ግብፅ እና ኤርትራ የቀይ ባሕር ጉዳይ የሚመለከተው "የጠረፉን አገራት ብቻ ነው" አሉ

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Foreign Affairs Media
ቀይ ባሕር ላይ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን እና የወደብ ትስስርን የተመለከተ ስምምነት የተፈራረሙት ግብፅ እና ኤርትራ፤ የቀይ ባሕር ጉዳይ የሚመለከተው "የቀይ ባሕር ጠረፍ አገራትን ብቻ" እንደሆነ ገለጹ።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባድር አብዲላቲ እና የግብፅ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሌተናንት ጄነራል ከማል አልዋዚር፤ ግንቦት 8 ቀን 2018 ዓ. ም. ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተወያይተዋል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባድር አብዲላቲ "የቀይ ባሕር አስተዳደር እና ደኅንነት ጉዳይ በዋነኛነት የሚመለከተው የቀይ ባሕር አጎራባች አገራትን ነው" ማለታቸውን መሥሪያ ቤታቸው አስታውቋል።
ቀይ ባሕርን ከሚያዋስኑ የባሕር ዳርቻ አገራት "ብሔራዊ ደኅንነት ጋር ቀጥተኛ ትስስር" እንዳለው በመጥቀስም "የቀይ ባሕር አጎራባች ያልሆነ አካል ቀይ ባሕርን በሚመለከቱ ጉዳዮች መግባት የለበትም" ማለታቸው ተገልጿል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ባድር አብዲላቲ "ኤርትራ ቀይ ባሕርን በማስተዳደር ረገድ ያላትን ዓላማ ግብፅ ትደግፋለች። ለቀይ ባሕር አጎራባች አገራት አንድነት እና ሉዓላዊነትም ዕውቅና ትሰጣለች"ብለዋል።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ሁለቱ አገራት የባሕር ላይ የትራንስፖርት ስምምነት የተፈራረሙት "በነጻነት የሚመራ የዓለም አቀፍ የባሕር ትራንስፖርት እንቅስቃሴን መርሕ መሠረት በማድረግ በዘርፉ ትብብርን ለማጠናከር" እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የኤርትራ የትራንስፖርት እና ኮምንኬሽን ሚኒስትር አቶ ብርሃነ ተስፋሥላሴ ከግብፅ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሌተናንት ጄነራል ኢ/ር ከማል አልዋዚር ጋር ስምምነቱን ፈርመዋል።
የግብፅ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሌተናንት ጄነራል ከማል አልዋዚር፤ ካይሮ የአሥመራን የወደብ እና የባሕር ትራንስፖርት ልማት መደገፍ ትሻለች ማለታቸው ተገልጿል።
በባሕር ትራንስፖርት ዘርፍ እና በቀይ ባሕር በኩል የግብፅ እና ኤርትራን ወደቦችን የሚያስተሳስረውን የካርጎ እንቅስቃሴ በተመለከተ የተደረሱትን ስምምነቶችም አሞካሽተዋል።
ሁለቱ አገራት በጋራ "ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙርያ" መወያየታቸውም ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከግብፅ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ባደረጉበት መድረክ ላይ በትራንስፖርት፣ ኢነርጂ እና ማዕድን ቁፋሮ ዘርፍ የተሰማሩ የግብፅ ኩባንያዎች ኃላፊዎች መገኘታቸው ተዘግቧል።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ በሁለቱ አገራት ባለሥልጣኖች መካከል የተደረጉ ውይይቶች "የጋራ ጠቀሜታ ባላቸው ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉን አቀፍ የሁለትዮሽ ትስስር ማሳደግን" የተመለከቱ ናቸው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ "በኤርትራ እና ግብፅ መካከል ሁሉን አቀፍ ትስስር ማጠናከር ለሁለቱም አገራት ዜጎች የጋራ ጥቅም የሚያስከብር መሆኑን አስምረውበታል" ሲሉም የማስታወቂያ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ኤርትራ ከግብፅ የንግድ ተቋማት ጋር "የጋራ ፕሮጀክቶች ላይ ለመሳተፍ" ዝግጁ መሆኗንም ጠቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, @hawelti
ከኤርትራ እና ከግብፅ በኩልም የወጡ መግለጫዎች የካይሮ ባለሥልጣናትን ጉብኝት "የሁለቱ አገራት የወንድማማችነት ትስስር እና ትብብር ማሳያ" በማለት ነው የገለጹት።
ሁለቱ አገራት "የንግድ እና የምጣኔ ሃብት ትስስርን" ማጠናከር እንደሚሹም ተመልክቷል።
ያለፈው ዓመት መባቻ ላይ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ካይሮ ማቅናታቸው ይታወሳል።
ከኢትዮጵያ ጋር በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የምትወዛገበው ግብፅ ከአሥመራ ጋር ያላትን ግንኙነት እያጠናከረች መጥታለች።
ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ፍላጎቷን በተደጋጋሚ መግለጿን ስትቀጥል፤ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነትም ውጥረት አጥልቶበታል።
በሌላ በኩል በኢራን ጦርነት ምክንያት የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት ያሳሰባት አሜሪካ የኤርትራን ማዕቀቦች እንደምታነሳ ተገልጿል። ይህም ኤርትራን የቀይ ባሕር ስትራቴጂያዊ አጋር የማድረግ አካል እንደሆነ ይታመናል። አሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ የተጣለውን የመሣሪያ ማዕቀብም አንስታለች።
ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ ጋር "የመከላከያ ትብብር" የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ምክክር ማዕቀፍ ስምምነት የተፈራረሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጤሞቲዮስ፤ በዋሽንግተን ቆይታቸው ስለ ሕዳሴ ግድብ እና ቀይ ባሕር መነጋገራቸው አይዘነጋም።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ኤርትራ "ሉዓላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን እንድትጠብቅ" ካይሮ ድጋፍ ታደርጋለች።
ግብፅ በሱዳን እና ሶማሊያ ደኅንነት እና መረጋጋት እንዲሰፍን እንደምትሻ እና ጉዳዩ "የግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት ተቀጥላ" እንደሆነ ተገልጿል።
በተጨማሪም ሁለቱ አገራት የምጣኔ ሃብት እና የንግድ ትስስራቸውን ከሚያጠናክሩባቸው ዘርፎች መካከል የማዕድን፣ የትራንስፖርት፣ የመድኃኒት አቅርቦት እና የዓሣ ምርት ተጠቅሰዋል።














