እንደ አገር ዕውቅና ማግኘትን አጀንዳቸው ያደረጉት ዕጩዎች የሚፎካከሩበት የሶማሊላንድ ምርጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ምንም እንኳን ነጻ አገርነቷን ዕውቅና የሰጠ አገር ባይኖርም አንድ አገር የሚያስፈልገውን ሁሉ የምታሟላው ሶማሊላንድ፣ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በአፍሪካ ውስጥ በዴሞክራሲያዊነት ከሚጠቀሱ ምርጫዎች መካከል የሚጠቀሱ ምርጫዎችን አካሂዳለች።
በተለያዩ ምክንያቶች ለረዥም ጊዜ የዘገየውን ፕሬዝዳንታዊ እና የፓርቲዎች ምርጫ ለማካሄድ ስትዘጋጅ ቆይታ ዛሬ ሌላኛውን ዙር ምርጫ ታካሄዳለች።
ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩ ሲሆን፣ እርሳቸውን በመቀናቀን ደግሞ የዋዳኒ ፓርቲ ተወካዩ አብድራህማን አሕመድ አብዱላሂ እና የጀስቲስ ኤንድ ዴቨሎፕምንት ፓርቲ ተወካዩ ፈይሰል አሊ ወራቤ ይፎካከራሉ።
ላለፉት 33 ዓመታት የዓለም አቀፍ እውቅናን ለማግኘት እየጠየቀች ያለችው እና ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ እንዳላት የሚገመተው ሶማሊላንድ የብዝሃ ፓርቲ ሥርዓት ትከተላለች።
ይህ የሶማሊላንድ ምርጫ የሚካሄደው በምላሹ የአገርነት ዕውቅናን ለማግኘት ለኢትዮጵያ የባሕር በር በኪራይ ለመስጠት የፈረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር የገባችው ፍጥጫ በተካረረበት ወቅት ነው።
በ1980ዎቹ ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የዚያድ ባሬ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ሶማሊያ ቀውስ ውስጥ ስትገባ ሶማሊላንድ ራሷን ከሶማሊያ መነጠሏን ብታስታውቅም፤ የሶማሊያ መንግሥት ግን የግዛቱ ዘካል አድርጎ አሁን ድረስ ይመለከታታል።
እንደ ሶማሊላንድ ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን መረጃ መሠረት ከአንድ ሚሊዮን በላይ መራጮች ተመዝግበው በቀጣይ አምስት ዓመት የሚመራቸውን ፕሬዝዳንት እና በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ የሚሳተፉ ፓርቲዎችን ለመምረጥ ተዘጋጅተዋል።
ለፕሬዝዳነትነት የሚፎካከሩ ሦስት ዕጩዎች ለመራጮቻቸው የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ለማሻሻል፣ ዓለም አቀፍ እውቅና ለማስገኘት እንዲሁም በአገሪቱ ያለውን ዲሞክራሲ ማስፋት ይጠበቅባቸዋል።
ሶማሊላንድ ራሷን የቻለች አገር መሆኗን ካወጀች ወዲህ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ስታካሄድ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ነው።
ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ሶማሊያ በጦር አበጋዞች ግጭት እንዲሁም በእስላማዊው ቡድን አልሻባብ በምትታመስበት ጊዜ ሶማሊላንድ የተረጋጋች ሆና ለመዝለቅ ቆይታለች።
በዚህም በአግባቡ የመንግሥትን ሥራ የሚያቀላጥፉ ተቋማት፣ ዲሞክራሲያዊ ሽግግርን የሚያሳልጥ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የራሷ ገንዘብ እንዲሁም ፓስፖርት እና የፀጥታ ኃይል ያላት አገር ለመሆን ችላለች።

የፎቶው ባለመብት, BBC/GETTY/FB
ዛሬ በሚካሄደው የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የገዢው ፓርቲ ኩልሚዬን ከ2010 ጀምሮ ሊቀመንበር ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አብዲ፣ የዋዳኒ ፓርቲ ዕጩው አብድራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ ወይንም በቅጽል ስማቸው “ኢሮ” እንዲሁም ፈይሰል አሊ ወራቤ ከጀስቲስ ኤንድ ዴቬሎፕምንት ፓርቲ ይሳተፋሉ።
ተማራጮቹ በአገሪቱ ያለውን ዲሞክራሲ ለማጠናከር፣ የምጣኔ ሀብት እድገቱን ለማፋጠን፣ እንዲሁም እንደ አገር ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና እንዲያገኙ ማድረግ ከአጀንዳዎቻቸው መካከል ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን በምርጫ ቅስቀሳዎቻቸው ወቅት ተናግረዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 ተመርጠው የፕሬዝዳንትነት ሥልጣኑን የያዙት ሙሴ ቢሂ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር የገቡት ስምምነት እንደሚቀጥል እና አገራቸው እውቅና እንደምታገኝ ቃል ገብተዋል።
ሶማሊላንድ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ለደጋፊዎቻቸው የሚናገሩት ፕሬዝዳንቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚጠበቅበትን እስከሚያደርግ እየጠበቁ መሆኑን አብራርተዋል።
