ትራምፕ የዘር እና የፆታዊ ጉዳዮች እኩልነት ፖሊሲን በማስቀረት ሠራተኞች በግዳጅ እረፍት እንዲወጡ አዘዙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ብዝሐነት፣ እኩልነት እና አካታችነትን የሚያረጋግጠው አሠራር እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በሌሎችም መሥሪያ ቤቶች ለዚህ ትግበራ ፖሊሲ ያሠማሯቸውን ሠራተኞች ዝርዝር እንዲያሳውቁ ተጠይቀዋል።
ለዚህ አሠራር የሚመደበው በጀትም እንዲቋረጥ መወሰናቸው አነጋጋሪ ከሆኑ ውሳኔዎች መካከል ይጠቀሳል።
በአሜሪካ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በብዝሐነት፣ እኩልነት እና አካታችነት መሠረት በማድረግ በሥራ ላይ ያሉ ሠራተኞች በአጠቃላይ እየተከፈላቸው እረፍት እንዲወጡም ትራምፕ ውሳኔ አሳልፈዋል።
ይህንንም ውሳኔ ተከትሎ ሠራተኞቹ "በአፋጣኝ" የግዳጅ እረፍት እንዲወጡ በመወሰኑ ተጨማሪ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ ከሥራ ውጪ ሆነው ደሞዝ ይከፈላቸዋል።
በምጽሐረ ቃሉ ዲኢአይ (DEI) የሚባለው አሠራር በፆታ፣ በቀለም፣ በሃይማኖት፣ በወሲባዊ ዝንባሌ እና በሌሎችም የማንነት መገለጫዎች ምክንያት ሰዎች መድልዎ እና መገለል እንዳይደርስባቸው ከለላ የሚሰጥ ነው።
ዲኢአይ ፖሊሲዎችን እና አሠራሮችን የያዘ ሲሆን፣ በመንግሥት እንዲሁም በግል ተቋማትም ውክልና ያላገኙ እና ለመድልዎ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎችን እኩል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
ተቋማዊ የሆነ ኢ-ፍትሐዊነትን፣ ፆተኛነትን፣ ዘረኛነትን፣ የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች ላይ የሚደርስ መገለልን በመታገል እኩል የሥራ ዕድክ እና ተሳትፎ እንዲኖር ለማስቻል የተዘረጋ አሠራሩ ነው።
ትራምፕ ዲኢአይ ወይም diversity, equity and inclusion እንዲቋረጥ እንደሚያደርጉ ቀደም ሲልም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ሲናገሩ ነበር።
አሁን ለዚህ አሠራር የሚመደበው በጀት እንዲገታ አዘዋል።
ዲኢአይ የተባለው ብዝሐነት፣ እኩልነት እና አካታችነትን የሚያረጋግጠው አሠራር ዲኢአይኤ (DEIA) በሚል የተደራሽነት (accessibility) ፖሊሲንም ያካትታል።
ይህም የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎችን የሥራ ቦታ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት አንዲሁም ተደራሽነት ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
ትራምፕ ዲኢአይ በመንግሥት እና የግል ተቋማትም እንዳይተገበር አዘዋል።
"አደገኛ፣ ኢ-ሞራላዊ እና ብዙ የሚጠይቅ" ሲሉ አጥላልተውታል።
በዚህ ፖሊሲ ሥር የታቀፉ አሠራሮች "ለረዥም ጊዜ የቆዩ የፌደራል የሲቪል መብቶችን የሚጻረሩ" ናቸው ሲሉም ትራምፕ ተደምጠዋል።
ትራምፕ ይህንን አሠራር እንዲገታ በወሰኑበት ጽሑፍ ላይ ፖሊሲው "ብሔራዊ አንድነትን የሚያንኳስስ" ነው ተብሏል።
"የአሜሪካውያንን የትጉህ ሠራተኛነት ባህል ዋጋ የሚያሳጣና የሚያናንቅ ነው" ሲል ጽሑፉ ያትታል።
