ከፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት በኋላም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው የኢሮብ ሕዝብ

የኢሮብ አካባቢ ነዋሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢሮብ አካባቢ ነዋሪ (ፎቶ ፋይል)

በትግራይ ክልል ምሥራቃዊ ዞን በሚገኘው የኢሮብ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን ላለፉት ሁለት ዓመታት ከደውሃን ከተማ ወደ አዲግራት በሚወስደው እጅግ አስቸጋሪ እና ገደላማ መንገድ እየተመላለሱ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሰጣሉ።

በአካባቢው ጥሩ የዝናብ መጠን ስለነበረ ሕብረተሰቡ በአቅሙ በማረስ እና እህል በመዝራት ጥሩ ምርት እንደሚያገኝ ከመጠበቁ ባሻገር ያለው ሁኔታ ግን “እጅግ መጥፎ” ነው ይላሉ።

የኢሮብ ወረዳ በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት በክልሉ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።

የእርስ በእርስ ጦርነቱ ከሁለት ዓመት በፊት በተዋጊ ኃይሎች መካከል የተደረሰውን ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ቢቆምም ጦርነቱ ያስከተላቸው ቀውሶች አሁንም ጉዳት እያደረሱ ነው።

ኢሮብ ወረዳ ጨምሮ በሌሎች የትግራይ ክፍሎችን ተኩስ ቢቆምም በሕክምና እጦት እና በሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች ምክንያት የሚከሰት የሰዎች ሞት እና መፈናቀል መቀጠሉን ቢቢሲ ከወረዳው ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

“ተስፋችን በሰማይ ነው”

የኢሮብ ወረዳ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከጣልያን ቅኝ ግዛት ጀምሮ የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱበት ድንበር አካባቢ የሚገኝ ነው።

በህወሓት እና በመንግሥት መካከል ጦርነት በተቀሰቀሰበት ጊዜ ከኢትዮጵያ ጦር ጎን ተሰልፈው የተዋጉት የኤርትራ ወታደሮች ወረዳውን እንደተቆጣጠሩት ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በዚህም በአሁኑ ወቅት ወርዓትለ፣ እንዳልጌዳ፣ ከፊል የዓገራለ እና ዓሊቴና አካባቢዎች በኤርትራ ጦር ቁጥጥር ሥር መሆናቸውን ጨምረው አመልክተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኤርትራ መንግሥት ግን ወታደሮቹ የሚገኙት የግዛቱ አካል ተብለው በተወሰኑለት አካባቢዎች ውስጥ መሆናቸውን በመግለጽ በተለያዩ ጊዜያት ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ አብዛኞቹ የወረዳው ነዋሪዎች ወደ አዲግራት እና መቀለ ከተሞች የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ባሉት ባለፉት ሁለት ዓመታት በፀጥታ እና በማኅበራዊ አገልግሎቶች ዙሪያ ምንም ዓይነት መሻሻል አለመኖሩን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጦርነቱ የወደሙ እና የተዘረፉ ጤና ጣቢያዎች ዳግም እንዳልተገነቡ፣ የመድኃኒት እጥረት እንዳለ እና የአካባቢው አስተዳደርና ፀጥታ ወደ ቀድሞ ሁኔታው እንዳልተመለሰ ይጠቅሳሉ።

“የኢሮብ ሕዝብ ሁኔታ ያሳዝናል” የሚሉት ካህኑም “ወደ መቀለ እና አዲግራት የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት 90 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ እጅግ አስከፊ መንገድ ተጉዘን፣ የአሲምባ ተራራ ተሻግረን ነው አዲግራት መድረስ የምንችለው” ይላሉ።

ከጦርነቱ በፊት የወረዳው ሕዝብ ለገበያ እና ሌሎች ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የሚጠቀምበት አንድ የጠጠር መንገድ ብቻ ነበር።

አሁን ይሄ መንገድ የሚያልፍበት መሬት “የኤርትራ ነው” በሚል “በኤርትራ ኃይሎች በመዘጋቱ ምክንያት ነው ረጅም መንገድ ተዟዙረን የምንወጣው እና የምንገባው” ሲሉ ያስረዳሉ።

