ነጻ አውጪዎችን ለመደገፍ ከደቡብ ሱዳን እስከ ፍልስጤም የተጓዙት ኢትዮጵያዊ

ዶ/ር ሰይፈ ታደለ

የፎቶው ባለመብት, tadele

የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ሰይፈ ታደለ

"የሰው ልጅ ከግለኝነት ነፃ የሆነ ባህሪ ተላብሶ፣ ለሌሎች መትረፍ አለበት" የሚለው የዘወትር እምነታቸውና መለያቸው ነው።

በዚህ መሰሉ መርሃቸውም፣ ገና በወጣትነት ዘመናቸው ከአገራቸው አልፈው ለሌሎች ሕዝቦች የፀረ ጭቆና ትግል ደጋፊ ሆነው፣ በ1980ዎቹ ለነፃነታቸው ሲፋለሙ ከነበሩት ደቡብ ሱዳናውያን እና ዘመናቸውን ሁሉ በትግል እያሳለፉ ካሉት ፍልስጤማውያን ጎን ተሰልፈዋል።

ለዚህ ውሳኔያቸው እና እምነታቸው፣ እንደነ ቼ ጉቬራ ያሉ የቀደሙ ዓለም አቀፍ ድንበር የለሽ የነፃነት ትግል አቀጣጣዮች ተፅዕኖ አሳድረውባቸው እንደሆነ በቢቢሲ የተጠየቁት ዶ/ር ሰይፈ ታደለ፣ "ቼ ጉቬራን ልሁን ብዬ አላውቅም፣ ቼ ጉቬራን የመሆን ሕልምም አልነበረኝም" ይላሉ።

ይልቁንም፣ ከልጅነታቸው ጀምሮ በአገር ውስጥ ሲያዩት የኖሩት የድህነት እና የሰቆቃ ሕይወት፣ በሂደት ጭቆናን በማንኛውም መልኩ ለመፋለም እንዳነሳሳቸው ይናገራሉ።

ግራ የመጋባት ዘመን

የአፄ ኃይለሥላሴ ሥርዓት ሊወድቅ አንድ ዓመት ሲቀረው በአዲስ አበባ፣ ፊት በር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው የተወለዱት። ከሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ያለውና፣ አሁን ወዳጅነት ፓርክ የተሠራበት አካባቢ የልጅነት ዓለማቸውን አሳልፈውበታል።

አብዛኛው የልጅነት እና የወጣነት ዕድሜያቸውን በደርግ ዘመን እንደኖሩት ተናግረው፣ በወቅቱ የነበረውን አስከፊ ችግር እየተመለከቱ ማደጋቸውን አውስተዋል።

"በቤተሰብ ደረጃ ከጥሩ ኑሮ ወደ ታችኛው እርከን ያሽቆለቆልንበት፣ ኑሯችን የተናጋበት ወቅት ላይ ነበርን። የከፋ የድህነት መልክ የሚታይበት፣ የመጨረሻው የኑሮ ጥግ ላይ የነበሩ ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ ውስጥ ነው የኖርኩት። በቤታችን ውስጥ አየው የነበረው ሁኔታ አስከፊ ነበር። ወቅቱ ስለ ረሀብ የሚወራበት፣ ብዙ ሕዝብ ከገጠር ወደ ከተሞች የሚፈልስበት፣ ሩዝ የሚባል ምግብ በእርዳታ የሚታደልበት ወቅት ነበረ። በጣም መሠረታዊ የሚባሉት ሸቀጦችን ማግኘት ቅንጦት የሆነበት፣ ክብሪትና ሳሙና ሳይቀር በኮታ ከቀበሌ በሰልፍ የሚታደልበት ጊዜ ነበር" ይላሉ።