ዋይት ሐውስ በሰጠው ትዕዛዝ የመንግሥት ተቋማት የዲኢአይን አሠራርና ትግበራ "መታገል" ይኖርባቸዋል።
ዐቃቤ ሕግ በግል ተቋማት ውስጥ ዲኢአይ እና ዲኢአይኤን በተቀላጠፈ መንገድ ማስቆም የሚቻልበትን መንገድ እንዲጠቁም 120 ቀናት ተሰጥተውታል።
"በጣም አግላይ እና መጥፎ የሆኑ የዲኢአይ" ፖሊሲዎችን በመለየት እንዴት ማስቆም እንደሚቻል ዐቃቤ ሕግ ምክረ ሐሳብ እንዲያቀርብም ይጠበቃል።
ትራምፕ የምረጡኝ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ፖሊሲው ነጮች ሥራ እንዳይቀጠሩ ስለሚያሰናክል እንደሚሰርዙት ቃል መግባታቸው ይታወሳል።
የትራምፕን መመረጥ ተከትሎ ማክዶናልድስ፣ ዋልማርት እና ሜታን ጨምሮ አብዛኞቹ የአሜሪካ ተቋማት የዲኢአይ አሠራራቸውን ለውጠዋል ወይም ትግበራውን ቀንሰዋል።
እንደ አፕል፣ ታርጌት እና ካስኮ ያሉ ተቋማት ደግሞ አሁን የሚሠሩበትን መንገድ በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ትራምፕ ዲኢአይ እና ዲኢአይኤን "ብክነት" ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
የትራምፕን ትዕዛዝ ተከትሎ ፕረስ ሴክሬተሪያቸው ካሮላይን ሌቪት እንዳሉት መንግሥት አሠራሩን የሚገታበት መንገድ እስከሚቀየስ ድረስ በዚህ ፖሊሲ ትግበራ ላይ የተሠማሩ ሠራተኞች እየተከፈላቸው እረፍት እንዲወጡ ተወስኗል።
ብዝሐነት፣ እኩልነት እና አካታችነትን የሚያረጋግጠው አሠራር መሰረዙን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄም "ጥያቄ ላቀረባችሁ ጋዜጠኞች ይህ እውነት መሆኑን በደስታ አረጋግጣለሁ" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ተቋማት ከዲኢአይ እና ዲኢአይኤ ጋር የተያያዙ ድረ ገጾችን እና የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን እንዲገዙም ታዘዋል። ከጉዳዩ ጋር የተያያዘ ሥልጠናዎችን መስጠትም እንዲቆም ትዕዛዝ ተላልፏል።
ስለ ትራምፕ ውሳኔ በወጣው ጽሑፍ ላይ እንደተገለጸው በአሜሪካ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በብዝሐነት፣ እኩልነት እና አካታችነት ክፍሎች ያገለግሉ የነበሩ ሠራተኞች ባጠቃላይ እየተከፈላቸው እረፍት እንዲወጡ ቀነ ገደብ የተሰጠው ከጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ነው።
ሠራተኞቹ እረፍት ላይ በሚሆኑበት ጊዜ "የዲኢአይ እና ዲኢአይኤ ቢሮዎች፣ አሠራሮች እና ፕሮግራሞች" እንደሚቋረጡ ተገልጿል።
ምን ያህል ሠራተኞች ከሥራ ውጪ እንደሚሆኑ እስካሁን ትክክለኛው ቁጥር ለማወቅ አልተቻለም።
ይህንን አሠራር "በድብቅ" ለማስተግበር የሚሞክሩ ሠራተኞች ላይ ጥቆማ እንዲደረግም ተጠይቋል።
የዲኢአይ እና ዲኢአይኤ አሠራር በአሜሪካ ውስጥ ያለ መድልዎ እና መገለል የሥራ ዕድል እና ሌሎችም ተያያዥ ጥቅሞችን ተደራሽነት የሚያደርግ ሲሆን፣ እኩልነት እና ፍትሐዊነትን በማረጋገጥ ረገድ ዋጋ እንዳለውም ይገለጻል።
ሆኖም ግን ትራምፕ ያስተላለፉትን ዕግድ ተከትሎ በወጣው መመሪያ መሠረት የአሜሪካ የፍትሕ ቢሮ የግል ተቋማት እና የትምህርት ተቋማት ለዲኢአይ እንዲሁም ዲኢአይኤ የሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ ማበረታታት ይኖርበታል።












