የፌደራል እና የኦሮሚያ መንግሥታት በአርሲ ዞን የሚፈጸመውን ግድያ እንዲያስቆሙ ኢሰመኮ አሳሰበ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂዎች እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎች እና የተለያዩ ግፎችን ለማስቆም የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግሥታት ተጨባጭ እና ዘላቂ እርምጃዎችን እንዲወስዱ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ።
በአርሲ ዞን የሚንቀሰቀሱ ታጣቂዎች ለረጅም ጊዜ በነዋሪዎች ላይ ግድያ፣ የአካል ጉዳት፣ አገታ፣ የንብረት ውድመት እና መፈናቀል ሲፈጽሙ መቆየታቸው ሲዘገብ ቆይቷል።
ባለፈው ሳምነት ማብቂያ ላይ በነበሩ ቀናትም በዞኑ ታጣቂዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የኢሰመኮ ረቡዕ የካቲት 25/2018 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከሁለት ዓመት በፊት ከተፈጸመ ተመሳሳይ ጥቃት በኋላ በዞኑ የነበረው ሁኔታ ለተወሰኑ ጊዜያት "እየተሻሻለ የነበረ ቢመስልም" አሁን መልሶ መገርሸቱን ጠቅሷል።
በዚህም ከጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ታጣቂዎች በሽርካ፣ በጉና፣ በመርቲ፣ በአሰኮ እና በኦንቆሌ ዋቤ ወረዳዎች በሰዎች ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች በሰዎች ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን በመረጃ ማረጋገጡን ገልጿል።
የካቲት 19/2018 ዓ.ም. በዞኑ ሽርካ ወረዳ ጃዊ ቀበሌ እና በሮቤ ወረዳ ገባ ቀበሌ በተፈጸመ ጥቃት ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸውን፣ አካል ጉዳት መድረሱን፣ እገታ እና መፈናቀል ማጋጠሙን ኢሰመኮ አመልክቶ፤ ለድርጊቶቹ "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ("ኦነግ ሸኔ")" ተጠያቂ እንደሆነ አሰባሰብኩት ባለው መረጃዎች ማረጋገጡን አመልክቷል።
ባለፈው ሳምንት የተፈጸመውን የ30 በላይ ሰዎች ግድያን ተከትሎ ኢሰመኮ ተጠያቂ ያደረገው መንግሥት "ሸኔ" የሚለው እና በሽብር ቡድንነት የተፈረጀው "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" ባወጣው መግለጫ በጥቃቱ ውስጥ እጁ እንደሌለበት አስተባብሏል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ አርሲ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ አካል ጉዳቶች፣ ማፈናቀሎች፣ እገታዎች እንዲሁም የንብረት ውድመቶች እና ዘረፋዎች በሕይወት የመኖር መብትን ጨምሮ ነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን በሰላም እንዳያከናውኑ አድርጓቸዋል ብለዋል።
ኢሰመኮ ባይጠቅስም ነዋሪዎች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተከታታይ ጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ሰዎች ዒላማ የተደረጉት በሃይማኖታቸው ምክንያት መሆኑን ይጠቅሳሉ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ባወጣው መግለጫ በምሥራቅ አርሲ 21 "ንጹኃን ኦርቶዶክሳውያን በግፍ መገደላቸውን፤ በሕይወት የተረፉትም ታግተው የደረሱበት እንደማይታወቅ" በመግለጽ ጥቃቱ በእምነቱ ተከታዮች ላይ የተነጣጠረ መሆኑን ገልጿል።
ኢሰመኮ በመግለጫው ግድያውን እና የሚፈጸመውን ግፍ በዘላቂነት እዲያስቆሙ ጥሪ ያቀረበላቸው የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደር በተከታታይ ቀናት ስለተፈጸመው ግድያ እስካሁን ድረስ በይፋ ያሉት ነገር የለም።















