ኤአይ የሚሰጣቸው ፈጣን ምላሾች የሰው ልጅን የማሰብ አቅም ሊያዳክሙ እንደሚችሉ ባለሙያዎች አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለጥያቄዎች እና ውስብስብ ችግሮች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) መተግበሪያዎች እየበዙ መምጣታቸው የሰው ልጅን የማሰብ አቅም ሊያዳክሙ እንደሚችሉ 'ሮያል ኦብዘርቫቶሪ ግሪንዊች' የተባለው ተቋም አስጠነቀቀ።
ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ከሚገኙ ለሳይንሳዊ ዓላማ የተቋቋሙ ጥንታዊ ተቋማት አንዱ የሆነው ኦብዘርቫቶሪው፤ ለሥነ ፈለክ (አስትሮኖሚ) ምርምር ባበረከተው አስተዋፅኦ ይታወቃል።
ኦብዘርቫቶሪውን የሚቆጣጠረው 'ሮያል ሙዚየም ግሪንዊች' ዳይሬክተር የሆኑት ፓዲ ሮጀርስ፤ ተቋሙ ያለው ከፍተኛ የምርምር ታሪክ የሰው ልጅ እውቀት እና ጠያቂነት ምን ያህል ኃይል እንዳለው እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
ኤአይ ላይ የሚኖር "ሙሉ በሙሉ የሆነ ጥገኝነትን" ማስወገድ እንደሚገባም የተቋሙ የምርምር ታሪክ እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
"በፍጥነት የሚመጡ መልሶች ላይ በብቸኝት መተማመን ለእውቀት፣ ሙያዊ ብቃት እና ፈጠራ መሠረት የሆኑት የመጠየቅ እና የመመርመር ልምዶች እንዲጠፉ የማድረግ አደጋ አለው" ብለዋል።
ዳይሬክተሩ፤ ሥነ ፈለክ ላይ የተመዘገቡ ግኝቶች ያለ ቴክኖሎጂ ሊታሰቡ የሚችሉ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ። ነገር ግን ያለ ጥያቄ እና በራስ ጥረት ለጥያዌዎች መልስ ለማግኘት ከሚደረግ ሙከራ ውጪ እንዳልተገኙ ገልጸዋል።
የሰው ልጅ ለጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የሚያደርጋቸው ጥረቶች ያልተጠበቀ መረጃ ላይ እንዲደርስ እንደሚያደርጉት የሚናገሩት ሮጀርስ፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ሥርዓት የሚሰጣቸው ፈጣን ምላሾች ግን ይህንን እንደሚያስቀሩ አብራርተዋል።
ቀደምት የከዋክብት አጥኚዎች "ስለ ሰማያት ያከማቿቸው ከፍተኛ መጠን ያላቸው መረጃዎች ኋላላይ እነርሱ አስበው ለማያውቋቸው ጉዳዮች እንዳገለገሉ" ገልጸዋል።
"ማሽን የማያከናውናቸውን" ተግባራት መሥራት የቀድሞ ተመራማሪዎች የሥራ አካል እንደነበረም ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"የሰው ልጆች ሠርተውታል፤ ከጻፉት ከ150 ዓመታት በኋላ ሰዎች ምድር ላይ የሚደረግ ጉዞ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ ብለው የገመቷቸውን ነገሮች ለማረጋገጥ የሚጠቅም ትልቅ ሀብት ሆኗል" ብለዋል።
በጽሑፍ፣ ምሥል፣ ቪዲዮ ወይም በድምጽ ለሚቀርቡላቸው ውስብስ ትዕዛዞች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ የኤአይ መገልገያዎች በፍጥነት ማደጋቸውን ቀጥለዋል።
ቀላል ረዳት የነበሩት የኤአይ ቻትቦቶች ሰዎች በርካታ ነገሮች የሚያዋዩአቸው ወዳጆች ሆነዋል። ምሥል የሚሠሩ የኤአይ መገልገያዎች በአደገኛ ፍጥነት እውነተኛ የሚመስሉ ምሥሎችን መሥራት ጀምረዋል።
አዳዲስ እና የላቁ የኤአይ ሞዴሎች ለአሥርት ዓመታት የቆዩ መተግበሪያዎች ውስጥ ያሉ ስህተቶችን ማውጣታቸው እየተነገረ ነው።
በእኩል መጠን ሙገሳ እና ትችት እያስተናገደ ያለው ይህ የቴክኖሎጂ እድገት፤ ስላሉበት ውስንነቶች እና በኤአይ ላይ ብቻ መተማመን በተጠቃሚዎች ላይ ስለሚያስከትለው አደጋ የሚያስጠነቅቁ ማሳሰቢያዎች እየወጡ ነው።
ሮጀር እንደሚናገሩት ከዚህ ቀደም የነበሩት እንደ ዊኪፒዲያ ያሉ መገልገያዎች "ፍላጎቱ ያላቸው ሰዎች ወደ ዋናዎቹ የመረጃው ምንጮች መሄድ እና ማረጋገጥ" ያስችሉ እንደነበር ያስረዳሉ። ሰዎች ይህንን በማድረግ "መረጃው እምነት የሚጣልበት መሆን አለመሆኑን መመልከት ይችሉ እንደነበር" ይናገራሉ።
የኤአይ መገልገያዎች ይህንን እንደሚያስቀሩ የሚገልጹት ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ምክንያት ሰዎች መረጃዎችን በራሳቸውን የመመርመር ልምዳቸው እንደሚቀንስ ጠቁመዋል።














