በአርሲ ዞን ትናንትን ጨምሮ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ምንጮች ተናገሩ

መሳሪያ የያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ትናንትን ጨምሮ ባለፈው ሳምንት ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች እና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ለቢቢሲ ተናገሩ። ትናንት ምሽት በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሰዎች እንደተገደሉ ሦስት የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት የአካባቢው ነዋሪዎች እና የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች እንደገለጹት፤ በአርሲ ዞን ውስጥ በሚገኙት ሽርካ እና መርቲ ወረዳዎች ጥቃት መፈጸም የጀመረው ካለፈው ሳምንት መጀመሪያ አንስቶ ነው።

ማክሰኞ 17/2018 ዓ. ም. በመርቲ ወረዳ 'ፈቀርሳ' በተባለው ቀበሌ በተፈጸመው የመጀመሪያው ጥቃት አራት ሰዎች መገደላቸውን በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአካባቢው የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች እና አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

በአቅራቢያው በሚገኝ ሥፍራ አባቱ ላይ ጥቃት እንደተፈጸመ የገለጸ ሌላ አንድ ነዋሪ፤ አራቱ ነዋሪዎች የተገደሉት በጥይት እንደሆነ ተናግሯል። ከዚህ ጥቃት በኋላ ደግሞ ወደ እነርሱ አካባቢ የመጡ ታጣቂዎች አባቱን "እግራቸው ላይ በስለት ፋስ" መምታታቸውን እና ቤታቸውን ማቃጠላቸውን ተናግሯል።

አንድ የአካባቢው የቤተ ክርስቲያን ኃላፊ፤ ከተገደሉት አራት ሰዎች "አንዱ ሙስሊም ነው፤ ሦስቱ ክርስቲያኖች ጓደኞቹ ናቸው። 'ለምን ክርስቲያን ትገድላላችሁ?' ስላለ 'ተባባሪ' ብለው እርሱንም ገደሉት" ብለዋል።

ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር የተመዘገበበት ሁለተኛው ጥቃት የደረሰው ደግሞ ሐሙስ የካቲት 19 ቀን እንደሆነ ምንጮቹ አስረድተዋል። በሽርካ ወረዳ ጃዊ ዋጩ ቀበሌ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት 19 ሰዎች እንደተገደሉ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች እና ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኘው ጃዊ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን አመራር እና የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ አንድ ኃላፊ፤ "ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ሳናስበው መጡብን። ከዚያም በኋላ የሆነውን አድርገው፣ 21 ሰው በጥይት ጨርሰው፣ የፈለጉትን ነገር አድርገው ገቡ" ሲሉ የተፈጠረውን አስረድተዋል። ሁለት ዘመዶቻቸው መገደላቸውንም አክለዋል።

ነዋሪዎቹ የተገደሉት "በየተገኙበት" እንደሆነ የሚናገሩት ምንጮቹ፤ መንገድ ላይም፣ ቤታቸው ውስጥም ጥቃት እንደተፈጸመ ገልጸዋል። ሐሙስ ዕለት የተገደሉት ነዋሪዎች በጃዊ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን "በጅምላ" መቀበራቸውን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቢቢሲ ያነጋገራቸውን ሦስት ምንጮች እንደተናገሩት፤ በማግሥቱ ከቀኑ ዘጠኝ ወይም 10 ሰዓት ገደማ በዚሁ ቀበሌ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ደግሞ ስምንት ሰዎች ተገድለዋል። "አምስት ሰዎች ደግሞ ታግተው" መወሰዳቸውን የአካባቢው ነዋሪ የሆኑ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ታጣቂዎቹ "የአካባቢውን ነዋሪዎች ቤቶች እና የቤተ ክርስቲያኑን አስተዳደር ጽሕፈት ቤት" ማቃጠላቸውን አስረድተዋል። "እንደገና ሽማግሌዎቹን፣ አሮጊቶቹን እሳት ውስጥ እየጨመሩ እዛው አቃጠሏቸው" የሚሉት ነዋሪው፤ ከዚህ ጥቃት በኋላ እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች መሸሻቸውን ተናግረዋል።

በሁለቱ ጥቃቶች ጉዳት የደረሰባቸው ስምንት ሰዎች ሕክምና እየተከታተሉ እንደሆነ ምንጮቹ አክለዋል።

ትናንት [እሑድ] ሌሊት ላይም በዚሁ ሽርካ ወረዳ ቢያንስ ሁለት ነዋሪዎች እንደተገደሉ አንድ ነዋሪ እና አንድ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትናንቱ ጥቃት አዛውንት የሆኑ "ሁለት ወንድማማቾች ቤታቸው ውስጥ" እንደተገደሉ ገልጸዋል። ሌላ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው የተገደሉት "አምስት ሰዎች" ናቸው ብለዋል።

