እስራኤል በጄኒን በከፈተችው ከባድ ጥቃት ዘጠኝ ፍልስጤማውያን ተገደሉ

እስራኤል የከፈተችው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, AFP

እስራኤል በኃይል በተቆጣጠረቻት የፍልስጤሟ ዌስት ባንክ በምትገኘው ጄኒን ከተማ በከፈተችው ከባድ ጥቃት ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ 35 መቁሰላቸውን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በርካታ ቁጥር ያላቸው የእስራኤል ወታደሮች ወደ ከተማዋ እና ወደ ስደተኛ ካምፑ ሲገቡ በድሮኖች፣ ሄሊኮፕተሮች እና በታጠቁ ቡልዶዘሮች ታግዘው እንደሆነ የፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። በከተማዋ ተከታታይ የአየር ጥቃቶች ተፈጽመዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በጄኒን "ሽብርተኝነትን ለማሸነፍ ሰፊ እና ጉልህ የሆነ ዘመቻ" አገራቸው መጀመሯን ተናግረዋል።

ጦሩ ይሄንን ጥቃት የከፈተው በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ከሆነ ከሶስት ቀናት በኋላ ነው። ከጦሩ በተጨማሪ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በአንድ ጀምበር የፈጸሟቸው ጥቃቶች በዌስት ባንክ በቀጣዪ ሊኖር የሚችለውን ብጥብጥ አሳይ ነው ተብሏል።

የጄኒን አስተዳዳሪ ካማል አቡ አል ሩብ "እየሆነ ያለው የስደተኞች ካምፑ ላይ ወረራ ነው። በፍጥነት ነው የተካሄደው። ሄሊኮፕተሮች በሰማይ ላይ ሲያንዣብቡ እና የእስራኤል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች በሁሉም ቦታ ላይ ገቡ" ሲሉ ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

እስራኤላውያን ሰፋሪዎች የፈጸሟቸው ጥቃቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, እስራኤላውያን ሰፋሪዎች የፈጸሟቸው ጥቃቶች

የፍልስጤም የዜና ወኪል ዋፋ በበኩሉ የእስራኤል ወታደሮች የጄኒን የስደተኞች ካምፕን "ሙሉ በሙሉ ከበባ ውስጥ እንዳስገቧት እና የታጠቁ ቡልዶዘሮች በርካታ መንገዶችን ለመቁረጥ ቁፋሮ ማካሄዳቸውን" የሃገር ውስጥ ምንጮችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

በእስራኤል ጥቃት ከቆሰሉት መካከል ሶስት ዶክተሮች እና ሁለት ነርሶች እንደሚገኙበት ዋፋ የጄኒን የመንግሥት ሆስፒታል ዳይሬክተር ዊሳም ባከርን ጠቅሶ ዘግቧል።

የፍልስጤም የደኅንነት አባላት የእስራኤል ወታደሮች ማክሰኞ ማለዳ ላይ ከመግባታቸው በፊት በጄኒን የስደተኞች ካምፕ ዙሪያ ከሚገኙ አንዳንድ ይዞታቸው ለቀው መውጣታቸው ተዘግቧል።

የፍልስጤም የጸጥታ ኃይሎች ቃል አቀባይ ብሪጋዲየር ጄነራል አንዋር ራጂብ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የእስራኤል ወታደሮች በሰላማዊ ሰዎች እና በጸጥታ ኃይሎች ላይ ተኩስ ከፍተው ጉዳት አድርሰዋል።

ማክሰኞ ማምሻውን የፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር ሙታዝ አቡ ተቤክ የባለ የ16 ዓመት ታዳጊ እና ስምንት ሰዎች በእስራኤል ወታደሮች መገደላቸውን አስታውቋል።

ቲያኔክ በተሰኘች መንደር አንድ ፍልስጤማዊ በእስራኤል ወታደሮች በጥይት ተመትቶ መገደሉን አክሏል። ከጦሩ በተጨማሪ በዌስት ባንክ እስራኤላውያን ሰፋሪዎች በፍልስጤማውያን ጂንሳፉት እና አል ፉንዱቅ በተሰኙት መንደሮች ላይ ጥቃት ከፍተዋል።

በርካታ ጭምብል ያጠለቁ ሰፋሪዎች የፍልስጤማውያን ቤቶች ላይ እና መኪኖቻቸው ላይ እሳት በመልቀቅ ንብረቶቻቸውን አውድመዋል። በዚህም ቢያንስ 21 ፍልስጤማውያን መቁሰላቸውን የፍልስጤም ቀይ ጨረቃ አስታውቋል።