የሶማሊያው ፕሬዝደንት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት “ውድቅ የሚያደርግ ሕግ” አወጡ

የፎቶው ባለመብት, Hassan Sheikh Mohamud
የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት “ውድቅ የሚያደርግ” ያሉትን ሕግ ፈርመው አፅድቀዋል።
ፕሬዝደንቱ በኤክስ ገፃቸውን በለጠፉት መልዕክት “ዛሬ አመሻሹን የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሶማሊላንድ የገቡትን የመግባቢያ ሰነድ ውድቅ የሚያደርግ ሕግ ፈርሚያለሁ” ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ በመልዕክታቸው ይህ ሕግ “አንድነታችንን እና ሉዓላዊነታችንን እንዲሁም የግዛት አንድነታችንን ለመጠበቅ” ወሳኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ከሆነችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነድ ሰኞ ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. መፈራረሟ ይታወሳል።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ‘የግዴታ ተፈፀማኒት የሌለውን’ የመግባቢያ ሰነድ የፈረሙት አዲስ አበባ ላይ በተካሄድ ሥነ-ሥርዓት ነው።
በዚህ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ወደብ 20 ኪሎ ሜትር ገደማ ወደብ ታገኛለች። በምትኩ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አሊያም ከኢትዮ ቴሌኮም የተወሰነ ድርሻ እንደምታገኝ መንግሥት ገልጧል።
ይህን ስምምነት ተከትሎ አስቸኳይ ስብሰባ የጠራችው ሶማሊያ ስምምነቱ “ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው” የሚል መግለጫ ማውጣቷ ይታወሳል።
በተባበሩት መንግሥታትም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት ዕውቅና ያልተሰጣት ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ዕውቅና ልታገኝ እንደምትችል ቢጠቆምም እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ሶማሊላንድ እንደ አንድ ክፍሏ የምትቆጥረው ሶማሊያ ጠ/ሚ ዐቢይ እና ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ የገቡትን ስምምነት በመቃወም አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ ጠርታለች።
ይህን ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከግብጽ ፕሬዝዳንት እና ከኳታር መሪ ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ግብፅ በይፋ “የሶማሊያ የግዛት አንድነት ሊጠበቅ ይገባል” ማለቷ አይዘነጋም።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ምን አሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስምምነቱን ተከትሎ የተሰሙትን “መግለጫዎች የጠበቅናቸው ናቸው” ብለዋል።
አምባሳደር ሬድዋን ከብሔራዊው ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ነው ይህን ያሉት።
አማካሪው “ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ መድረክ ጋር የሚያገናኛትን የባሕር በር ካገኘች በሁለት እግሯ ልትቆም ትችላለች የሚል ሥጋት አላቸው” ያሏቸው አካላት “እሳትና ነዳጅ ሲያቀብሉ አይተናል” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
አምባሳደር ሬድዋን መግለጫ ካወጡት መካከል “የራሳችን የምንላቸው ሰዎች ከሌላው በለላይ ሲወራጩ ሲታይ ያስቆጫል፤ ያሳዝናልም” ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ራሷ የምትቆጣጠረውና የምታለማው የባሕር በር መኖሩ ለሀገሪቱ ደኅንነትና የንግድ እንቅስቃሰሴ ትልቅ ሚና እንደሚኖረውም እሙን ነው” ይላሉ አማካሪው።
አምባሳደሩ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ስለመስጠትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
“የመግባቢያ ሰነዱ ጉዳይ ወደ ተሟላ ስምምነት ደርሶ መሬቱን ስንረከብና ሂደቱ ሲቋጭ እነሱ እውቅና ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት በተመለከተ ኢትዮጵያ አቋም የምትወስድበ ደረጃ ላይ እንደርሳለን የሚሉ አመላካች ነገሮች ናቸው ያሉት።
“ስለዚህ ስምምነቱን አልተረከብንም፣ መስማማት እንዳለብን ግን ተስማምተናል፤ እርሱን ደግሞ በመግባቢያ ሰነድ ፈርመናል” ብለዋል።
አምባሳደሩ ድርድሩ እንደሚቀጥልና ከሌሎች ሀገራትም ጋር የሚደረግ ንግግር እንደሚኖር ሲጠቁሙ “የተሻለ ኦፈር፣ ድርድር፣ ኢንቨስትመንት እና ዘላቂነት ካለ አሁንም ንግግሩ ይቀጥላል” ሲሉ ተናግረዋል።
ሶማሊላንድ የምትሰጠው የባህር በር የሚገኘው በበርበራ እና ዘይላ መካከል የሚገኝ ሎግሃያ የሚባል አካባቢ” እንደሆነ አምባሳደሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የገቡትን ስምምነት ተከትሎ ሀገራትና አህጉራት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮፓ ኅብረት “የሶማሊያ የግዛት አንድነት ሊጠበቅ ይገባል” የሚል አስተያየት ሲሰጡ የአፍሪካ ኅብረት በበኩሉ በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው “ውጥረት እንዲረግብ” ጥሪ አቅርቧል።