ደውሃን ከአዲግራት በ45 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ከተማ ናት።

ከዚህ ቀደም ለትራንስፖርት ከ80 እስከ 90 ብር ይከፈልበት የነበረው ጉዞ አሁን ከመደበኛው ታሪፍ ውጪ 1,000 ብር እና ከዚያ በላይ እንደሚጠየቅበት ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፕሪቶሪያ ስምምነት “ሊያጠፋን የሚችለውን የጦርነት ማዕበል እንዲቆም ማድረጉ መልካም ነገር ነው” ሲሉ አንድ የወረዳው ነዋሪ ይናገራሉ።

እኚህ አካባቢው ላይ ባለው የፀጥታ ሁኔታ ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ግለሰብ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ግን ምንም ዓይነት መሻሻል አለመኖሩን ይናገራሉ።

“አሁን ኢሮብ ውስጥ የወደሙ ቤቶች፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የጤና ጣቢያዎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ውሃ መስመሮች ናቸው በየቦታው የሚታዩት።”

የሕብረተሰቡ ማኅበራዊ ሕይወት እና አብሮነት “ለመበታተን የተጋለጠ ነው” የሚሉት እኚህ ግለሰብ፣ በአካባቢው በቂ የፀጥታ፣ የሰብአዊ ድጋፍ፣ የማኅበራዊ አገልግሎት፣ የትራንስፖርት እና የጤና አገልግሎት አቅርቦት የለም ብለዋል።

“ሁሌም ያለንበት ሁኔታ ‘መቼ ይሆን የሚያበቃው?’ እያልን ወደ ሰማይ እንጸልያለን። አዝመራ በሚሰበሰብበት ወቅት ሰዎች የዘሩትን ሳያጭዱ ሽሽት ላይ ናቸው። እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚያረጋጋ ነገር ካልፈጠረ በስተቀር ተስፋ የለም። የምናየው የመንግሥት መረጋጋት እጦት፣ መበታተን እና ተስፋ መቁረጥ ብቻ ሆኗል” ሲሉ ይናገራሉ።

ይህ ዓይነቱ ስሜት በሁሉም የአካባቢው ሕዝብ ላይ እንደሚታይ የሚናገሩት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን፣ “በሕይወት እንዲቀጥሉ ግን ‘ክርስቲያን ተስፋ አይቆርጥም’ እያልን ሞራል ለመስጠት እየታገልን ነው። እምነታችን ከሰማይ እንጂ በምድር ላይ የሚታይ ምንም ተስፋ የለንም” በማለት በሁኔታው እንደሚያዝኑ ገልጸዋል።

አብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ጦርነቱ እና ሌሎች ችግሮች ባደረሱት ጉዳት ምክንያት ለሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ መጋለጡን ጠቅሰዋል።

“የወሲብ ጥቃት የተፈፀመባቸው፣ ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው አሉ። [በአካባቢው] ልጆቻቸው በጦርነቱ የተገደሉባቸው ከ500 በላይ ወጣት ቤተሰቦች መርዶ ተነግሯቸዋል። ስለዚህ ሕዝቡ በአካል፣ በመንፈሳዊ፣ በኢኮኖሚ እና በአስተዳደራዊ ችግሮች ውስጥ ነው ያለው።

“ሰዎች በዋነኛነት በሕክምና እጦት ምክንያት እየሞቱ ነው። ዛሬ [ባለፈው ሳምንት የተደረገ ቃለ ምልልስ ነው] ባስፈጸምኩት የቀብር ሥነ ሥርዓት ሁለቱም በመድኃኒት እጦት ነው የሞቱት። ከፕሪቶሪያ በኋላ ተኩስ ብቻ ነው የቆመው እንጂ የሰላም እጦት፣ የሥነ ልቦና ጉዳት እና ሐዘን አልቆመም።”

ከዚህ ባለፈም ወጣቶች ወደ ሊቢያ እና የመን በመሰደድ በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች ምክንያት የዝርፊያ፣ የአፈና እና ግድያ ሰለባ እየሆኑ መሆኑን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የወረዳው ነዋሪዎች ይጠቁማሉ።

“እያንዳንዱ ወጣት፣ አረጋውያን ወላጆቹን በቤት ውስጥ ትቶ ነው ወደ ስደት እያመራ ያለው። እነዚህ ወጣቶች የመን ሲደርሱ ከፍተኛ ገንዘብ ይጠየቃሉ፤ አንድ ሰው ቢያንስ 1.7 ሚሊዮን ብር እየተጠየቀ ነው” ብለዋል።

