ሪያል ማድሪድ 1 ቢሊዮን ዩሮ ትርፍ በማግኘት የመጀመሪያ ክለብ ሲሆን ዩናይትድ እና አርሰናልም አትርፈዋል

ሪያል ማድሪድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የስፔኑ ሪያል ማድሪድ አንድ ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ትርፍ በማጋበስ የመጀመሪያ ክለብ መሆኑን ዴሎይት የተባለው ድርጅት አስታወቀ።

ዴሎይት በሚያወጣው ዓመታዊ መረጃ መሠረት ሪያል ማድሪድ በ2023/24 የውድድር ዘመን 1.05 ቢሊዮን ዩሮ ትርፍ አስገብቷል።

ማድሪድ ባለፈው የውድድር ዘመን የስፔን ላ ሊጋ እና የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ባለድል ሆኗል።

የእንግሊዙ ክለብ ማንቸስተር ሲቲ 708 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ባለፈው የውድድር ሲቲ ለአራተኛ ተከታታይ ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሲያሸንፍ የክለብ ዓለም ዋንጫ እና የአውሮፓ ሱፐር ካፕ ባለቤትም ሆኗል።

ፓሪ ሳን ዠርማ 681 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ በማምጣት ሶስተኛ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ በ651 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ አራተኛ እንዲሁም ባየርን ሙኒክ በ646 ሚሊዮን ዩሮ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ከአውሮፓውያኑ 2011 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውሮፓ ውድድሮች የተመለሰው አስተን ቪላ በጣም ትርፋማ ከሚባሉት 20 ቡድኖች መካከል ተመድቧል።

አርሰናል፣ ሊቨርፑል፣ ቶተንሀም፣ ቼልሲ፣ ኒውካስል እና ዌስት ሀምን ጨምሮ በጠቅላላው 9 የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ቡድኖች ከፍተኛው 20 ውስጥ ተመድበዋል።

ብራይተን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ሊግ መሳተፉን ተከትሎ 21ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ክሪስታል ፓላስ፣ ኤቨርተን፣ ፉልሀም እና ዎልቭስ ከ26 እስከ 29 ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ከ1-20 ያሉት ቡድኖች ዓመታዊ ትርፍ 6 በመቶ በመጨመር በጠቅላላው 9.47 ቢሊዮን ዶላር ሆኗል።

የስፔኑ ኃያል ክለብ ሪያል ማድሪድ በርናቤዩ የተባለውን ስታድየሙን በማደሱን ገቢው ካለፈው የውድድር ዘመን ሲነፃፀር እጅግ ከፍ ያለ ሆኗል። ማድሪድ ከስታድየም 210 ሚሊዮን ዩሮ ማስገባት ችሏል።

በተቃራኒው ባርሴሎና ከስታድየም የሚያገኘው ገቢ በመቀነሱ ከአራተኛ ደረጃ ወደ ስድስት ዝቅ ብሏል።

ሌሎች የገቢ ምንጮች የማስታወቂ እና የጨዋታ ሥርጭት ገቢ ሆነው ተመዝግበዋል።