ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ እውቅና ማግኘትን ለምን አጥብቃ ፈለገች?

የሶማሊላንድ መዲና ሐርጌሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሶማሊላንድ መዲና ሐርጌሳ

ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት እንደ ሀገር የሚያስቆጥራትን እውቅና ለማግኘት ስትባዝን የቆየችው ራስ ገዟ ሶማሊላንድ፤ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችው የመግባቢያ ሠነድ የመጀመሪያውን እውቅና እንደሚያስገኝላት ይፋ አድርጋለች።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ እና ሐርጌሳ መንግሥታት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረማቸውን ተከትሎ የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ባለስልጣናት ለኢትዮጵያ የባሕር በር ሰጥተው በምላሹ ከአዲስ አበባ እውቅና ለመቀበል መስማማታቸውን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በበኩሏ የእውቅናን ጉዳይ በተመለከተ እስካሁን ግልጽ ምላሽ አልሰጠችም።

ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር እና የባሕር ላይ ንግድ አገልግሎት የሚሰጥ የባሕር ጠረፍ በሊዝ ለማግኘት የሚያስችላትን የሊዝ ስምምነት መፈጸሙን የገለጸው የአዲስ አበባው መንግሥት፤ በምላሹ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደሚኖራት አስታውቋል።

ለሶማሊላንድ እውቅና የመስጠት ጉዳይን በተመለከተ ግን በስምምነቱ ላይ የተቀመጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዩን “በጥልቀት አጢኖ አቋም እንደሚወስድ” መሆኑን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ከትላንት በስቲያ ረቡዕ 24፤ 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና የመስጠቱን ጉዳይ በግልጽ ባያሳውቅም ጉዳዩ ሶማሊላንድን እንደ አንድ የግዛቷ አካል በምትቆጥረው ሶማሊያ ዘንድ ቁጣን ቀስቅሷል። ግብጽ እና የአረብ ሊግ ከሶማሊያ ጎን እንደሚቆሙ ባወጧቸው መግለጫዎች አንጸባርቀዋል። የአውሮፓ ኅብረትም የሶማሊያ ሉዐላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲከበር ጠይቋል።

የአፍሪካ ኅብረት እና ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢጋድ ደግሞ በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ያለው ውጥረት እንዲረግብ ጥሪ አቅርበዋል።

እውቅና መስጠት “የባሕር በሩን ማግኘት የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ነው”

በሰኞ ዕለቱ የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ ለ50 ዓመታት በሚቆይ ሊዝ እንደምታገኝ ተገልጿል። ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳ ካዪድ የመግባቢያ ስምምነቱ የባሕር በር ጉዳይን ጨምሮ ኢኮኖሚ፣ ደኅንነት፣ ትምህርት፥ ጤና እና ወታደራዊ ትብብሮችን የተመለከቱ ጉዳዮች እንደተካተቱበት ተናግረዋል።

እንደ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገለጻ የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ሶማሊላንድ ከአዲስ አበባ እውቅና ከማገኘቷ ጋር ትስስር ያለው ነው። ኢሳ፤ “ይሄ የመግባቢያ ስምምነት ነው። ይህንን ተከትሎ የተለያዩ ስምምነቶች ይመጣሉ። ፕሬዝዳንታችን ሲናገሩ እንደተደመጡት እውቅና ማግኘት ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ነው። [እውቅና መስጠት] የባሕር በሩን ማግኘት የሚችሉበት ብቸኛው መንገድ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ፤ ሶማሊላንድ “ነጻ ሀገር” ስለመሆኗ እውቅና እንደምትሰጥ ማወጅ እንዳለባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለዋል።

የሶማሊያ የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር ዳውድ አዊስ ግን ሀገራቸው የሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያን ፊርማ የምትመለከተው “የሶማሊ ሕዝብን ፍላጎት እና ፈቃድ የማይወክል ሕገ ወጥ የመግባቢያ ስምምነት” አድርጋ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህንን አይነቱን ስምምነት የመፈራረም ስልጣን ያለው የሞቃዲሾው የፌደራል መንግሥት መሆኑን አስረግጠው የሚናገሩት ዳውድ፤ “ክልላዊ መንግሥት ዓለማ አቀፋዊ ስምምነት መፈራረሙ የሕግ ጥሰት እና በሶማሊያ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው” ብለዋል።

