በሶማሊላንድ ምርጫ የተቃዋሚው ፓርቲ መሪ አሸነፉ

የፎቶው ባለመብት, Cabdiraxmaan Cirro
ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ባደረገችው ስድስተኛ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ ተቀናቃኝ የሆኑት የተቃዋሚው ፓርቲ ዋዳኒ መሪ አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ (ኢሮ) አሸነፉ።
የሶማሊላንድ የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ማሸነፋቸውን ይፋ ያደረገው የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን በመዲናዋ ሃርጌሳ ማክሰኞ፣ ህዳር 10/2016 ዓ.ም በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በርካቶች ደስታቸውን በሃርጌሳ ጎዳናዎች ላይ እየገለጹ መሆኑን የቢቢሲ ሶማሊ ዘጋቢ ከስፍራው ተመልክቷል።
ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በሶማሊያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ለሶማሊላንድ እና ለተመራጩ ፕሬዚዳንት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቱን በኤክስ ገጹ አስፍሯል።
“የሶማሊላንድ አስደናቂ የምርጫ ታሪክ እንዲሁም ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ለቀጣናው እና ከዚያም ባለፈ አርዓያ ነው” ሲል ኤምባሲው አሞካሽቶታል።
በውጤቱ መሠረት ተመራጭ ፕሬዚዳንት አብዲራህማን 63.92 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሲሆኑ፣ ኩልሚዬ የተሰኘ ፓርቲን የሚመሩት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ 34.81 በመቶ ድምጽ አግኝተዋል።
ሌላኛው ዕጩ ፕሬዚዳንት የጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ፓርቲ ተወካይ ፋይሳል አሊ ዋራቤ 0.74 በመቶ ድምጽ በጊዜያዊ ውጤቱ ማግኘታቸው ተገልጿል።
ለ12 ዓመታት የአገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ተመራጩ ፕሬዚዳንት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ፣ አገራቸው ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ እንደሚሠሩ ቃል ገብተው ነበር።
አገራቸው ከዚህ ቀደም ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ነጻ አገር መሆኗን በሚመለከት ያደረገቻቸውን ያልተሳኩ ንግግሮችን መለስ ብሎ ማየት እና ከሶማሊያ ጋር ተቀምጦ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ከተመረጡም ይህንኑ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር።
አብዲራህማን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ስለፈረመችው የመግባቢያ ስምምነትን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በተጠየቁበት ወቅት፣ ሶማሊላንድ ከማንኛውም አገር ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት የማድረግ መብት እንዳላት መናገራቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት ሙሴ ቤሂ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት እና በምትኩም ለሶማሊላንድ እንደ አገር ዕውቅና ለመስጠት የመግባቢያ ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ለማግኘት ለ33 ዓመታት ያህል እየጠየቀች ያለችው ሶማሊላንድ የዘንድሮው ምርጫ ዋነኛ አጀንዳ እንደ አገር እውቅና በማግኘት ላይ ያተኮረ ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ተመርጠው የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን የያዙት ሙሴ ቢሂ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር የገቡት ስምምነት እንደሚቀጥል እና አገራቸው እውቅና እንደምታገኝ ቃል ገብተዋል።
ሶማሊላንድ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ለደጋፊዎቻቸው የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚጠበቅበትን እስከሚያደርግ እየጠበቁ መሆኑን አብራርተዋል።
“ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ትፈልጋለች፤ እኛ ደግሞ እውቅና ማግኘት እንፈልጋለን ስምምነቱ ይህንን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ነው” ሲሉ ነበር በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የተናገሩት።
የጀስቲስ ኤንድ ዴቬሎፕምንት ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ ዕጩ ወራቤ በበኩላቸው ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት በመመሥረት ለእውቅና እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል።
ኢትዮጵያ በዚህ ስፍራ የባሕር ኃይል ሰፈር እንደምታቋቁም እና በምትኩም ለሶማሊላንድ ዕውቅና ትሰጣለች መባሉን ተከትሎ እንደ ግዛቷ አካል የምታያት ሶማሊያ ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ወስዳዋለች።

የፎቶው ባለመብት, sm
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ማን ናቸው?
አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ሶማሊላንድ ከሶማሊያ ተለይታ የራሷን አስተዳደር ከመሠረተች በኋላ የተቋቋመው የመጀመሪያው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው አገልግለዋል። አሁን በምርጫ ያሸነፉበትን ዋዳኒ ፓርቲ መሥራች እና ሊቀመንበር የሆኑት አብዲራህማን ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በሶማሊያ መንግሥት ውስጥ አገልግለዋል።
ወደ ሰባ ዓመት ዕድሜ ሊገቡ የተቃረቡት አብዲራህማን በመንግሥት ሥራ በተለያዩ የሶማሊያ አካባቢዎች ውስጥ የሠሩ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 1981 በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ሞስኮ በሚገኘው የሶማሊያ ኤምባሲ ውስጥ ዲፕሎማት ሆነው ለአስር ዓመታት ያህል አገልግለዋል።
በሶማሊያ ውስጥ ሲካሄድ የቆየው ጦርነት ተባብሶ የዚያድ ባሬ መንግሥት ሲወድቅና በአገሪቱ የጦር አበጋዞች ፍልሚያ ሲቀጥል አብዲራህማን ቤተሰቦቻቸው በሚገኙበት ፊንላንድ መቀመጫቸውን አድርገው የነበረ ሲሆን ዜግነትም አግኝተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2002 ከሶማሊያ ነጻ በመውጣት ነጻ አገርነቷን ባወጀችው ሶማሊላንድ ውስጥ የሚካሄደውን መልሶ ግንባታ ለማገዝ የፖለቲካ አጋራቸው ከሆኑት ፋይሳል አሊ ዋራቤ ጋር በመሆን የፍትህ እና ልማት የተባለ ፓርቲ መሥርተው በምርጫ በመወዳደር የአገሪቱ ምክር ቤት አባል ሆኑ።
ከዚያ ጊዜ በኋላ በሶማሊላንድ ፖለቲካ ውስጥ ጉልህ ተሳትፎ እያደረጉ የቆዩት አብዲራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ዋዳኒ የተባለውን ፓርቲ አቋቁመው ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ምርጫ ላይ በመሳተፍ በሥልጣን ላይ ያሉትን ሙሴ ቢሂን ማሸነፋቸው ተነግሯል።
አንድ አገር ሊኖረው የሚገባውን ነገሮች የምታሟላው ሶማሊላንድ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ዕውቅና ሳታገኝ ብትቆይም በበርካቶች ዘንድ የተወደሰ አሳታፊ ምርጫ ማከሄዷ ይነገርላታል።
ሦስት ዕጩዎች ለፕሬዝዳንትነት በተወዳደሩበት የአሁኑ ምርጫ የተፎካካሪዎቹ ዋነኛ ግብ ከሆኑት መካከል የሶማሊላንድ ዕውቅና ጉዳይ አንዱ ነው። ተመራጩ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን በቀጣይ የሥልጣን ዘመናቸው በአገሪቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እና ማኅበራዊ ትስስርን ማጠናከር ግባቸው አድርገዋል።












