አያቶላህ አሊ ኻሜኒን የሚተካው ቀጣዩ የኢራን ጠቅላይ መሪ ማን ሊሆን ይችላል?

ሞጅታባ ኻሜኒ፣ አሊሬዛ አራፊ፣ ሐሳን ኾሜኒ፣ ሞሐመድ መህዲ ሚርባቄሪ፣ ሐሺም ሁሴይኒ ቡሼህሪ እና ሞህሲን አራኪ
የምስሉ መግለጫ, ሞጅታባ ኻሜኒ፣ አሊሬዛ አራፊ፣ ሐሳን ኾሜኒ፣ ሞሐመድ መህዲ ሚርባቄሪ፣ ሐሺም ሁሴይኒ ቡሼህሪ እና ሞህሲን አራኪ
የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በአሜሪካ እና በእስራኤል የአየር ጥቃት ቅዳሜ የካቲት 21/2018 ዓ.ም. ተገድለዋል።

የ86 ዓመቱ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የእስላማዊ ሪፐብሊክ መሥራች የሆኑትን አያቶላህ ሩሆላ ኾሜኒን ተክተው ከአውሮፓውያኑ 1989 ጀምሮ ሥልጣን ላይ ቆይተዋል።

ከዚህ በፊት ደግሞ ለሁለት የሥልጣን ዘመናት ከ1981 እስከ 1989 ድረስ አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።

የኢራን መንግሥት የጠቅላይ መሪውን ሞት ካረጋገጠ በኋላ ለ40 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን እንዲሁም ለሰባት ቀናት ሥራ ዝግ እንዲሆን አውጇል።

የአሊ ኻሜኒን ሞት ተከትሎ እርሳቸውንም ሆነ ሌሎች የአገሪቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ማን ይተካቸዋል የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል።

የኢራን አብዮት ከአውሮፓውያኑ 1979 ወዲህ በጥር ወር የተካሄደውን ሕዝባዊ አመጽ ጨምሮ እጅግ አደገኛ የተባለ የኅልውና አደጋ አጋጥሞታል።

የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ

የፎቶው ባለመብት, KHAMENEI.IR

የምስሉ መግለጫ, የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ

የኢራን ሕገ መንግሥት ምን ይላል?

በኢራን ሕገ መንግሥት ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ቀጣዩ መሪ የሚመረጠው ከፍተኛ መንፈሳዊ እና ፖለቲካዊ ሥልጣን ባላቸው የባለሙያዎች ጉባዔ (Assembly of Experts for Leadership) ይሆናል።

ይህ የባለሙያዎች ጉባዔ በየስምንት ዓመቱ የምክር ቤቱ ጠባቂዎች በሚል የሚመረጡ 88 ከፍተኛ የሃይማኖት አባቶች አሉት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እነዚህ የሃይማኖት አባቶች አክራሪ አቋም ያላቸው የበላይ ባለሥልጣናት ሲሆኑ፣ የሚቀርቡላቸውን ሁሉንም ዕጩዎች አብጠርጥረው ይመዝናሉ።

በ2024 በተደረገው ምርጫ የጠቅላይ መሪው ታማኝ የሆኑ ቡድኖች ሁሉንም መቀመጫዎች አሸንፈዋል።

አራት የጉባዔው አባላት በሞት በመለያታቸው የተነሳ መቀመጫዎቹ እስካሁን ድረስ ክፍት ናቸው።

እነዚህ ክፍት ቦታዎች በ2026 ግንቦት ወር በሚካሄድ ምርጫ ይሞላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአገሩቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 111 አዲስ መሪ እስኪመረጥ ድረስ የጠቅላይ መሪውን ኃላፊነት በጊዜያዊነት ሦሰት አባላት ያሉት ምክር ቤት እንደሚረከብ ይገልጻል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ ጎላምሆሴይን ሞህሴኒ ኢጄ እና የበላይ ምክር ቤት አባል ከሆኑ መካከል አንድ የሃይማኖት መሪ የሚካተቱበት ነው።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ሦስተኛ አባል የሚሰየመው ከፍተኛ ሥልጣን ባለው በሳዴቅ አሞሊ ላሪጃኒ የሚመራ ከፍተኛ የግልግል ምክር ቤት (Expediency Discernment Council) ነው።

ይህ የግልግል ምክር ቤት የኢራን ከፍተኛው የሥልጣን አካል በሆኑት መካከል አለመግባባት ሲከሰት ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን አባላቱም በበላይ መሪው የሚሾሙ ናቸው።

የካቲት 22/2018 ዓ.ም. ወግ አጥባቂ የሆኑት አሊሬዛ አራፊ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክር ቤት ሦስተኛ አባል ሆነው የተሾሙ ሲሆን፣ ጠቅላይ መሪውን ከሚተኩ ሰዎች መካከል ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የሳዴቅ ላሪጃኒ ወንድም እና የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፀሐፊ የሆኑት አሊ ላሪጃኒ ለአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ምክር ቤቱ የካቲት 22/2018 ዓ.ም. ጉባዔውን ያካሄዳል።

በዚያው ዕለት ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን ምክር ቤቱ ሥራውን መጀመሩን ተናግረዋል።

ምንም እንኳን አዲስ መሪ ይሰየማል ተብሎ የሚጠበቀው የባለሙያዎች ምክር ቤት ጉባዔ ወዲያውኑ ሥራውን ቢጀምርም እስከ መቼ ድረስ ለሚለው በሕጉ ላይ የተቀመጠ ቀነ ገደብ ግን የለም።

ጠቅላይ መሪው በኢራን የፖለቲካ ሥልጣን የመጨረሻው አካል ነው

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ መሪው በኢራን የፖለቲካ ሥልጣን የመጨረሻው አካል ነው