“የሶማሊያ ፌደራላዊ ሪፐብሊክን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና አንድነት ለመጣስ የሚደረግን የትኛውንም ሙከራ በተመለከተ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግሥትን አጥብቀን እናስጠነቅቃለን” ሲሉም ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ላይ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ “ሕጋዊ ያልሆነ ድርጊት” እንደማትቀጥል ለማረጋገጥ ሲባልም ሶማሊያ መንግሥት “በዓለም አቀፉ መድረክ የሚገኝ ማንኛውንም ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ” መሆኑን አስታውቀዋል።

“ይህ የማይደረግ ከሆነ ግዛታችንን ለመከላከል ዝግጁ ነን። ሁሉም [አማራጭ] ጠረጴዛው ላይ ነው” ያሉት የኢንፎርሜሽን ሚኒስትሩ፤ ይሁንና ሶማሊያ ከጎረቤቶቿ ጋር “የትኛውም አይነት ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ለመግባት” ዝግጁ እንዳልሆነች ገልጸዋል። የሶማሊያ መንግሥት ጥሪ እያቀረበ ያለው ጉዳዩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ መሆኑም አክለዋል።

ወደብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳ ግን ራስ ገዟ “ከቀሪው ሶማሊያ የተነጠለች” መሆኗን በመጥቀስ የሞቃዲሾ እንቅስቃሴ “ምንም አይነት ተጽእኖ እንደማይኖረው” ተናግረዋል።

“[ሶማሊያ] በእኛ አቋም ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚያስችል ምንም አይነት ሕጋዊም ሆነ ሌላ መሠረት የላትም። የሀገሪቱ ጠቅላይ፣ የውጭ ጉዳይ ወይም የሀገር ውስጥ ሚኒስትሮች የሚናገሩት ማንኛውም ነገር በእኛ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ የለም” ሲሉም የመንግሥታቸውን አቋም አስረድተዋል።

“ሀገራት እውቅና ለመስጠት የመጀመሪያው እንደማይሆኑ ነግረውን ነበር”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ እውቅና ልትሰጥ ተስማምታለች የሚለው ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰማው የመግባቢያ ሠነዱ በተፈረመበት ዕለት በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ነበር።

የሀገሪቱ ካቢኔ ከትላንት በስቲያ ካደረገው ስብሰባ በኋላም ባወጣው መግለጫ ላይ ደግሞ ኢትዮጵያ “ለሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ሉዐላዊነት በመስጠት የመጀመሪያዋ ሀገር” መሆኗን በመጥቀስ ምስጋውን አቅርቧል።

ሶማሊላንድ ባለፉት 33 ዓመታት እውቅና ለማግኘት ስትጥር እንደነበረ የሚያስታውሱት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳ፤ የኢትዮጵያ እውቅና መስጠት ሀርጌሳ ስታደርግ የነበረው ጥረት ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ለቢቢሲ ተናግረዋል። እስካሁን ድረስ በነበረው ጥረት ብዙ ሀገራት ለሶማሊላንድ እውቅና በመስጠት የመጀመሪያ ሲያፈገፍጉ እንደነበርም ጠቁመዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ “ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ እስካሁን ጥያቄ ስናቀርብላቸው የነበሩ ሁሉም ሀገራት [ለሶማሊላንድ እውቅና በመስጠት] የመጀመሪያ ሀገር እንደማይሆኑ፤ [ነገር ግን] ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ ሀገር እንደሚሆኑ ነግረውናል። ስለዚህ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሀገር ናት” ሲሉ ሌሎች ሀገራት ይህንን ፈለግ ሊከተሉ እንደሚችሉ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድም ሆነ ለአፍሪካ እና ለተቀረው ዓለም “በጣም ወሳኝ ሀገር” መሆኗን የሚናገሩት ኢሳ፤ “ብዙ ለውጥ ያመጣል። ምክንያቱም [እውቅና ለማግኘት] በአፍሪካ ኅብረት፣ አረብ ሊግ እና የአውሮፓ ኅብረት [በምናደርገው ጥረት] ኢትዮጵያ ከእኛ ጋር ሆና ዘመቻ ታደርጋለች” ብለዋል።

የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን በመተንተን የሚታወቁት አሌክስ ደ ዋል ግን የኢትዮጵያ እውቅና መስጠት ሌሎች ሀገራትም እንዲከተሉ ማድረጉ ላይ ብዙም እምነት እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል። ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠትን በተመለከተ የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች “ምናልባት ቀጣይ እርምጃ የምትወስድ ሀገር” ልትሆን እንደምትችል አሌክስ አስረድተዋል። “ነገር ግን ይሄ ሌሎች እንዲከተሉ የሚስችል አሻራ ያስቀምጣል ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ይልቁንስ በቀጠናው ላይ ጠላትነትን ሊያፋፍም ይችላል” ሲሉ ጉዳዩ ስጋት የሚጭር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ስምምነት እድል እና ስጋቶች