የመርቲ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ከሊል ገና ጥቃቱ መፈጸሙን ለቢቢሲ አረጋግጠው "ጥቃቱ ሃይማኖት ተኮር አይደለም" ብለዋል።

ከአራቱ ሟቾች ውስጥ አንዱ ሙስሊም መሆኑን የጠቀሱት አስተዳዳሪው፤ መጀመሪያ ጥቃት የተፈጸመው "ሙስሊሙ ነዋሪ ላይ እንደሆነ" ገልጸው "ሌሎቹ ሦስቱ ክርስቲያኖች የተገደሉት ሙስሊሙ ሲጠቃ በመከላከላቸው" መሆኑን ተናግረዋል።

አቶ ከሊል ጥቃቱን "ሸኔ" ሲሉ የጠሯቸው ታጣቂዎች እንደፈጸሙት ገልጸዋል። በተፈጸመው ጥቃት አራት ቤቶች እንደተቃጠሉ አክለል።

ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ወደ አካባቢው በመሰማራታቸው ዝርዝር መረጃ መስጠት እንደማይችሉ የገለጹት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ የፀጥታ ኃይሎች ከታጣቂዎች ጋር የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ቅዳሜ የካቲት 21/2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ በምሥራቅ አርሲ 21 "ንጹኃን ኦርቶዶክሳውያን በግፍ መገደላቸውን ፤ በሕይወት የተረፉትም ታግተው ያሉበትና የደረሱበት እንደማይታወቅ" ገልጾ ከ10 በላይ አባወራዎች ቤት እና ንብረት በቃጠሎ መውደሙን አስታውቋል።

ቋሚ ሲኖዶሱ በንጹኃን ላይ የተፈጸመው ግድያ "በሃይማኖት ስም" የተፈጸመ ነው ያለ ሲሆን "በሃይማኖት ስም ይፈጸሙት እንጂ የሃይማኖት ሰዎች ግን አይደሉም" ብሏል።

ሲኖዶሱ አክሎም ለረዥም ዘመናት ተከባብረው አብረው በኖሩት የሃይማኖት ተቋማት መካከል ግጭትን መፍጠር ዓላማው በማድረግ ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጿል።

"የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮችና ሕዝበ ክርስቲያኑ በጋራ ሊያወግዛቸው ይገባል" ሲልም አክሏል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እሑድ የካቲት 22/2018 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ "በንጹኃን የኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ወገኖቻችን ላይ በደረሰው አሰቃቂ አደጋ በእጅጉ አዝነናል" ብሏል።

ድርጊቱ የትኛውንም ሃይማኖት አይወክልም ያለው ጠቅላይ ምክር ቤቱ "ይልቁኑም በሃይማኖቶች መካከል ለዘመናት ያለውን የመከባበር እሴት በመናድ በአማኞች ሕዝቦች መካከል ጥርጣሬና ግጭት ለመፍጠር የተቀነባበረ እኩይ ሴራ ነው ብለን እናምናለን " ሲል ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ ደግሞ በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በተደጋጋሚ እየተፈጸመ ያለው ሞትና መፈናቀል "የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ጥቃቱ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል በነጻነት ሠርተው የመኖርና ሥርዓተ አምልኮ የመፈጸም ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጋፋ ነው" ብሏል።

የክልሉ መንግሥት እና የአካባቢው መስተዳደር "ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው" ያለው ቋሚ ሲኖዶስ ጥረቱን እንዲያጠናክር ወደፊትም ችግሩ እንዳይደገም ከመሠረቱ የሚፈታ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤም የተፈጸመውን ግድያ አውግዞ "ይህን ኢ-ሃይማኖታዊ እና ኢ-ሰብዓዊ እጅግ ዘግናኝ ተግባር የፈጸሙትን አካላት መንግሥት ተከታትሎ ለፍርድ እንዲያቀርብ" አሳስቧል።

ጉባኤው ባወጣው መግለጫ፤ መንግሥት "በአካባቢው የሚኖሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት በድጋሚ እንዳይፈጸም በቂ ጥበቃ እንዲያደርግ" ጠይቋል።

በተጨማሪም "ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ይህን ዘግናኝ ተግባር በአንድ ድምጽ እንዲቃወሙ" እንዲሁም "በአንድነት በመቆም ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጠር የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ" ጥሪ አቅርቧል።

በጥቅምት ወር በምሥራቅ አርሲ ዞን በጉና፣ በመርቲ፣ በሸርካ እና በሆሎንቆ ዋቤ ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ "ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች" በተፈጸሙ ጥቃቶች ሕጻናትን ጨምሮ 25 ሰዎች መገደላቸውን የተጎጂዎች ቤተሰቦች እና በአካባቢው የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የኦሮሚያ ክልል ስለተፈጸመው ግድያ እስካሁን ድረስ በይፋ ያሉት ነገር የለም።