“ኢትዮጵያ የባሕር በር ማግኘት ትፈልጋለች፤ እኛ ደግሞ እውቅና ማግኘት እንፈልጋለን ስምምነቱ ይህንን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ነው” ሲሉ ነበር በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የተናገሩት።
ለ11 ዓመታት የአገሪቱ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት የዋዳኒ ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ አብድራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ፣ አገራቸው ዓለም አቀፍ እውቅና እንድታገኝ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።
አገራቸው ከዚህ ቀደም ከሶማሊያ መንግሥት ጋር ነጻ አገር መሆኗን በሚመለከት ያደረገቻቸውን ያልተሳኩ ንግግሮችን መለስ ብሎ ማየት እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ፕሬዝዳንታዊ ዕጩው፣ ከሶማሊያ ጋር ተቀምጦ መነጋገር እንደሚያስፈልግ ከተመረጡም ይህንኑ እንደሚያደርጉ ይናገራሉ።
የሶማሊላንድ የቀድሞ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የዋዳኒ ፓርቲ ሊቀመንበር ሞሐመድ አብዱላሂ አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ስለፈረመችው የመግባቢያ ስምምነትን በሚመለከት በተጠየቁበት ወቅት፣ ሱማሊላንድ ከማንኛውም አገር ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት የማድረግ መብት እንዳላት መናገራቸው ይታወሳል።
የጀስቲስ ኤንድ ዴቬሎፕምንት ፓርቲ ፕሬዝደንታዊ ዕጩ ወራቤ በበኩላቸው ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት በመመሥረት ለእውቅና እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።
“ላለፉት ሰባት ዓመታት ሥልጣን ላይ የነበሩት ፕሬዝዳንት ቢሂ እና ፓርቲያቸው ወደ ሥልጣን ዳግም ከተመለሱ ለሶማሊላንድ መራጮቸ ጥሩ አማራጭ አይደለም. . . ከተመረጥኩ ሶማሊላንድ በተሻለ የብልጽግና መንገድ እውቅና እንድታገኝ እሰራለሁ” ብለዋል።
የቢሂ ተፎካካሪ ሆነው የቀረቡት ፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች፣ አብድራህማን ሞሐመድ አብዱላሂ እና ፋይሳል አሊ ዋራቤ፣ ሶማሊያን ያስቆጣውን አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ላይ ተቃውሞ አላቀረቡም።
ነገር ግን ቢሂን ሶማሊላንድ ውስጥ መከፋፈል በመፍጠር፣ በግጭት እና በዋጋ ንረት ያብጠለጥሏቸዋል።
ሶማሊላንድ የመጨረሻውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ያካሄደችው እንደ አውሮፓውያኑ በ2017 ነው።
የፕሬዝዳንት ቢሂ የሥልጣን ዘመን በኅዳር ወር 2022 ከማለቁ በፊት የአገሪቱ የምርጫ ቦርድ በገንዘብ እና ቴክኒካዊ ጉዳዮች ምርጫውን በማራዘሙ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሥልጣን ዘመናቸውን ለሁለት ዓመት ያህል አራዝመውላቸዋል።
በወቅቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ዋዳኒ እና ዩሲአይዲ ከዚህ በኋላ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት አድርገው እንደማይቀበሏቸው አሳውቀው ነበር።
በሶማሊላንድ ሕገ መንግሥት መሠረት አንድ ፕሬዝዳንት በሁለት የምርጫ ዘመን መመረጥ ይችላል።
ሶማሊላንድ ወሳኝ ወደ ሆነው የቀይ ባሕር መስመር መግቢያ በመሆነችው በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ በአፍሪካ ቀንድ ስትራተጂክ ቦታ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ ሰፊ የባሕር ጠረፍ ያላት አገር ናት።
ምንም እንኳን ከየትኛውም አህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊ እና ከአገራት ዕውቅናን ባታገኝም የአካባቢው እና ሌሎች አገራት ሶማሊላንድ ባላት ቁልፍ ቦታ ምክንያት በቅርበት የሚከታተሏት ናት።
አሁን የምታካሂደው ምርጫ እንደከዚህ ቀደሞቹ በተሳካ መንገድ በዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የሚጠናቀቅ ከሆነ የበለጠ ተቀባይነቷን የሚያጠናክረው ሲሆን፣ በቀውስ ለሚታመሰው የአፍሪካ ቀንድም ተስፋ ትሆናለች።
ለፕሬዝዳንትነት ከሚፎካከሩት ዕጩዎች መካከል የትኛውም በምርጫው ቢያሸንፍ ከዓላማዎቹ አንዱ የሶማሊላንድን ዕውቅና ማረጋገጥ በመሆኑ እንደ አገር ለመታወቅ የምታደርገው ጥረት መቀጠሉ አይቀርም።
በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ጋር የተደረሰው የመግባቢያ ሰነድ ለዚሁ ዓላማ ፈር ቀዳጅ በመሆኑ ወደ ተግባር ለማሸጋገር ወደ ኋላ የሚሉ አይሆኑም።












