ስለሶማሊላንድ ዕውቅና በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ምን ይላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Embassy in Mogadishu, Somalia
ኢትዮጵያ እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችውን ዕውቅና በቅርበት እየተከታተለችው መሆኑን በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ እንደ ሉዓላዊ አገር ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘት ስትጥር የነበረችው ሶማሊላንድ ከሳምንት በፊት ከእስራኤል የመጀመሪያውን ዕውቅና አግኝታለች።
የተለያዩ የዓለም አገራት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የአረብ ሊግ የእስራኤልን ዕውቅና በማውገዝ ከሶማሊያ የግዛት አንድነት ጎን አንደሚቆሙ አሳውቀዋል።
በሶማሊያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ሱሌይማን ደደፎ ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ወቅት "ስለ እስራኤል ዕውቅና ምንም ዓይነት መረጃ አልነበረንም" በማለት ከቀሪው ዓለም ጋር ዜናውን እንደሰሙ በመግለጽ ስለጉዳዩ ኢትዮጵያ እንደማታውቅ ተናግረዋል።
በአፍሪካ ቀንድ የኃያላን አገራት ፉክክር እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት አምባሳደሩ የአገራት ነጻነት እና ሰላም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።
እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው እውቅና ሶማሊያን ጨምሮ የተለያዩ የዓለም አገራት አውግዘውታል።
እስራኤል በበኩሏ በውሳኔዋ እንደምትፀና ገልጻለች።
ኢትዮጵያ ሶማሊላንድ ስላገኘችው የአገርነት ዕውቅና እስካሁን ድረስ ምንም ያለችው ነገር የለም። የአገሪቱ ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃንም ስለጉዳዩ የዘገቡት ነገር የለም።
በዚህ ጉዳይ ላይ ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ለአምባሳደሩ ያቀረበላቸውን ጥያቄ ሲመልሱ "ይህ ወደፊት የምናየው ጉዳይ ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ በእስራኤል ዕውቅና ትስማማ እንደሆን ሲጠየቁ "እስራኤል ስለያዘችው አቋም ምንም ዕውቅናው አልነበረንም። በዚህ ጉዳይ ላይም ዝም ያልን ብቸኛ አገርም አይደለንም" ሲሉ መልሰዋል።
"እስካሁን ድረስ በርካታ ዓለም አገራት ታላቅ ጥረት ማድረጋቸውን አይተናል። እኛን ብቻ ለምን ትኩረት አድርገው ይጠይቁናል። ጎረቤት አገራት ብቻ አይደሉም፤ ሌሎች አገራትም አሉ። ስለዚህ ምንም የሚጠየቅ ነገር የለም። ለሁሉም ነገር የወደፊቱን ነው የምናየው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ መቼ አቋሟን እንደምታሳውቅ የተጠየቁት አምባሳደሩ "ቀጠሮ የለንም። የተቆረጠ ቀን የለም። አቋም ወስደናል፤ ያ ደግሞ አቋማችን ነው፤ ምን እንደሚሆን እንከታተላለን" ሲሉ መልሰዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ መካከል የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን ስምምነቱ ምን ደረጃ ላይ አንደሚገኝ ሁለቱም መንግሥታት ሲናገሩ አይሰማም።
በወቅቱ ሶማሊያ በስምምነቱ ተቆጥታ የነበረ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ባላንጣ ከሆኑት ከግብፅ እና ኤርትራ ጋር ያላትን ወዳጅነት በማጠናከር የተለያዩ የትብብር ሰምምነቶችን ተፈራርማለች።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት ለባሕር ኃይል የሚውል 20 ኪሎ ሜትር የሚረዝም የባሕር ጠረፍ ማግኘት የሚያስችላት ነበር።
በምላሹ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ለመስጠት መስማማቷ ቢነገርም ይህ ስምምነት ግን በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በይፋ አልተገለጸም።
ሶማሊላንድን እንደ ግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥራት ሞቃዲሾ በበኩሏ ስምምነቱን ተቃውማ ሉዓላዊነቷን የሚጥስ መሆኑን ገልጻለች።
ሁለቱ አገራት ወደ ወታደራዊ ፍጥጫ ይገባሉ ተብሎ በሚፈራበት ወቅት ነው ቱርክ ጣልቃ በመግባት ስምምነት እንዲፈራረሙ ያደረገችው።
አለመግባባቱን ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያን አምባሳደር አስወጥታ ከቆየች በኋላ ግንኙነቸታው ሲሻሳል ሱሌይማን ደደፎ አምባሳደር ሆነው መሾማቸው ይታወቃል።
"አሁን ከሶማሊያ ጋር ምንም ችግር የለብንም፤ በሰላም እየሠራን ነው" ሲሉ በአሁኑ ወቅት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በአንካራ የፈረሙት ስምምነት ኢትዮጵያ በሶማሊያ አስተማማኝ፣ ደኅንንቱ የተጠበቀ ለንግድ አገልግሎት የሚውል ወደብ በሊዝ እንድታገኝ የሚያስችል ነው።
ቢቢሲ ለአምባሳደር ሱሌይማን ይህ ስምምነት የት እንደደረሰ ጠይቋቸው ሲመልሱ "ወደፊት የተራመደ ነገር የለም" ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ተገልላ እድትቀር አንፈልግም" የሚሉት አምባሳደር ሱሌይማን "በቀጠናው ያሉ አገራትን ጠቅላይነት አንቀበልም" በማለት መንግሥት የባሕር በር ለማግኘት ሰላማዊ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
"ኢትዮጵያ የባሕር በር ስታገኝ የሚጎዳ አንድም አገር የለም። የማግኘት መብት አለን።"
ሌሎቹ ቀይ ባሕር ላይ "ክንዳቸውን ለማሳየት እየተረባረቡ ነው" ያሉት አምባሳደር ሱሌይማን "ቀይ ባሕር የእኛ ነው። የኛ ምርጫ ሁሌም ሰላማዊ መንገድ ነው" ብለዋል።
ይህ የማይሆን ከሆነስ ተብለው የተጠየቁት በቀጥታ ወደ ጦርነት ስለመግባት ባይናገሩም "ይህን የሚያህል አገር ታፍኖ ተዘግቶ ይቀመጣል ማለት አንዳልሆነ" አመላክተዋል።















