ከእስራኤል የመጀመሪያዋን የአገርነት ዕውቅና ስላገኘችው ሶማሊላንድ የምናውቀው

በሶማሊላንድ የነጻነት በዓል ላይ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የሚታዩ ታዳጊ ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በሶማሊላንድ የነጻነት በዓል ላይ ሰንደቅ ዓላማ ይዘው የሚታዩ ታዳጊ ሴቶች

ከዋናው የሶማሊያ ክፍል በስተ ሰሜን የምትገኘው ሶማሊላንድ በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ የምትገኝ ከፊል በረሃማ የሆነች አካባቢ ናት።

ሶማሊላንድ በስተ ሰሜን ከጂቡቲ፣ በስተ ምዕራብ ደግሞ ከኢትዮጵያ እንዲሁም በስተ ደቡብ ምሥራቅ በኩል ደግሞ ከሶማሊያዋ ፑንትላንድ ግዛት ጋር ትዋሰናለች።

ሶማሊላንድ ከፑንትላንድ ጋር በሚያዋስናት ሰፊ ግዛት ምክንያት የይገባኛል ውዝግብ ውስጥ ስትሆን አልፎ አልፎ ግጭቶች ሲያጋጥሙ ቆይተዋል።

የሶማሊያ ወታደራዊ መሪ የነበሩት ሲያድ ባሬ በአውሮፓውያኑ 1991 ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ነጻ አገር መሆኗን አውጃለች።

ሶማሊላንድ የነጻ አገርነት ፍላጎቷን ይፋ ያደረገችው በሲያድ ባሬ የመሪነት ዘመን ነጻነታቸውን ለማግኘት ሽምቅ ውጊያ ሲያካሄዱ የነበሩ ታጣቂዎች የረዥም ዓመተት የትጥቅ ትግል ካደረጉ በኋላ ነው።

በዚህ የሶማሊያ የእርስ በእርስ ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ ከተሞች ደግሞ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል።

ምንም አንኳ ከየትኛውም የዓለም አገር እውቅና ባታገኝም ሶማሊላንድ የራሷ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የመንግሥት ተቋማት፣ ወታደራዊ እና የፖሊስ ኃይል እንዲሁም የራሷ መገበያያ ገንዘብ አላት።

ከዚህ ቀደም በታሪኳ ዘለግ ላለ ጊዜ በብሪታኒያ የሞግዚት አስተዳደር ሥር የነበረችው ሶማሊላንድ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በሶማሊያ የሚካሄደውን ጦርነት፣ ግጭት ሁሉ ማምለጥ ችላለች።

ስለ ሶማሊላንድ በጥቂቱ

  • ዋና ከተማዋ፡ ሐርጌሳ
  • የቆዳ ስፋት፡ 177 ሺህ ስኬዌይር ኪሎ ሜትር
  • የሕዝብ ብዛት፡ 5.7 ሚሊዮን
  • ቋንቋ፡ ሶማሊኛ፣ አረብኛ እና እንግሊዘኛ
  • አማካይ የዕድሜ ጣሪያ፡ 50 ዓመት
የሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሐርጌሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሶማሊላንድ ዋና ከተማ ሐርጌሳ

በሰባተኛው ክፍለ ዘመን- ወደ አሁኗ ሶማሊላንድ የእስልምና ሃይማኖት እንደገባ ይነገራል።

1888- ብሪታኒያ ወደ አካባቢው ዘልቃ ሱልጣኖች ጋር በመስማማት የሞግዚት አስተዳደር መሠረተች።

1899- ሞሐመድ አብደላህ በብሪታኒያ ላይ በማመጽ እስከ 1920 ድረስ ውጊያ ተካሄደ።

1960- የብሪታኒያን ሶማሊላንድ እና የጣልያን ሶማሌላንዶች ነጻ ሆነው የሶማሊያ ሪፐብሊክ አለል ሆኑ።

1991- የሲያድ ባሬን ከሥልጣን መወገድን ተከትሎ የቀድሞ የብሪታኒያ ሶማሊላንድ ግዛት ነጻ አገር መሆኗን አወጀች።

2001- ከ97 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ሕዝብ በ1997 የተረቀቀውን ሕገ መንግሥት በማጽደቅ ሶማሊላንድ ነጻ አገር መሆኗን አረጋገጠ።

2016- ሶማሌላንድ ምንም እንኳ የትኛውም የዓለማችን አገራት ነጻ አገር መሆኗን ባይቀበሉትም፣ የተመሠረተችበትን 25ኛ ዓመት የነጻነት በዓል አክብራለች።

የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት

የዋዳኒ ፓርቲ መሥራች እና ሊቀመንበር የሆኑት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ነበር።

በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲን የመራጩን 64 በመቶ ድምጽ በማግኘት ነበር ያሸነፉት።

በአውሮፓውያኑ እስከ 2012 ድረስ ከጀስቲስ ኤንድ ዌልፌር ፓርቲ (ዩሲአይዲ) ጋር በመሆን ይሠሩ የነበሩት ፕሬዚዳንት አብዲራህማን ከፓርቲው አመራሮች ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ዋዳኒን መሥርተዋል።

ለ12 ዓመታት የአገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የነበሩት ፕሬዚዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ፣ አገራቸው ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ እንደሚሠሩ ቃል ገብተው ነበር።

አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ

የፎቶው ባለመብት, Cabdiraxmaan Cirro

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ

ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ነጻ አገር መሆኗን በሚመለከት ያደረገቻቸውን ያልተሳኩ ንግግሮችን መለስ ብሎ ማየት እና መነጋገር እንደሚያስፈልግ ይህንንም እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር።

አብዲራህማን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ስለፈረመችው የመግባቢያ ስምምነትን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በተጠየቁበት ወቅት፣ ሶማሊላንድ ከማንኛውም አገር ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት የማድረግ መብት እንዳላት መናገራቸው ይታወሳል።

በሲያድ ባሬ አስተደዳር ወቅት በሶማሊያ መንግሥት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት እና በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የሶማሊያ ኤምባሲ ውስጥ ዲፕሎማት ሆነው ያገለገሉት አብዲራህማን የሰባ ዓመት አዛውንት ናቸው።

በሶማሊያ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ተባብሶ የዚያድ ባሬ መንግሥት ሲወድቅ እና በአገሪቱ የጦር አበጋዞች ፍልሚያ ሲቀጥል አብዲራህማን ቤተሰቦቻቸው በሚገኙበት ፊንላንድ መቀመጫቸውን አድርገው የነበረ ሲሆን ዜግነትም አግኝተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2002 ከሶማሊያ ነጻ በመውጣት ነጻ አገርነቷን ባወጀችው ሶማሊላንድ ውስጥ የሚካሄደውን መልሶ ግንባታ ለማገዝ የፖለቲካ አጋራቸው ከሆኑት ፋይሳል አሊ ዋራቤ ጋር በመሆን የፍትህ እና ልማት የተባለ ፓርቲ መሥርተው በምርጫ በመወዳደር የአገሪቱ ምክር ቤት አባል ሆነዋል።

ከዚያ ጊዜ በኋላ በሶማሊላንድ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ እያደረጉ የቆዩት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ዋዳኒ የተባለውን ፓርቲ አቋቁመው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሆነው እስከመመረጥ ደርሰዋል።

የፊንላንድ ዜግነት ያላቸው ፕሬዚዳንት አብዲራህማን ሶማሊኛ፣ እንግሊዘኛ፣ አረብኛ፣ ሩሲያኛ እና ፊንላንድኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ።