ ያለፈው ዓመት የቢቢሲ ስፖርት የዓመቱ ምርጥ ሴት እግር ኳስ ተጫዋች ዕጩ እንደነበረች አይዘነጋም።












