ኢራን ሆርሙዝ ሰርጥን መዝጋት ትችላለች? በቀሪው ዓለም ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?

በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በኦማን ባሕረ ሰላጤ መካከል የሚገኘው የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ የሳተላይት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Stocktrek / Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና በኦማን ባሕረ ሰላጤ መካከል የሚገኘው የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ የሳተላይት ምስል

በእስራኤል እና በኢራን መካከል በሚካሄደው የሚሳዔል ጥቃት ምክንያት ኢራን የዓለም ወሳኙ የነዳጅ ዘይት መተላለፊያ የሆነውን የሆሙዝ የባሕር ሰርጥን ትዘጋ ይሆናል የሚል ስጋት ቀስቅሷል።

የምድራችን አንድ አምስተኛው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በዚህ 40 ኪሎ ሜትር ብቻ ስፋት ባለው፣ በጣም ጠባብ በሆነው ሰርጥ በኩል ነው የሚያልፈው።

እንደ የኢራን የባሕር ኃይል አዛዥ ከሆነ የባሕር ሰርጡን ለመዝጋት ልታስብ ትችላለች።

የቀድሞ የዩናይትድ ኪንግደም የስለላ ድርጅት ኤምአይ6 ኃላፊ ሰር አሌክስ ያውንገር ለቢቢሲ እንደተናገሩት የከፋው ሁኔታ ሰርጡ ሊዘጋ ይችላል።

"ሰርጡን መዝጋት በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተግዳሮት እንደሚሆን ግልጽ ነው" ይላሉ።

በሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ ምን ያህል ነዳጅ ያልፋል?

የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር (ኢአይኤ) በ2023 የመጀመሪያ አጋማሽ በቀን 20 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ እንዳለፈ ይገምታል።

ይህም በዓመት ወደ 600 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የነዳጅ ንግድ በባሕር መስመሩ ላይ ይጓጓዛል ማለት ነው።

በባሕር ሰርጡ ላይ የሚከሰት ማንኛውም ዓይነት መስተጓጎል በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መዘግየቶችን ሊያስከትል ይችላል፤ ይህም ወዲያውኑ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ያደርጋል።

ነገር ግን ተንታኞች በእስራኤል እና በኢራን መካከል ያለው ግጭት እየተባባሰ የሚሄድ ከሆነ የበለጠ ከባድ መዘዝ ይኖረዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ይህ ከባሕረ ሰላጤው አገራት በሚገባ የነዳጅ ዘይት ላይ ጥገኛ በሆኑ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በሌሎችም አገራት ላይ ከፍተኛ ጫና ሊኖረው ይችላል።

የኢራን ወታደራዊ ፈጣን ጀልባ በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ ላይ ከግዙፍ ነዳጅ ዘይት ጫኝ መርከብ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Atta Kenare / Getty Images

የሆርሙዝ ሰርጥ ምን ያህል ጠባብ ነው?

የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ በኢራን እና በኦማን መካከል የሚገኝ ነው። መግቢያው እና መውጫው 50 ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ በመሃል ላይ ደግሞ በጣም ጠባብ የሆነው ቦታ 40 ኪ.ሜ. ብቻ ይሰፋል።

ሰርጡ በማዕከላዊው ክፍል ብቻ ትላልቅ መርከቦች ለማሳለፍ የሚሆን ጥልቀት አለው።

የባሕር አሳሾች መግቢያ እና መውጫው ለትልልቅ መርከቦች ደኅንነቱ የተጠበቀ መሆኑን ያረጋገጡ ሲሆን፣ በመካከልም ክብደት ያለውን ነዳጅ ጭነው ለሚጓዙ ምቹ መሆኑን ይገልጻሉ።

እነዚህ ግዙፍ መርከቦች ወደ 10 ኪሎ ሜትር ስፋት ባለው የሰርጡ ክፍል ላይ መቅዘፍ ይኖርባቸዋል።

ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ሲያልፉ በኢራን እና በአረብ አገራት መካከል አወዛጋቢ በሆኑት የቱንብ ደሴቶች አቅራቢያ ያልፋሉ።

በሰርጡ ላይ የሚተላለፉ የንግድ መርከቦችን የሚያስተጓጉሉ ካሉ ወታደራዊ እርምጃ ከግምት እንደሚገባ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህ ደግሞ በአውሮፓውያኑ 1980 እስከ 1988 ድረስ በተካሄደው የኢራን እና የኢራቅ ጦርነት ወቅት ተከስቷል።

ካርታ

ወታደራዊ እርምጃ?

