ኤርትራ የሶማሊላንድ እውቅናን በተለመከተ የፀጥታው ምክር ቤት የማያሻማ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል አለች

የፎቶው ባለመብት, MOI ERITREA
ቤንያሚን ኔታኒያሁ ሀገራቸው እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠታቸውን ተከትሎ የኤርትራ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የማያሻማ ምላሽ እንዲሰጠ ጠይቋል።
የኤርትራ ማስታወቂ ሚኒስቴር በለቀቀው አጭር መግለጫ “ተውኔቱ ምስጢራዊ አይደለም ሲብላላ የቆየ እንጂ” ብሎ “አደገኛ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ቀውስ እና መረበሽ” ይዞ ይመጣል ሲል አስጠንቅቋል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረ መስቀል የመንግሥታቸውን መግለጫ በኤክስ ገፃቸው አጋርተው የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የማያሻማ ምላሽ ሊሰጡት እንደሚገባ አስምረዋል።
መግለጫው “በተለይ ‘ከታይዋን’ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ያለውን ጉዳይ ከግምት በማስገባት ቻይና ትልቅ ኃላፊነት ልትወጣ እንደሚገባ” ገልጿል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መቃቃር ውስጥ የገባው የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝ ከሶማሊያ እና ግብፅ ጋር ልዩ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እንደደረሰ ይታወሳል።
አርብ ዕለት የተሰማውን የሶማሊላንድ እውቅና ዜና ተከትሎ በርካታ የአረብ እና የአፍሪካ ሀገራት የእስራኤልን ውሳኔ እንደሚቃወሙ የሚገልፁ መግለጫዎች አውጥተዋል።









