የተመራጩ የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ፓርቲ ከኢትዮጵያ ጋር ስለተፈረመው ስምምነት ምን ይላል?

የፎቶው ባለመብት, Cabdiraxmaan Cirro
ከሶማሊያ ተነጥላ ነፃ ሀገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ፤ ለአራተኛ ጊዜ ባደረገችው ምርጫ አዲስ ፕሬዝዳንት መርጣለች። በዚህ ምርጫ ላለፉት ሰባት ዓመታት ሶማሊላንድን በፕሬዝዳንትነት የመሩት ሙሴ ቢሂ በተቃዋሚው ዋዳኒ ፓርቲ መሪ አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) ተሸንፈዋል።
የሶማሊላንድ ምርጫ ኮሚሽን ማክሰኞ፣ ኅዳር 10/2016 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ውጤት እንደሚያመለክተው ፕሬዝዳንት ቢሂ ከመራጮች ድምፅ ውስጥ ያገኙት 35 በመቶው ገደማውን ነው። የሶማሊላንድ ፓርላማ አፈ ጉባኤ የሆኑት ተቃዋሚው አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ደግሞ 64 በመቶው ገደማውን ድምፅ አግኝተዋል።
ከቢቢሲ ኒውስ ዴይ ፕሮግራም ጋር ቆይታ ያደረጉት የተመራጩ ፕሬዝዳንት ፓርቲ ቃል አቀባይ ማህሙድ አደም ጃማ ጋላል፤ ምርጫው “ከፍተኛ ፉክክር” የታየበት ቢሆንም ሂደቱ “በተቃና ሁኔታ” መከናወኑን ተናግረዋል።
“በቀጣናው ከሚገኙ ብዙ ሀገራት” ከሚታየው የምርጫ ሂደት አንጻር የሶማሊላንዱ ምርጫ “እጅግ ነፃ እና ፍትሐዊ” እንደነበረም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
በቀጣናው ላይ ተፅዕኖ ያላቸው አሜሪካ እና ኢትዮጵያም የሶማሊላንድን ምርጫ አሞግሰዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት አርብ ኅዳር 6/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ምርጫውን “ሰላማዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ነጻ እና ፍትሐዊ” ሲል አሞካሽቷል።
ሚኒስቴሩ ትናንት ማክሰኞ ከምርጫው ውጤት ይፋ መሆን በኋላ ባወጣው መግለጫ ደግሞ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ እና ተመራጩ ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) ላሳዩት “ምሳሌ የሚሆን ዲሞክራሲያዊ መሪነት” አድናቆቱን ችሯል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ሞሐመድ አብዱላሂ በፕሬዝዳንትነት ለመመረጣቸውም “የእንኳን ደስ አለዎት” መልዕክቱን አስተላልፏል።
በሶማሊላንድ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አጀንዳ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ የተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ነበር። የመግባቢያ ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለባሕር ኃይል እና ለንግድ የሚውል 20 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው የባህር ጠረፍ ከሶማሊላንድ በሊዝ እንድታገኝ የሚያደርግ ነው።
በምላሹ ደግሞ ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ እንደ ሀገር እውቅና ላላገኘችው ሶማሊላንድ እውቅና ልትሰጥ እንደተስማማች የሐርጌሳ ባለሥልጣናት ገልጸዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የተስማማው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻን ለሶማሊላንድ ለመስጠት እና እንደ ሀገር እውቅና የመስጠቱን ጉዳይ “አጢኖ አቋም ለመያዝ” እንደሆነ አስታውቋል።
ሁለቱ ሀገራት በተፈራረሙበት ወቅት የመግባቢያ ሰነዱ በአንድ ወር ውስጥ ተግባራዊ ወደሚሆን ስምምነት እንደሚቀየር ቢገለጽም፤ አንድ ዓመት ሊሞላው ቢቃረብም እስካሁን በይፋ የተገለጸ ነገር የለም። በአንጻሩ የስምምነቱ መፈረም የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድን እንደ ግዛቷ አካል የምትቆጥረው ሶማሊያን ግንኙት አሻክሮታል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ተመራጩ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት፤ ፓርቲያቸው ስምምነቱን እንደሚገመግመው ተናግረው ነበር። ተመራጩ ፕሬዝዳንት የመግባቢያ ስምምነቱን ውድቅ አድርገው ባያውቁም ስለጉዳዩ ሲያወሩ ዲፕሎማሲያዊ ቋንቋን ይጠቀማሉ።
የተመራጩ ፕሬዝዳንት ፓርቲ ስምምነቱን እንዴት እንደሚመለከተው ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የዋዳኒ ፓርቲ ቃል አቀባይ ማህሙድ አደም፤ “ከቀድሞም ቢሆን አቋማችን አንድ ነው፤ ተመሳሳይ ሆኖ ይቆያል” ሲሉ ስምምነቱን የመገምገም ሀሳብ እንዳልተቀየረ አስረድተዋል።
ቃል አቀባዩ፤ ፓርቲያቸው በአሁኑ ሰዓት ከኢትዮጵያ ጋር ስለተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት አስተያየት መስጠት እና መወያየት እንደማይችል አስታውቀዋል። ማህሙድ፤ አስተያየት ላለመስጠት በምክንያትነት የጠቀሱት “በሂደቱ ወቅት ስምምነቱ ለፓርቲው ያልተገለጸ” መሆኑን እና “ከዚያም በኋላ ፓርቲው ስምምነቱን አለመመልከቱን” ነው።
ቃል አቀባዩ፤ “በአጠቃላይ ግን ከጎረቤቶቻችን ጋር የሚደረግ ማንኛውም ፍትሐዊ እና የጋራ ተጠቃሚነት ትብብርን እንቀበላለን። በተለይ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ታላቅ አጋር እና ወዳጅ ነበረች። ወደ ሥራ ስንገባ ደግሞ ያለፈው መንግሥት የሠራውን እንገመግማለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
እስካሁን ድረስ እየተሸኘ ካለው የሶማሊላንድ መንግሥት ጋር ውይይት አለመደረጉን የገለጹት ማህሙድ፤ “እስከሚያውቁት ድረስ” ፓርቲያቸው ከኢትዮጵያ ጋር ያደረገው ንግግር አለመኖሩን ጠቅሰዋል።
ይሁንና ፓርቲው እንደ ገዢው ፓርቲ ሁሉ የሶማሊላንድን እንደ ሀገር እውቅና የማግኘት ጥረት እንደሚያስቀድም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል። ፓርቲያቸው ሶማሊላንድ እንደ ሀገር እውቅና የሚያስገኝላት “አሳማኝ ምክንያት” አላት ብሎ እንደሚያምን ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ፤ “እንደ ዋዳኒ ፓርቲ፤ ተመራጩ ፕሬዝዳንት እና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚመሠርቱት መንግሥት ይህንን ህልም እውን ለማድረግ፣ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና ለማግኘት የምናደርገውን ጥረት ለመሳካት የምንችለውን ሁሉን እናደርጋለን” ብለዋል።
ተመራጩ ፕሬዝደንት በአውሮፓውያኑ በመጪው ታኅሣሥ አጋማሽ መንበረ ሥልጣናቸውን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።