"ዳቦ በቁጥር ነበር የሚሰጠው፣ በሰልፍ ነው የሚገኘው፣ ወተት አይታሰብም" በማለትም ያወሳሉ።

ከድህነቱ ባሻገር፣ የጭቆናው ስፋት እና ጥልቀትም እንዲሁ እረፍት የሚሰጥ አልነበረም።

"ጭቆናውም ድህነቱም ነፍሴን ያስጨንቃት ነበር። ይህ ተገቢ የሰው ልጅ የኑሮ ደረጃ አይደለም እላለሁ። የተሻለ ሕይወት የምለው የማወዳድርበት እውቀቱ እና ተጋላጭነቱ ባይኖረኝም፣ ያን የመሰለ አስቀያሚ ሕይወት ለሁላችንም አይበጅም የሚል ድምዳሜ ላይ ግን ደርሻለሁ። ይህ በደመ ነፍስ የመጣ የፀረ-ጭቆና ስሜት ነው" ሲሉም ያክላሉ።

"በ1980ዎቹ የተነሳኋቸውን ፎቶዎች ስመለከት፣ በወቅቱ በኢትዮጵያ የነበረው የተሳከረ ሁኔታ፣ ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ብሎም ማኅበራዊ ቀውስ፣ ስር የሰደደ ድህነት፣ ፖለቲካዊ ውጥረት፣ ዕረፍት የሚነሳ ጭቆና እና አስከፊ ሕይወት ድቅን ይሉብኛል" የሚሉት ዶ/ር ሰይፈ፣ በእነዚህ መልኮች የገለጹትን ወቅትም "ግራ የመጋባት ዘመን" ይሉታል።

ይህም፣ ገና በለጋ ዕድሜያቸው ወደ ትግሉ ዓለም እንዲቀላቀሉ ሳይገፋፋቸው አልቀረም።

⁠ዶ/ር ሰይፈ እና ጓዶቻቸው

የፎቶው ባለመብት, tadele

የምስሉ መግለጫ, ⁠ዶ/ር ሰይፈ እና ጓዶቻቸው በ 1987 ዓ.ም የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎችን ለመቀላቀል ሲዘጋጁ

የወጣትነት ፖለቲካዊ ተሳትፎ፣ እስር እና መከራ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባለታሪኩ እንደሚሉት በ1979 አካባቢ የደርግ ሥርዓት መናጋት የጀመረበት ወቅት ነበር።

"አገራችንን እንለውጣለን" የሚል እምነት የነበራቸው የኢህአፓና የመኢሶን ሰዎች በደርግ ታስረው፣ አልያም ተገድለው፣ ካልሆነም ከአገር ተሰደው በጥቅሉ ከነበሩበት ተጠራርገው የጠፉበት፣ ሕዝቡም በግራ መጋባት ስሜት ውስጥ የነበረበት ዘመን ነው።

በዚህ ጊዜ ዶ/ር ሰይፈ በ16 ዓመታቸው ኢሕዲህ (የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ኅብረት) ወደሚባል ድርጅት ተቀላቀሉ።

"እኔ ባግባቡ ሳላውቀው ነው ዶ/ር ሃይማኖት በምትባል ሰው አማካኝነት የተመለመልኩት። የድርጅቱን ሰዎች፣ ሳር ቤት አካባቢ ሔጄ አገኘኋቸው እና መጽሐፍ ሰጡኝ። ከዚያ በኋላ ግን በመደበኛነት መገናኘት ጀመርን። ያኔ የ8ኛ ወይም የ9ኛ ክፍል ተማሪ ነው የነበርኩት" ብለዋል።

እነሱ ገና ልጆች ቢሆኑም፣ መልማዮቻቸው ግን ለሆነ ተልዕኮ እንዳዘጋጁዋቸው ያስታውሳሉ።

"ከዚህ ጀርባ የነበሩት ዋናዎቹ የድርጅቱ ሰዎች ከትግራይ እና ከኤርትራ ሳይሆኑ አይቀሩም" የሚሉት ዶ/ር ሰይፈ፣ የተሰጣቸው ተልዕኮም ከአንድ የደርግ የደኅንነት ባለሥልጣን ቤት የተለያዩ መረጃዎች የያዙ ሰነዶችን ማውጣት ነበር።

እሳቸው እና ጓዶቻቸው ይህንን ተልዕኮ በሚገባ ፈጸሙ፣ ዳጎስ ያለ ገንዘብም ተከፈላቸው። በእሳቸው አገላለጽ፣ "ከዚያ በፊት አይተውትም አግኝተውትም የማያውቁት የገንዘብ መጠን" ነበር።

እሳቸውና ጓዶቻቸው ይህን ተልዕኮ ፈፅመው በሰላም የሰነበቱበት ጊዜ ግን አጭር ነበር። ግዳጃቸውን በተወጡ በጥቂት ጊዜ ውስጥ፣ የተልዕኮው አቀነባባሪዎች እና ፈፃሚዎች በደርግ የደኅንነት ሰዎች ከያሉበት ተለቅመው ማዕከላዊ ገቡ፣ ከዚያም ወደ ዓለም በቃኝ እስር ቤት ተወረወሩ።

እዚያም በብዙ ስቃይ እና መከራ የታጀቡ አራት የእስር ዓመታትን አሳለፉ።

"እግራችን በሰንሰለት ታስሮ ነው የኖርነው።ካራቴ ስለሚሠሩ ዘለው ይጠፋሉ ተብለን ነው በሰንሰለት የታሰርነው። መፀዳጃ ቤት ስንሔድ ብቻ ነበር የሚፈቱልን" ብለዋል፣ የእስር ቤት ቆይታቸውን ሲያስታውሱ።

ዶ/ር ሰይፈ፣ በ16 ዓመታቸው ወደ ፍልውሃ እየወሰደች ሻይ እና ጭማቂ ትጋበዛቸው የነበረችው እና የፖለቲካ ድርጅት እንዲቀላቀሉ መንገዱን ያሳየቻቸው ዶ/ር ሃይማኖትን ከዓመታት በኋላ በዓለም በቃኝ እስር ቤት አገኙዋት።

ከእስር ቤቱ በሕይወት ስለመውጣቷ ግን የሚያውቁት ነገር የለም። የእሷን መጨረሻ ባያዩም ግን፣ በርካቶች መረሸናቸውን ሰምተዋል።

አብረዋቸው ወደ ማዕከላዊ ከገቡት ሀያ ሰባት ወጣቶች መካከልም፣ ሀያ አንዱ ተገድለዋል። እሳቸውም ሞት ተፈርዶባቸው፣ ቀናቸውን ሲጠብቁ ነበር ደርግ ሊወድቅ አካባቢ በምህረት የተለቀቁት።

ዶ/ር ሰይፈ ታደለ ከተለያዩ አገራት ሰዎች ጋር

የፎቶው ባለመብት, tadele

የምስሉ መግለጫ, ⁠ዶ/ር ሰይፈ ታደለ ከጓዶቻቸው እና ከደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪዎች ጋር

የደቡብ ሱዳን ትግልን የመቀላቀል ሀሳብ

የዶ/ር ሰይፉ ታደለ ዓለም አቀፋዊ የፀረ-ጭቆና ትግል ጅማሬ የመጣው ከደርግ ውድቀት ማግስት ነበር። በዚህ ወቅት ከእስር ቤት እንደወጡ፣ በቄራዎች ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው መሥራት ጀመሩ። በመብት ተሟጋችነት ሲሠሩ ከነበሩት ከእነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ጋርም ተገናኙ።

በዚህ መሀል ነበር ዶ/ር ሰይፈ ወርልድ ፌደሬሽን ዲሞክራቲክ ዩዝ ከተሰኘ የዓለም ወጣቶች ፌደሬሽን አባላት ጋር በመተዋወቅ ወደ ውጭ የመሔድ ዕድል አገኙ።

ይህን ዕድል በመጠቀምም፣ ወደ ፖርቹጋል አቅንተው በድርጅቱ ጉባኤ በተሳተፉበት ጊዜ ዶ/ር ሰይፈ የድርጅቱ የቁጥጥር ኮሚሽን አባል ሆነው ተመረጡ። ከፖርቹጋሉ የዓለም ወጣቶች ፌደሬሽን ጉባኤ በኋላ፣ ከባልደረቦቻቸው ጋራ ሆነው የዓለም የፀረ-ጭቆና ትግልን መቀላቀል የሚለውን ሀሳብ አመጡ። ትግላቸውንም የደቡብ ሱዳን የነፃነት ታጋዮችን በመቀላቀል እንደሚጀምሩ ተስማሙ።

"እኔ፣ አንድ ፈረንሳዊ፣ አንዲት ደቡብ አፍሪካዊት እና አንዲት ሕንዳዊት ሆነን ይህን ሀሳብ አነሳን፣ እንቅስቃሴም ጀመርን። ቀጠሮ ይዘንም የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ግንባር መሪ ጆን ጋራንግ ጽህፈት ቤት ወደሚገኝበት ኬንያ ናይሮቢ አመራን። ድርጅታችን ግራዘመም፣ ፀረ ኢምፔርያሊስት እና ፀረ-ኮሎኒያሊስት እንደሆነ ሰውየው በደንብ ያውቁታል" ብለዋል ዶ/ር ሰይፈ፡፡

ከጆን ጋራንግ ፈቃድ ካገኙ በኋላም፣ ከናይሮቢ ኬንያ ግማሹን መንገድ በጭነት መኪና፣ የተወሰነውን ደግሞ በፒክአፕ ተጉዘው ከዋና ከተማዋ ጁባ 100 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ ከሚገኝ የጦር ሰፈር ደረሱ።

"በሌላ መስመር ግን በርካታ የሌሎች አገራት ተወላጆች የነበሩባቸው ወደ ደቡብ ሱዳን የዘመቱ ቡድኖች ነበሩ። እዚያ እንደደረስን እንደ ታጋዮቹ ሆነን ነበር የምንኖረው" በማለት በጫካ ውስጥ የነበረውን ፈታኝ ሕይወት ዶ/ር ሰይፈ ያስታውሳሉ። ጦርነት በሚደረግበት ወቅት አንዳንዴ የአውሮፕላን ድብደባ እና ውጊያ ያጋጥማቸው ነበር።

የቡድኑ አባላት ተግባር በወታደራዊ ክንፉ ውስጥ ከሠራዊቱ ጋር ተሰልፈው መዋጋት ሳይሆን፣ የፖለቲካዊ ትግሉ አካል ነበሩ። በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለ ትግሉ ዓላማ ፖለቲካዊ ግንዛቤ መፍጠር ነበር ዋና ግባቸው። "ትግሉ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ስለነበረ ሕዝቡ በእጅጉ ተሰላችቶ ነበር። በየሄድንበት የሚያነሱት ጥያቄ የምግብ ነው። 'ምግብ እንጂ ፖለቲካ አንፈልግም' በማለት በአብዛኛው ምግብ እንድንሰጣቸው ነበር የሚጠብቁን" በማለት የሕዝቡ ዋነኛው ፍላጎት ማኅበራዊ አገልግሎት እና እንደ ሰው ተከብሮ መኖር እንደነበር ያስታውሳሉ።

የደቡብ ሱዳን የመገንጠል ጉዳይ "የፖለቲከኞቹ ፍላጎት ነበር። የሕዝቡ እና የፖለቲከኞቹ ፍላጎት ለየቅል ነበረ" የሚሉት ዶ/ር ሰይፈ፤ "የደቡብ ሱዳን ነፃነት ንቅናቄ መሪ ጆን ጋራንግ የመገንጠል አቀንቃኝ አልነበረም፤ ፍላጎቱ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ራስገዝ ሆኖ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ፣ ሀብቱን ከሰሜኑ ጋር እኩል እየተጠቀመ አብሮ መኖር አለበት የሚል ነበር፡፡ የእኛም ፍላጎት የነበረው ይኸው ነበር" ሲሉ ያክላሉ።

በመጨረሻ ግን የደቡብ ሱዳን ትግል ፖለቲከኞቹ ባቀዱት እንጂ እነሱ በተመኙት መንገድ አልተጓዘም። ያ የበርካታ ሺዎችን ሕይወት የቀጠፈው እና ሚሊዮኖችን ያፈናቀለው የረዥም ዘመኑ የትጥቅ ትግል የተቋጨው በአውሮፓውያኑ 2011 በደቡብ ሱዳን አገር መሆን ነበረ።

⁠ዶ/ር ሰይፈ ታደለ ከጓዶቻቸው እና ከደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪዎች ጋር

የፎቶው ባለመብት, tadele

የምስሉ መግለጫ, ⁠ዶ/ር ሰይፈ ታደለ ከጓዶቻቸው እና ከደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪዎች ጋር

