ለሶማሊላንድ ዕውቅና የምትሰጥ ሁለተኛዋ ሀገር ማን ልትሆን ትችላለች?

የሶማሊላንዱ ፕሬዝደንት ኢሮ ከእስራኤሉ ጠ/ሚ ኔታኒያሁ ጋር በቪድዮ ሲነጋገሩ

የፎቶው ባለመብት, Somaliland Presidential Office

እስራኤል ለሶማሊላንድ ሀገርነት ይፋ ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ የሶማሊላንድ እና የሶማሊያ እንዲሁም የቀጣናው ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ጥያቄ መነሳት ጀምሯል።

ሶማሊያ፣ ቱርክ፣ ግብፅ፣ ጂቡቲ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች የአረብ እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት ውሳኔውን በፅኑ ተቃውመውታል።

በሌላ በኩል ሶማሊላንድ ሌሎችም ሀገራትም እስራኤልን ተከትለው ዕውቅና እንዲሰጡ የአቅሟን እያደረገች ትገኛለች።

የሶማሊላንዱ ፕሬዝደንት አብዲራህማን ኢሮ እስራኤል ዕውቅና መስጠትን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር "ሌሎች ሀገራትም ለሶማሊላንድ እውቅና እንደሚሰጡ" ጠቁመዋል።

መገናኛ ብዙኃን እና የፖለቲካ ተንታኞች የእስራኤል እውቅና በቀጣናው ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ እና ሌሎች ሀገራትስ ይቀላቀሉ ይሆን? የሚለውን ጥያቄ እያብላሉ ነው።

በቀጣይ ምን ይሆናል?

በፖለቲካው መድረክ ኃያላን ከሚባሉ ሀገራት መካከል አንዷ እና የአሜሪካ የቅርብ አጋር የሆነችው እስራኤል ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር እንደምትቀጥል ይጠበቃል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ለትራምፕ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ እና ሶማሊላንድ የአብራሃም ስምምነትን እንድትቀላቀል እንደሚጥሩ አስታውቀዋል።

ኔታኒያሁ እሑድ ወደ አሜሪካ አቅንተው በፍሎሪዳ ከፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ከፍተኛ የእስራኤል ባለሥልጣናት ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

እየተጠናቀቀ ባለው የአውሮፓውያኑ ዓመት ኔታኒያሁ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሲያቀኑ ይህ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

የአውሮፓውያኑን ገና እያከበሩ የሚገኙት ዶናልድ ትራምፕ ከኔታኒያሁ ጋር ተገናኝተው በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ እንደሚያወሩ ይጠበቃል።

የወዳጃቸው ኔታኒያሁን ውሳኔ ተከትለው ለሶማሊላንድ ዕውቅና ይሰጡ አንደሆነ በመገናኛ ብዙኃን የተጠየቁት ትራምፕ "ሁኔታውን እያጤንን ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አንዳንድ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት እና ምዕራባዊያን እንዲሁም የአረብ ሀገራት ለሶማሊላንድ ዕውቅና ሊሰጡ ይችላሉ።

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን ከእነዚህ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ። ቢቢሲ ይህንን ጉዳይ ማረጋገጥ አልቻለም።

የኢትዮጵያ ጉዳይ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ለረዥም ዓመታት የዘለቀ የንግድ እና የፀጥታ ግንኙነት አላት። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ባትሰጥም ሀገራቱ በሐርጌሳ እና በአዲስ አበባ ቆንስላዎች አሏቸው።

በአውሮፓውያኑ 2024 መባቻ የቀድሞው የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተፈራረሙት ስምምነት በሶማሊያ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር። ነገር ግን ይህ ስምምነት ፍሬ አላፈራም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኢትዮጵያ "የትኛውንም ዋጋ ከፍላ" የባሕር በር ለማግኘት ቁርጠኛ መሆኗን በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይስተዋላል።

"ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የጋራ ጥቅምና ግንኙነት አላቸው። ምናአልባትም ሶማሊላንድ ዕውቅና ለማግኘት ይህንን ግንኙነት ትጠቀምበት ይሆናል። ሶማሊላንድ ከሌሎችም ሀገራት እውቅና ማግኘት ስትጀምር ይህን ጉዳይ ያጤኑት ይሆናል ብዬ እጠብቃለሁ" ይላሉ የሶማሊላንዱ የሕግ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ ጉሌድ ዳፋቅ።

በአውሮፓውያኑ 2004 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከብሪታኒያው የፓርላማ አባል ሎርድ ዴቪድ ትሪስማን ጋር ሲወያዩ "ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እውቅና ለመስጠት የመጀመሪያዋ ሀገር አትሆንም። ነገር ግን ሦስተኛዋም አትሆንም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

መለስ ይህን ማለታቸውን ትሪስማን በ2010 በቻታም ሐውስ ባደረጉት ንግግር ነው ይፋ ያደረጉት። ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ለሶማሊላንድ ዕውቅና በመስጠት ኢትዮጵያ ሁለተኛዋ ሀገር እንደምትሆን እቅድ እንደነበራቸው ይነገራል።

ጉሌድ እንደሚሉት ከሶማሊላንድ ጎረቤት ሀገራት "በጣም አስፈላጊዋ እና ዕውቅና ልትሰጥ የምትችለው" ኢትዮጵያ ናት።

በሌላ በኩል የቀድሞው የሶማሊያ ባለሥልጣን እና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ሞሐመድ ሙክታር ሁኔታው ለሶማሊያ አደገኛ እንደሚሆን ይናገራሉ።

"ኢትዮጵያም ሆነች ሌላ ሀገር ዕውቅና መስጠቱ ለሶማሊያ ትልቅ ስጋት ነው" ይላሉ።

እስራኤል ለሶማሊላንድ የሉዓላዊ ነጻ ሀገርነትን ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ምንም ዓይነት አልሰጠች ም።

ጂቡቲ እና ኤርትራ የእስራኤልን ውሳኔ የተቃወሙት ሲሆን፣ ለአካባቢው እና ለሶማሊያ ወሳኝ ኃይሎች የሆኑት ኢትዮጵያ እና ኬንያ ግን ሁኔታን በዝምታ እየተከታተሉ ይመስላሉ።

የሶማሊላንድ እውቅና በቀጣናው ምን ሊያመጣ ይችላል?

የአፍሪካ ቀንድ እና የምሥራቅ አፍሪካ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በሶማሊላንድ ዕውቅና ላይ የተመሠረተ ሊሆን እንደሚችል ጉሌድ ይናገራሉ።

ተንታኙ እንደሚሉት ለሶማሊላንድ እውቅና ተሰጠ ማለት በቀጣናው ፖለቲካ አዲስ ጫና ሊፈጥር የሚችል ተዋናይ ተቀላቀለ ማለት ነው።

በዚህም "ዕውቅናው ሶማሊላንድን ከፍ የሚያደርግ ነው። ለረዥም ዓመታት ተረስታ የነበረችው ሶማሊላንድ ድምፅ ከግምት ውስጥ መግባት ይጀምራል" ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ሞሐመድ ሙክታር በበኩላቸው በመንግሥታት መካከል ያለው ፉክክር እና ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች በቀጣናው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ትልቅ ተፅዕኖ አለው።

"ቀጣናው ፉክክር እየበዛበት መጥቷል። በጣም ወሳኝ የሚባል ለዓለም አቀፍ ንግድ ትልቅ ቦታ ያለው ነው። የሶማሊያ አንድነትም ሆነ መከፋፈል በቀጣናው ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል" ይላሉ።