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ እና በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ዙሪያ ጥናቶችን ያደረጉት አቶ ነገራ ጉደት፤ የመግባቢያ ስምምነቱ ለሶማሊላንድ ትልቅ ጥቅም ይዞ ይመጣል ይላሉ። “ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረሙት የመግባቢያ ሠነድ ከዲፕሎማሲ አንጻር ካየነው እንደ ሀገር እውቅና እንዲያገኙ ያስችላዋለች። ይህ ትልቅ ትርጉም አለው” የሚሉት አቶ ነገራ፤ ኢትዮጵያም ለጂቡቲ ወደብ የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ እንደሚቀንስላት ያስረዳሉ።

ከዚህም ባሻገር ከሶማሊላንድ በሚገኘው 20 ኪሎ ሜትር የባሕር ጠረፍ ላይ ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል መገንባት የምትችል መሆኑን በእድልነት ያነሱታል። “አንድ አገር ሙሉ የሆነ ጠንካራ ሠራዊት ገንብቷል የሚባለው በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአየር፣ የምድር እና የባሕር ኃይሎች ሲኖረው ነው” ሲሉም የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር መገንባት ያለውን ጥቅም ይጠቅሳሉ።

ይሁንና አቶ ነገራ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰው ስምምነት “ምርቃትም፤ እርግማንም ይዞ ይመጣል” ባይ ናቸው። የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያው ኢትዮጵያ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ወይም በቀይ ባሕር ላይ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር የምትገነባ ከሆነ ሂደቱ በቀጠናው ላሉ አገራት እረፍት የሚነሳ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ይህ ስምምነት ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ ጠላት የሆኑት የሶማሊያ መንግሥት እና ጽንፈኛው እስላማዊ ቡድን አል-ሸባብ አንድ ሆነው ኢትዮጵያ ላይ ብረት ሊያነሱ ይችላሉ ሲሉም ይገምታሉ። አቶ ነገራ እንደሚሉት ስምምነቱ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያበላሽ ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ይፈልጋል።

የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኙ አሌክስ ደ ዋል በበኩሉ ከስምምነቱ ወዲህ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል እየታየ ያለው መካረር “በአጭር ጊዜ” ውስጥ ወደ ወታደራዊ እርምጃ የመቀየር እድሉ ዝቅተኛ መሆኑን ይናገራል።

“የዲፕሎማሲው አካሄድ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ ወይም ኤርትራ ጋር ላላት ግንኙነት ምን አይነት ትርጉም ይሰጣል የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው። ጉዳዩ ብዙ ስጋት እየፈጠረ ያለው እዚህ ላይ ነው” ሲል በአሁኑ ሰዓት በጉዳዩ ላይ በእርግጠኝነት መናገር እንደማይቻል ይጠቁማል።

ይሁንና በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት “እጅጉን ወታደራዊ” እና “ራሱን እያስታጠቀ” መሆኑ እንዲሁም የመንግሥት እንቅስቃሴ “ወጥ ያልሆነ” መሆኑ ስጋት መሆኑን ያነሳል። “ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገሪቱ ውስጥም ሆነ በድንበር አካባቢዎች የሚገኝ የትኛውንም ጦርነት የሚያጠናክር ከሆነ ስፋት ያለው ቀጠናዊ ጦርነት ሊፈጠር ይችላል” ሲል ስጋቱን ገልጿል።

በሶማሊላንድ እና ኢትዮጵያ ስምምነት ውስጥ የአረብ ኤምሬቶች “አሻራ ይታያል” የሚለው የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ተንታኙ አሌክስ ደ ዋል፤ አቡ ዳቢ “በሶማሌ ላንድ እና ወደቧ ላይ በጣም ፍላጎት” እንዳላት ያስረዳል።

“ሳውዲ አረቢያ፣ ኳታር እና ሌሎች ሀገራት የተባበሩት ኤምሬቶች በአፍሪካ ቀንድ፣ ቀይ ባሕር እና በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ የምታደርገው እንቅስቃሴ እየተከታተሉት ያለው በከፍተኛ ስጋት ነው” ሲልም ከዚህ ስምምነት ቀጥሎ በአቡ ዳቢ የሚወሰድ እርምጃ “በቀጠናው ላይ ጠላትነትን ሊያፋፍም” እንደሚችል ይናገራል።