“ፈጣሪ ከእኛ ጋር እንዳለ እናምናለን፤ በዓለማዊው ግን ምንም ተስፋ የሚሰጠን ኃይል አላየንም። በወረዳው መልካም ነገር አገኘን የምንለው ነገር ቢኖር ባለፈው የክረምት ያገኘነው ዝናብ ነው፤ ለከብቶች ሳር አገኘን። በዘር እጦት ምክንያት መሬታቸውን ሳያርሱ የቀሩ አሉ፤ የቻሉ ግን ትንሽም ቢሆን አግኝተዋል። ይሁን እንጂ በሙሉ ልብ ማምረት አልቻሉም። ሁልጊዜም ስጋት ላይ ናቸው” ይላሉ።

ተፈናቃዮች የሚኖሩበት መጠለያ

የፎቶው ባለመብት, Goitom

የምስሉ መግለጫ, ተፈናቃዮች የሚኖሩበት መጠለያ

የአልጀርስ ስምምነት ምን ነበር?

በአውሮፓውያኑ ከ1998 - 2000 በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል በተፈጠረው የድንበር ውዝግብ ምክንያት ደም አፋሳሽ ጦርነት ተካሂዶ በአልጀርስ ስምምነት ጦርነቱ ቆሞ፣ የድንበር ይገባኛል ጉዳዩ ወደ በፍርድ ቤት መሄዱ ይታወሳል።

በዚህም ፍርድ ቤቱ የድንበር ጦርነቱ ምክንያት ናት የምትባለው ባድመ ከተማን ለኤርትራ ሲወስን፣ የተለያዩ የድንበር አካባቢዎችን በተመሳሳይ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ እንዲካተቱ አድርጎ ነበር።

ቢሆንም ግን ውሳኔው ከግንዛቤ ያላስገባቸው ጉዳዮች አሉ በሚል የኢትዮጵያ መንግሥት የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ሳያደርግ ለሁለት አስርት ዓመታት ሰላምም ሆነ ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ቆይተዋል።

ምንም እንኳን የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ለ20 ዓመታት ያህል የኢትዮጵያ ጦር በኢሮብ ወረዳ በሰፈረበት ጊዜ አንፃራዊ መረጋጋት እንደነበረ አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጦርነቱን ተከትሎ በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ የደን ውድመት እና ሌሎችም ማኅበራዊ ችግሮች ሲከሰቱ ቆይተዋል። በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ተባብሶ የከፋ መሆኑን ይናገራሉ።

“በኤርትራ ጦር በተያዙ አካባቢዎች ወጣቶች በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጠርጥረው ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ ይገደላሉ። ይህ እየሆነ ያለው በዓራገለ ቀበሌ እንዲሁም በእንዳልጌዳ ነው። ከዚህ በባሰ መልኩ ሕዝቡ ተበታትኖ በቂ እርዳታ በማያገኝበት ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው።”

ቢቢሲ ይህንን በገለልተኛ አካል አላረጋገጠውም። የኤርትራ መንግሥት በሠራዊቱ ቁጥጥር ሥር ናቸው ስለሚባሉ አካባቢዎች ምንም ዓይነት መረጃ አልሰጠም።

ነዋሪዎች ግን “ትልቁ ጭንቀታችን ደኅንነት ነው። የሰዎች መፈናቀል ነው እያየን ያለነው። እርሻቸውን ጥለው የሚሸሹና ተስፋ ያጡ ሰዎች ብዙ ናቸው። የተረጋጋ መንግሥ እና እርዳታ የተነፈገው ሕዝብ ሆነን ነው ያለነው” ይላሉ።

ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ በጊዜያዊ አስተዳደር የሚመራው የትግራይ መንግሥት በህወሓት አመራሮች መካከል በተፈጠረው ውዝግብ ምክንያት ቀውስ ውስጥ ገብቷል። ክልሉ ተመልሶ ወደ አላስፈላጊ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ ስጋት አላቸው።

በኢሮብ ወረዳ የሚኖሩት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ካህን በመሪዎች መካከል የሚታየው ችግር ሕብረተሰቡ ዘንድ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ በመግለጽ “አሁን ምንም ብሩህ ተስፋ አይታየኝም” ብለዋል።

“እስካሁን ድረስ እምነታችን ከሰማይ እንጂ ከምድር አይደለም” ሲሉም ይገልጻሉ።