የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል “ሥራውን ለመሥራት” የተወካዮች ምክር ቤትን እገዛ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, hopr/fb
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በትግራይ ክልል አጀንዳ እና ተሳታፊዎችን ለመለየት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን እገዛ እንደሚፈልግ ገለጸ።
የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው “[አስቻይ] ሁኔታ ለመፍጠር ጠንካራ ሥራ በጋራ ተቀናጅተን እንሠራለን። ከክልሉም ጋር እንመካከራለን” ብለዋል።
ከሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወራት በፊት የተቋቋመው የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዛሬ ማክሰኞ ኅዳር 10/2017 ዓ.ም. የአፈጻጸም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ኮሚሽኑ ያከናወናቸውን እና ቀሪ ሥራዎች ለምክር ቤት አባላት አብራርተዋል።
“ዛሬ ላይ ለእናንተ ሥራችንን ጨርሰን የምንወጣበት [exist] የምናደርግበትን ሪፖርት ነበር ማቅረብ ያለብን” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ተቋማቸው ይህን እንዳያደርግ ምክንያት የሆኑ ክፍተቶችን ዘርዝረዋል።
“ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ ቦታዎች ያጋጠሙት ሁኔታዎች” ከእነዚህ ክፍተቶች መካከል መሆናቸውን ፕ/ር መስፍን ገልጸዋል።
“ምዕራብ ኢትዮጵያ ችግር በነበረበት ወቅት ነው የእኛ ሥራ የተጀመረው” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ “ምዕራብ ኦሮሚያ በተመሳሳይ መልኩ ችግሮች ያጋጥማሉ። አማራ ስንጀምር ችግር አልነበረም፤በአሁኑ ሰዓት ግን አስቻይ ሁኔታ እና አንጻራዊ የሆነ ሰላም ያስፈልጋል” ብለዋል።
ፕሮፈሰር መስፍን ምዕራብ ኢትዮጵያ ነበር ያሉት ችግር ተቀርፎ ኮሚሽኑ በቤኒሻነጉል ጉሙዝ እና በጋምቤላ ክልሎች ሥራውን ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቁን ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታም ፕ/ር መስፍን በሪፖርታቸው ጠቅሰውታል።
ዋና ኮሚሽነሩ “የትግራይ አረጓዴ መብራት አግኝተን ሙሉ በሙሉ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፤ ግን በዚያ በኩል ደግሞ የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፤ ይህ እንግዲህ የሕዝብ ተወካዮች ኃላፊነት ነው ብለን ነው የምናምነው” ብለዋል።
“[ከትግራይ ክልል] ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጋር የተወሰነ ጊዜ በመውሰድ መክረናል” ያሉት ፕ/ር መስፍን፤ “በዚያ ምክክር ላይ የተግባባነው ነገር ቢኖር ይህን የአገራዊ ምክክር ሂደት በእርግጥም እንደሚያምኑበት. . . የአገራዊ ምክክር ሂደትን በመርኅ እንደሚቀበሉት እና ተገቢ እንደሆነ ነግረውናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, hopr/fb
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “ሁኔታዎች በሚመቻቹበት ጊዜ ካቢኔውን እና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንደምናነጋግር እና እንደሚያገናኙን ቃል ገብተውልን ነበር” ብለዋል።
ከፕሬዝዳንቱ ጋር ተደጋጋሚ ስብሰባዎች መደረጋቸውን የጠቀሱት ፕ/ር መስፍን ለምክር ቤት አባላቱ “ግልጽ በሆነ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ወደ ትግራይ የገባንበት አካሄድ የለም” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት “ግልጽ ናቸው” ያሏቸውን ምክንያቶች ግን አልዘረዘሩም።
ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ነዋሪዎች ጋር ውይይቶችን ባያደርግም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና በክልሉ ከሚገኙ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ጋር ውይይቶች መደረጋቸውን ዋና ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።
ፕ/ር መስፍን ሪፖርታቸውን ካቀረቡ በኋላ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
የቀረቡት ጥያቄዎች በዋናነት ከታጠቁ ቡድኖች ተሳትፎ፣ የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን እንዲሁም የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የትግራይ ክልል ተሳታፊዎች እና አጀንዳ ልየታ ላይ ያተኮሩ ነበሩ።
እታፈራሁ ዘገየ የተባሉ አንዲት የምክር ቤት አባል፤ “ቀጣይ በቀሩት ሦስት ወራት እነዚህ የተሰባሰቡ አጀንዳዎች ተጨምቀው እንደ አገር ሊያግባቡን እና አንድ ሊያደርጉን የሚችሉትን ለይቶ በማቅረብ የእናንተ ሂደት ምንድን ነው? ቀሪዎቹንስ በእነዚህ ወራቶች ማጠናቀቅ ትችላላችሁ ወይ?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል።
ሌላኛው የምክር ቤት አባል ዶ/ር ብዙአየሁ ደገፋም በተመሳሳይ “አሁንስ በምን ያህ ጊዜ ውስጥ ነው የቀረውን አጀንዳዎች ሰብሰብን የምክክር ሂደቱን የምናጠናቀቅው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ዶ/ር ብዙአየሁ አክለውም “በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጋር ለሦስተኛ ዙር ድርድር እንዲቀመጡ እና በአማራ ክልል የታጠቁ ኃይሎችም ስላሉ እነሱም ወደ ድርድር መጥተው የምክክር ኮሚሽን ሥራው እንዲሳካ ምን እየሠራችሁ ነው?” የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል።
ፕ/ር መስፍን በቀሩት ሦስት ወራት ውስጥ አወያይታችሁ፣ ምክረ ሃሳብ ሰብስባችሁ ሪፖርት በማቅረብ ታጠናቅቃላችሁ ወይ ለሚለው ጥያቄ “እኛ የካቲት 14/2014 ቃለ መሃላ ስንፈጽም ከአንድ ሰዓት በኋላ አፈ ጉባኤው በመሩት ስብሰባ ላይ ተገኝተን ስንነጋገር ቃል የገባነው በሦስት ዓመት ውስጥ ሥራችንን ልንጨርስ ነው። ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ሥራችንን እየሠራን አገባደን እናንተ ፊት መቅረብ ነው የእኛ አጀንዳ” ሲሉ መልሰዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም “ጊዜን በተመለከተ እኛ ይሄን ያህል ጊዜ ይሰጠን ወይም እንዲህ ይደረግልን ለሚለው ጥያቄ አይደለም ዝግጁነታችን። እኛ ዝግጁነታችን አሁንም በዚህ በቀረን ጊዜ ሠርተን የት መድረስ እንችላለን የሚል ነው” ብለዋል።
የኮሚሽኑን የሥራ ጊዜ ማራዘምን በተመለከተም፤ “ስታቋቁሙ እናንተ ናችሁ ያቋቋማችሁት፤ ሦስት ዓመት ብላችሁ የወሰናችሁት እናንተ ናችሁ። ከዚህ በኋላ ይብቃኝ ማለት መብት አላችሁ፣ ይቀጥል ማለት መብት አላችሁ። ስለዚያ ምንም እኛ የምንለው ነገር የለም። ነገር ግን በጊዜ ሂደት ከአፈ ጉባኤው እና ከሚመለከታችሁ አመራሮች ጋር ቁጭ ብለን በዝርዝር የምናስረዳበት ሂደት ግን አለ” ሲሉ አብራርተዋል።
ከግጭት ጋር በተያያዘ ለተነሱት ጥያቄዎች ደግሞ ምክትል ኮሚሽነሯ ሂሩት ገብረሥላሴ፤ “የእኛ ኃላፊነት እንዲህ ዓይነት ግጭቶች ውስጥ በመግባት የማደራደር ሥራ የመሥራት አይደለም። ነገር ግን እኛ ለማካሄድ ለተዘጋጀንበት አገራዊ ምክክር ሰላማዊ ዓውድ ቢኖር ይበጃል እና ሁሉንም ፓርቲዎች ወደ ሰላማዊ ሂደት እንዲመጡ እንጋብዛለን ከዚያ ውጪ እንደ ኮሚሽን የምንወስደው ኃላፊነት አይደለም” ብለዋል።
ምክትል ኮሚሽነሯ አክለውም፤ “አማራ ክልል ገብተን በቅርቡ መሥራት እንደምንችል በጣም ተስፋ እናደርጋለን ዕቅድ አለን።ሥራው ተጀምሯል። የትግራይ ክልልን ለእናንተ እጅ እንተወዋለን፤ የእናንተን እገዛ የሚፈልግ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።