ማንኛውም ተመራጭ የመራጮቹን ሁለት ሦስተኛ ድምጽ ማግኘት ካልቻለ የጊዜያዊ ምክር ቤቱ አገሪቱን ማስተዳደር ይቀጥላል።

ምንም እንኳን ሁሉም አባላቱ ለኻሜኒ ታማኝ ቢሆኑም ለውጥ ፈላጊ የሆኑት ፕሬዚዳንት ፔዜሽኪያንን የመሰሉ ሰዎች መኖራቸው በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ ለውጥ ያመጣል።

የጉባዔው ውሳኔ ቀጣዩን ጠቅላይ መሪ ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ እንዲሁም ከኻሜኒ የውስጥ አጋሮች እና ጽህፈት ቤቶች ጋር በጥምረት መሥራት ይጠይቃል።

ከኻሜኒ ጋር በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቢገደሉም በሕይወት ያሉ የአብዮታዊ ዘብ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጦርነት ውስጥ ያለችውን አገራቸውን በመምራት ረገድ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

የሃይማኖት አባቶቹ መደበኛ የሆነ ሥልጣን ቢኖራቸውም ኻሜኒን የሚተካው ግለሰብ የወታደራዊ ተቋሙ እና የደኅንነቱ ተቀባይነት ያስፈልገዋል።

በባለሙያዎች ጉባዔ ስር ሦስት አባላት ያሉት ንዑስ ኮሚቴ እጅግ ምሥጢራዊነቱን በጠበቀ መልኩ በቀረቡለት የዕጩዎች ዝርዝር ላይ እየመከረ መሆኑ ተገልጿል።

ነገር ግን ምስጢራዊነቱ የበለጠ ለጥርጣሬ በር የሚከፍት ሆኗል።

 ሞጅታባ ኻሜኒ

የፎቶው ባለመብት, DPA/Alamy Live News

ልጃቸው ሊተካቸው ይችላል?

ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ተደማጭነት ያለው እና ብዙ ጊዜ ከጀርባቸው እንደነበር የሚገለጸው ሞጅታባ ኻሜኒ አባቱን ሊተካ ይችላል በሚል የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረትን ስቦ ቆይቷል።

የአባቱን ቢሮ በማስተዳደር ባለው ሚና የሚታወቀው ሞጅታባ ኻሜኔ "የአባቱን ቀጠናዊ እና ጨቋኝ የአገር ውስጥ ዓላማዎችን" በማራመድ ረገድ በተጫወተው ሚና በዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ተጥሎበታል።

የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ኻሜኒ፣ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ይተኳቸዋል ተብሎ ከሚጠቀሱ ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ስሙ ይገኛል።

በተለይም ከፕሬዝዳንት ራይሲ ሞት በኋላ ከፊት ካሉት ዕጩዎች መካከል አንዱ መሆኑ ይነገራል።

ነገር ግን አባቱ ከተገደሉ በኋላ ባለቤቱ ከሞቱት ሰዎች መካከል አንዷ መሆኗ ቢገለጽም የእርሱ ሁኔታ ግን እስካሁን ድረስ ግልጽ አይደለም።

ከዚህ ቀደም አያቶላህ ኻሜኒም ሆኑ አያቶላህ ኾሜይኒ በዘር የሚወረስ ሥልጣንን ይተቹ ነበር።

በዚህም የተነሳ ኻሜኒ ልጃቸው እንዲተካቸው የሚቀርበውን ሃሳብ አጥብቀው ውድቅ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ሌሎች ዕጩዎች እነማን ናቸው?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከወግ አጥባቂም ሆነ ከለዘብተኛ ወገን ያሉት ፖለቲከኞች ወደ ጎን ገሸሽ ተደርገው ነበር።

ከእነዚህም መካከል የፍትሕ ሚኒስትሩ ሳዲቅ አሞሊ ላሪጃኒ እንዲሁም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሃሳን ሮሃኒ ይገኙበታል።

የባለሙያዎች ጉባዔ አባል የሆኑ የተወሰኑ ሰዎች ጠቅላይ መሪውን ይተካሉ ተብለው በዕጩነት ከቀረቡ ሰዎች መካከል ናቸው።

ከእነዚህመ መካከል በጊዜያዊ መሪዎች ምክር ቤት ውስጥ እንዲሳተፉ የተመረጡት አራፊ አንዱ ናቸው።

የ66 ዓመቱ የሕግ ባለሙያ በኻሜኒ በኢራን ሃይማኖታዊ ሥልጣኖች መካከል ከፍተኛው የሆነውን በመላ አገሪቱ የሚገኙ ሃይማኖታዊ የትምህርት ተቋማትን እንዲመሩ የተሾሙ ናቸው።

በአውሮፓውያኑ 2019 ደግሞ ኻሜኒ የጠባቂ ምክር ቤቱ አባል አድርገው መርጠዋቸዋል።

ሌሎች አክራሪ አቋም ያላቸው የባለሙያዎች ጉባዔ ምክር ቤቱ አባል የሆኑት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሃሼም ሆሴይኒ ቦውሼህሪ፣ ሞሼን አራኪ እንዲሁም ሞሐመድ ሜህዲ ሚርባቅሪ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት መካከል ናቸው።

የአያቶላህ ሩሆላህ ኾሜኒ የልጅ ልጅ ሃሳን ኾሜኒ በለዘብተኛ እና በለውጥ ፈላጊዎች ዘንድ ተመራጭ ነው።

ሃይማኖታዊ እውቀቱ አንዲሁም የቤተሰቡ ታሪክ በመራጮች ዘንድ ሚዛን ሊደፋ ቢችልም ፖለቲካዊ ልምዱ እና ያሉት ጠንካራ ተቀናቃኞች ግን የመመረጥ ዕድሉን ይቀንሱበታል።