የእስራኤል ወታደራዊ አዛዥ የመስከረም 26ቱን ጥቃት ባለማክሸፋቸው ከስራ ለቀቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ለ15 ወራት ለዘለቀው የጋዛ ጦርነት ምክንያት የሆነውን በፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ የተፈጸመው የመስከረም 26ቱን ጥቃት መከላከል ባለመቻላቸው የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዳልተወጡ የገለጹት የእስራኤል ወታደራዊ አዛዥ ከስራ ለቀቁ።
ሌተናል ጄኔራል ሄርዚ ሃሌቪ ለመከላከያ ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ፤ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት "የእስራኤልን ዜጎች የመጠበቅ ኃላፊነቱን አልተወጣም" ብለዋል።
"ይህንን ኃላፊነት ባለመወጣቴ በየቀኑ እና በየሰዓቱ አብሮኝ ያለ ሲሆን በቀሪው ህይወቴም አብሮኝ ይቀጥላል" ሲሉ አክለዋል።
ምንም እንኳን የእስራኤል የጦርነት ግቦች "ሁሉም" አንዳልተሳኩ ያመኑት ጄኔራሉ ለሰራዊቱ "ጉልህ ስኬቶች" በተመዘገቡበት በአውሮፓውያኑ መጋቢት 6 ሥራቸውን እንደሚለቁ ተናግረዋል።
"ጦሩ ሐማስን እና አመራሩን የበለጠ በማውደም ታጋቾቹ እንዲመለሱ ለማድረግ" እና በታጣቂ ቡድኖች ጥቃት የተፈናቀሉ እስራኤላውያን ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ በማድረግ ትግሉ ይቀጥላል ብለዋል።
ብዙም ሳይቆይ ደግሞ የእስራኤል ጦር የደቡባዊ ዕዝ ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ያሮን ፊንከልማን "ምዕራብ ኔጌቭን እና የሚወዷቸውን ጀግኖች ነዋሪዎቿን" የመጠበቅ ግዴታቸውን አልተወጣሁም በሚል ከኃላፊነት እንደሚነሱ አስታውቀዋል።
አመራሮቹ የስሥራ መልቀቂያቸውን ያስገቡት የጋዛ የተኩስ አቁም እና የታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ከሐማስ ጋር ስምምነት ተደርሶ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ከሦስት ቀናት በኋላ ነው። ሐማስ በእስራኤል፣ በአሜሪካ እና በሌሎች አገሮች በአሸባሪነት የተፈርጇል።
ከ15 ወራት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐማስ ታጣቂዎች የእስራኤልን ከጋዛ የሚያዋስናትን አጥር ጥሰው በአካባቢዎቹ ባሉ የእስራኤል ማህበረሰቦች ላይ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት የእስራኤል ወታደራዊ እና የስለላ ባለስልጣናት ብዙ ማስጠንቀቂያዎችን ባለመስማት ወይም ችላ በማለታቸው ወደ አንድ ሺህ 200 የሚጠጉ ሰዎች ሲገደሉ 251 ሰዎች ታግተዋል።
የመከላከያ ሃይሉ በጋዛ የአየር እና የምድር ዘመቻ በመክፈት ምላሽ የሰጠ ሲሆን ከ47 ሺህ 100 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ጄኔራል ሃሌቪ ማክሰኞ ዕለት በቴሌቭዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ "በከባድ ሁኔታ ተጎድቷል" ብለዋል። 20 ሺህ የሚጠጉ "ተላላኪዎችን ጨምሮ "አብዛኞቹ የቡድኑ አመራሮች እና ወታደራዊ አዛዦች" ተገድለዋል።
ኃላፊነቱን ከመልቀቃቸው በፊትም በመስከረም 26 ጥቃት ዙሪያ ጦሩ የጀመረው ምርመራ "ከፍተኛ ጥራት ያለው፣ የተሟላ እና ሙሉ በሙሉ ግልጽነት ያለው" ሆኖ እንደሚጠናቀቅም ቃል ገብተዋል።
ወታደራዊው ምርመራው ግን "በጦሩ ላይ ብቻ ያተኮረ እና ወደፊት ተመሳሳይ ክስተቶችን ሊከላከሉ የሚችሉ ሰፊ ሁኔታዎችን አያካትትም" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"የአጣሪ ኮሚሽንም ሆነ ሌላ የውጭ አካል መርምሮ እና አጣርቶ ከጦሩ ሙሉ ግልጽነት ያገኛል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው ጄኔራል ሃሌቪ በጦርነቱ ወቅት ላበረከቱት አገልግሎት እና የመከላከያ ሠራዊቱን ስላገዙት ምስጋናቸውን አቅርበው "ለእስራኤል ትልቅ ስኬት አስገኝቷል" ብለዋል።
ኔታንያሁ በራሳቸው በኩል እስካሁን ድረስ ስለመስከረም 26 የተናገሩት ነገር ቢኖር በተፈጸመው ነገር በጣም ማዘናቸውን እና ምንም አይነት ኃላፊነት ሳይወስዱ "አንዳንድ ከባድ ጥያቄዎችን" መመለስ እንዳለባቸው ብቻ ገልጸዋል። ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን የጋዛ ጦርነት እስኪያበቃ ድረስ መጠበቅ እንዳለበትም ተናግረዋል።
የተቃዋሚው መሪ ያይር ላፒድ የሃሌቪን ውሳኔ አድንቀው ኔታንያሁም ተመሳሳይ መንገድ እንዲከተሉ ጠይቀዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩና መላው መንግስታቸው አሁን ኃላፊነቱን ወስደው ስልጣን የሚለቁበት ጊዜ ነው።"
ጄኔራል ሃሌቪ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ጦር ከሐማስ ጋር የተደረሰው ባለሦስት ምዕራፍ የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነትን በበላይነት እየተቆጣጠሩ ነው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ሴቶች፣ ህጻናት እና አዛውንቶችን ጨምሮ 33 ታጋቾች ይለቀቃሉ።
እስራኤል በምላሹ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ትለቃለች።
የእስራኤል ጦር ከምሥራቃዊ የጋዛ ክፍል እንደሚወጣ እና የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን ወደቀያቸው እንዲመለሱ እንደሚፈቀድላቸው ተገልጿል።
በየቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ ሰርጥ እንዲገቡም ይፈቀዳል።
በሁለተኛው የስምምነቱ ዙር ተጨማሪ ታጋቾች የሚለቀቁ ሲሆን፣ የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና "ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት" ያለመ ሲሆን ይህም የሚተገበረው የመጀመሪያው ዙር 16 ቀን ሲሞላው ነው።
ሦስተኛው እና የመጨረሻው ምዕራፍ ጋዛን መልሶ መገንባት ሲሆን፣ ይህም ዓመታት ይወስዳል።
በዚህ ምዕራፍ የታጋቾች አስክሬንም ይመለሳል።
በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እና የታጋቾች ቤተሰቦች ስምምነቱ ይጸናል ወይ በሚል ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ወድቀዋል።
የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንዲደረስ ሚና እንደነበራቸው የገለጹት አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሦስቱም ምዕራፎች ተግባራዊ ይሆናሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ሰኞ ዕለት ገለጸዋል።
ኔታንያሁ በበኩላቸው እስራኤል "የሁለተኛው ምዕራፍ ድርድሮች ውጤት አልባ ናቸው ወደሚል መደምደሚያ ላይ ከደረሰች ወደ ጦርነቱ ለመመለስ የአሜሪካ ድጋፍ እንዳላት" ተናግረዋል።