በፍልስጤም ድንጋይ አልወረወርኩም

"ቀጣዩ የትግል ተሳትፏችን ራማላህ፣ ፍልስጤም ላይ ነበረ" በማለት ቀጣዩ ዓለም አቀፋዊ ትግላቸው የትና ምን ይመስል እንደነበር ያብራሩት ዶ/ር ሰይፈ፣ ግጭት ወደማይለየውና የዓለምን ትኩረት ወደሚስበው የመካከለኛው ምሥራቅ ቀጣና የመዝመቱ ሃሳብ የተጠነሰሰው በዚያው በዓለም የወጣቶች ፌደሬሽን ውስጥ እንደነበር ተናግረዋል።

በፌደሬሽኑ አመራር ውስጥ ፍልስጤማውያንም ስለነበሩበት እነሱ ስለማያባራው የሕዝባቸው ትግል እና የበርካቶች እልቂት መንስኤ ስለሆነው የእስራኤል እና የፍልስጤማውያን ግጭት ያስረዱዋቸው ዶ/ር ሰይፈ እና ሌሎች ወጣቶች ትግሉን ለማገዝ ወደ ፍልስጤም ተጓዙ።

"ከልጅነቴ አንስቶ የእስራኤል አምላክ እየተባለ በሚፀለይበት አገር ባድግም፣ ፍልስጤማውያን በጣም የተጨቆኑ ሰዎች ናቸው ብዬ አምን ስለነበር ከእነሱ ጎን ተሰልፌ ታግያለሁ። ሰው እንዴት ያለ አገር ይኖራል? ብዬ እጠይቅ ነበር። ይህም ነው የእነሱን ትግል እንድደግፍ ያነሳሳኝ። ማንም በገንዘብ አልደገፈኝም፣ የራሴን ገንዘብ አጠራቅሜ ነው ወደዚያ የሄድኩት።"

በቆይታቸው "ኢንትፋዳው (የፍልስጤማውያን የአመፅ ትግል) ላይ ሁለቴ ተሳትፌያለሁ። ከእነሱ ጋር ወደ አደባባዮች በመውጣት ድንጋይ ሲወረውሩ፤ አስለቃሽ ጭስ ሲተኮስባቸው አብሬ ነበርኩ" የሚሉት ዶ/ር ሰይፈ፣ በዚህም ድጋፋቸውን ለማሳየት እና ከጎናቸው መሆናቸውን አሳይተዋል።

በፍልስጤም ግዛት ውስጥ የነበራቸው ቆይታም ቤት ለቤት እየዞሩ ከተመደቡላቸው ቤተሰቦች ጋር ውይይት ያደርጉ ነበር። "በቆይታዬ ሰባት ቤተሰቦችን ጎብኝቻለሁ። እስከ ሦስት ቀናት ከተመደበልን ቤተሰብ ጋር እናድራለን። እየዞርን ስለትግሉ እናስተምራለን፣ ሞራላዊ ድጋፍም እንሰጥ ነበር። በተጨማሪም ዓለም ትግላቸውን እንዴት እንደሚገነዘበው በመንገር ብቻቸውን እንዳልሆኑ እናሳውቃቸዋለን" ይላሉ ዶ/ር ሰይፈ።

በዚህ ድንበር፣ ዘር እና ቀለም ሳይገድባቸው፣ ለተጨቆኑ ሕዝቦች ድምፅ በመሆን፣ ስቃያቸውን በመጋራት፣ በአካል ከጎናቸው ተሰልፈው አጋርነታቸውን በማሳየታቸው እርካታ ይሰማቸዋል።

"በስቃያቸው ጊዜ ከጎናቸው ቆሜ ኃላፊነቴን ተወጥቻለሁ። ከዚህ በኋላ ብሞትም አይቆጨኝም፡፡ ሁሌም ለሰው ልጆች መትረፍ አለብኝ የሚል ፅኑ እምነት አለኝ" ይላሉ ዶ/ር ሰይፈ።

ዶ/ር ሰይፈ ታደለ ኪዳኔ፣ በአሁኑ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ፣ ጆሀንስበርግ ዩኒቨርሲቲ፣ የአንድ የጥናት ማዕከል ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ሲሆኑ በተለያዩ አርዕስቶች ስድስት መፃህፍትን ፅፈዋል።