ትራምፕ ሥልጣን መረከባቸውን ተከትሎ የቻይና እና የሩሲያ ፕሬዝዳንቶች 'ለመተባበር' ተስማሙ

የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ዢፒንግ እና የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ዢፒንግ እና የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቃለ መሐላ ፈጽመው የመሪነት ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ።

የትራምፕን በዓለ ሲመት ተከትሎ ሁለቱ መሪዎች በቪድዮ ውይይት ካደረጉ በኋላ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን "ከፍ ወዳለ ደረጃ" ለማድረስ መስማማታቸው ተዘግቧል።

የሁለቱም አገራት ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ ፑቲን ዢን "ውድ ጓደኛዬ" ሲሉ ጠርተዋቸዋል።

ሩሲያ እና ቻይና የውጭ ጫና ቢበዛባቸውም ወዳጅነታቸው "በጓደኝነት፣ በጋራ ትብብር እና መተማመን" ላይ የተመሠረተ መሆኑን መሪዎቹ ተነጋግረዋል።

ዢ ጂንፒንግ "የጋራ ትብብራቸው እንዲጠናከር፣ የጋራ ፍላጎቶቻቸው እንዲጠበቁ እና ስትራቴጂያዊ ግንኙነታቸው የበለጠ እንዲጠናከር" ፑቲንን ጠይቀዋል።

ትራምፕ ቤይጂንግ ላይ ቀረጥ ለመጨመር ዝተዋል።

ቻይናን "በዝባዥ" ያሉት ትራምፕ ሩሲያን ደግሞ "ከፍተኛ ችግር" ይጠብቃታል ሲሉ አስፈራርተዋል።

ሩሲያ የዩክሬንን ጦርነት በስምምነት ካላስቆመች "ችግር" እንደሚጠብቃት ትራምፕ ተናግረዋል።

ፑቲን ከዢ ጂንፒንግ ጋር ሲወያዩ ከዩክሬን ጋር ስምምነት የሚኖረው ዩክሬን "የሩሲያን ፍላጎት ስታከብር" መሆኑን መግለጻቸውን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ አማካሪ ዩሪ ዩሻኮቭ ተናግረዋል።

ቻይና ሩሲያ በዩክሬን የተጠቀመችውን የጦር መሣሪያ ገንብታለች ተብሏል።

በሁለቱ አገራት መካከል የሚካሄደው ንግድ እአአ በ2023 ወደ 240 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል። በ2021 ከነበረው 64 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ አማካሪ ዩሪ ዩሻኮቭ እንዳሉት ፑቲን እና ዢ ጂንፒንግ "የጋራ ጥቅም ባስጠበቀ እና አክብሮት በተሞላ ሁኔታ" ከአሜሪካ ጋር ለመሥራት ዝግጁ ናቸው።

ይህ የሚሆነው የትራምፕ አስተዳደር ፍላጎት ካለው ነው ብለዋል።

የሁለቱ አገራት መሪዎች ንግግር ከትራምፕ ሥልጣን መያዝ ጋር የሚገናኝ እንዳልሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

የቪድዮ ውይይቱ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ የወሰደ ነው። መሪዎቹ ስለ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን መነጋገራቸውም ተጠቁሟል።

ዢ ዝርዝር መረጃ ባይሰጡም "የውጭ ስጋቶችን" በተመለከተ ከፑቲን ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዢ ጂንፒንግ ባለፈው ሳምንት ከትራምፕ ጋር በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን፣ ትራምፕ ውይይታቸውን ለሁለቱም አገራት "በጣም ጥሩ" ሲሉ ገልጸውታል።

ስለ ንግድ፣ ቲክቶክ እና ፌንታኒል ስለተባለው መድኃኒትም መወያየታቸው ተገልጿል።

ፑቲን ገና ከትራምፕ ጋር ባይነጋገሩም ከበዓለ ሲመቱ በኋላ ትራምፕን በቴሌቭዥን ቀርበው እንኳን ደስ አለዎት ብለዋል።