እስራኤል ለሶማሊላንድ የነጻ እና ሉዓላዊ አገርነት ዕውቅና በይፋ ሰጠች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ አገርነቷን ላወጀችው ሶማሊላንድ "የነጻ እና ሉዓላዊ አገርነት" ዕውቅና መስጠቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ይፋ አደረጉ።
ይህ የእስራኤል ውሳኔ ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ከሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት በመነጠል የነጻ አገርነት ዕውቅናን ስትጠብቅ ለቆየችው ሶማሊላንድ የመጀመሪያው የአገርነት እውቅና ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ እስራኤል የሶማሊላንድ ሪፐብሊክን እንደ ነጻ እና ሉዓላዊ አገርነት በይፋ እውቅና መስጠቷ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ እርምጃ ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሶማሊላንድን የግዛቷ አካል አድርጋ የምትቆጥረው ሶማሊያ የትኛውም አገር ዕውቅና እንዳይሰጥ ስትከላከል ቆይታለች።
የአሁኑን የእስራኤልን ውሳኔ በተመለከተ የሶማሊያ መንግሥት ምላሽ እየተጠበቀ ነው።
ይህንን ይፋዊ ዕውቅናን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳአር እንዲሁም የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱ የተፈረመው በፕሬዚዳንት ትራምፕ አነሳሽነት በተረቀቀው የአብርሃም ስምምነት አማካኝነት መሆኑ ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ሳር አርብ ዕለት እንዳስታወቁት እስራኤል እና ሶማሌላንድ ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመር የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት የአምባሳደሮች ሹመትን ጨምሮ በሁለቱም አገራት ኤምባሲዎችን ለመክፈት የሚያስችል ነው ተብሏል።
ኔታንያሁ የሶማሌላንድ ፕሬዚዳንትን አብድርሃማን ሞሐመድ አብደላህን እንኳን ደስ አለዎት ያሉ ሲሆን፣ ሰላም እና መረጋጋት ለማምጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት እና የሚሰጡትን አመራር አድንቀዋል።
የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት እስራኤል የሰጠችውን የሉዓላዊ አገርነት ዕውቅናን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ "ታሪካዊ እና በመርኅ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ" ሲል አድናቆት ገልጿል።
አክሎም እውቅናው ሶማሊላንድ በዓለም አቀፉ መድረክ ለዓመታት እውቅና ለማግኘት ስታደርግ ለነበረው ጥረት መሠረት ነው ብሎታል።
"ይህ ዕውቅና ሶማሊላንድ ለረዥም ጊዜ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ለማግኘት ስታደርግ የነበረው ረዥም ጉዞን የሚያመለክት ሲሆን ይህም ታሪካዊ፣ ሕጋዊ እና የሞራል አገርነት ይገባኛል ጥያቄን ያረጋግጣል" ብሏል።
የፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት መግለጫ ሶማሊላንድ ከእስአራል ያገኘችው የአገርነት ዕወቅና በአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋች፣ ዲሞክራሲያዊ እና ኃላፊነት የሚሰማት አገር መሆኗን ያሳያል ብሏል።
ሶማሊላንድ ከ30 ዓመታት ነጻ መንግሥት መሥርታ ከቀሪው የሶማሊያ ግዛት በተለየ የተረጋጋ ሥርዓት ለመገንባት ከመቻሏም በላይ በበርካቶች የተወደሱ ዴሞክራሲያዊ ምርጫዎችን በመካሄድ የመሪዎች ለውጥ አድርጋለች።
ነገር ግን ከየትኛውም የዓለም አገር፣ ቀጠናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋም የአገርነት ዕውቅናን ሳታገኝ ቆይታለች።
እስራኤል ለሶማሌላንድ የሰጠችው ሌሎችም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ በር ሊከፍት ይችላል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በአሜሪካ ባለሥልጣናት በኩል ለሶማሊላንድ ዕውቅና የመስጠት ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
5.7 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሶማሊላንድ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ ያስገኛል የተባለ የመግባቢያ ሠነድ ፈርማ በምትኩ ኢትዮጵያ የአገርነት እውቅና እንደምትሰጣት ተገልጾ ነበር።
ነገር ግን ስምምነቱን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያ "የግዛት አካሌ ጋር ስምምነት በመፈራረም ሉዓላዊነቴን ጥሳለች" በማለት ተቃውሞ በማሰማቷ እና ውጥረቶች በመከሰታቸው ፍጻሜ ሳያገኝ ቀርቷል።
ይህንንም ተከትሎ የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት "ውድቅ የሚያደርግ" ያሉትን ሕግ አውጥተዋል።
ፕሬዝደንቱ ሕጉ "አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን እንዲሁም የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ" ወሳኝ ነው ብለው ነበር።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ውጥረት መባባሱን ተከትሎ ቱርክ ጣልቃ በመግባት ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ አድርጋለች።
ከዚህ ስምምነት በኋላ በተከታታይ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ተነጋግረዋል።
በአንድ ዓመት ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ የነበረው የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የመግባቢያ ስምምነት መቋጫ ሳያገኝ ቀርቷል።
የሶማሊያ አካል የነበረችው ሶማሊላንድ የሶማሊያ ወታደራዊ መሪ የነበሩት ሲያድ ባሬ በአውሮፓውያኑ በ1991 ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ነጻ አገር መሆኗን አውጃለች።
ሶማሊላንድ የራሷን መንግሥት ያቋቋመችው በሲያድ ባሬ አገዛዝ ዘመን ነጻነታቸውን ለማግኘት ሽምቅ ውጊያ ሲያካሄዱ የነበሩ ታጣቂዎች ረዥም የትጥቅ ትግል ካደረጉ በኋላ ነው።
በዚህ የሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ከተሞች ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ውድመት ገጥሟቸው ነበር።
ሶማሊላንድ የራሷ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ወታደራዊ እና የፖሊስ ኃይል እንዲሁም የራሷ መገበያያ ገንዘብ አላት።
ከነጻነት በፊት በነበረው በታሪኳ ዘለግ ላለ ጊዜ በብሪታኒያ የሞግዚት አስተዳደር ሥር ከቆየች በኋላ በጣሊያን ቅኝ ግዛት ሥር ከነበረው የሶማሊያ ክፍል ጋር ተዋህዳ ነበር።