ተንታኞች እንደሚሉት ለኢራን የሆርሙዝ ባሕር ሰርጥን መዝጋት እንደ "መከላከያ ኃይል" በመጠቀም፣ ልክ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ከመያዝ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢራንን ወታደራዊ የኒውክሌር መርሃ ግብር ለረጅም ጊዜ ሲቃወም እንደነበረው ሁሉ፤ ታላላቅ አገራት ቴህራን ያላትን ስትራቴጂክ አቀማመጥ ተጠቅማ የዓለምን የኃይል አቅርቦት እንድታንቅ እንደማይፈቅዱ ደጋግመው ሲገልጹ ተሰምተዋል።

ብዙውን ጊዜ ኢራን የባሕር ሰርጡን ለጊዜው ልትዘጋው እንደምትችል ባለሙያዎች ይተነብያሉ።

ነገር ግን ብዙዎች ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ ወታደራዊ መንገዶችን በመጠቀም የባሕር መስመር ፍሰቱን በፍጥነት ወደ ነበረበት ሊመልሱት እንደሚችሉ እርግጠኞች ናቸው።

ኢራን በሳተላይት መስሉ ላይ በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ ጫፍ ላይ፣ ከቄሽም ደሴት እና በደቡብ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ትገኛለች

የፎቶው ባለመብት, Gallo Images via Getty Images

ኢራን የሆርሙዝ ሰርጥን እንዴት ልትዘጋው ትችላለች?

በአውሮፓውያኑ 2012 የአሜሪካ ኮንግረስ የምርምር አገልግሎት ባደረገው ጥናት መሠረት ኢራን ሰርጡን ለመዝጋት አዝጋሚ አካሄድን ልትከተል ትችላለች።

ይሆናሉ ተብለው የተዘረዘሩት እርምጃዎች የሚከተሉትን ያካትታሉ።

  • ጥሰት የሚያስከትለውን መዘዝ በግልፅ ሳይገልጽ በሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ መንቀሳቀስን ማገድ
  • በሰርጡ የሚያቋርጡ መርከቦች ሊፈተሹ ወይም ሊያዙ እንደሚችሉ ማወጅ
  • በመርከቦች ላይ የማስጠንቀቂያ ጥይቶችን መተኮስ፥
  • የተወሰኑ መርከቦችን በወታደራዊ ኃይል ዒላማ ማድረግ
  • በባሕር ሰርጡ እና በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ውስጥ የባሕር ውስጥ ፈንጂዎችን ማጥመድ
  • የንግድ እና ወታደራዊ መርከቦችን ዒላማ ለማድረግ ሰርጓጅ መርከቦችን እና ሚሳዔሎችን መጠቀም

በኢራን እና ኢራቅ ጦርነት ወቅት ኢራን የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ላይ ሚሳዔሎችን የተጠቀመች ሲሆን፣ በባሕረ ሰላጤው ላይ የባሕር ውስጥ ፈንጂዎችን አጥምዳለች።

ከእነዚህ ፈንጂዎች መካከል አንዱ ዩኤስኤስኤስ ሳሙኤል ቢ ሮበርትስን የተባለውን መርከብ በመምታቱ አሜሪካ በምላሹ ወታደራዊ እርምጃ ወስዳለች።

ኢራን የሆርሙዝ ባሕር ሰርጥን ሙሉ በሙሉ መዝጋት ሳትችል የቀረች ቢሆንም፤ የመርከብ ኢንሹራንስ ክፍያን በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

ከዚህም በተጨማሪ በባሕረ ሰላጤው መውጫ ላይ መጨናነቅ በመፈጠሩ መርከቦች ለከፍተኛ ወጪ ተዳርገውም ነበር።

የኢራን ወታደራዊ አቅም

እስራኤል በቴህራን ላይ በፈፀመችው የአየር ጥቃት ከመገደላቸው ሁለት ቀን ቀደም ብሎ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አዛዥ የነበሩትን ሜጀር ጄነራል ሆሴን ሳላሚ በሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ ላይ የሚገኘውን የባሕር ኃይል ጎብኝተው ነበር።

በዚህ ጉብኝታቸው ወቅት የፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና አካባቢው የእስላማዊ ሪፐብሊኩ በጣም ወሳኝ የመከላከያ ቀጠና እንደሆኑ ገልጸዋል።

በተለይም 10 ኪሎ ሜትርን ከሦስት ደቂቃ በታች መጓዝ የሚችሉ ባለከፍተኛ ፍጥነት ሚሳዔል ማስወንጨፊያ መርከቦችን በንግግራቸው አንስተዋል።

ጄነራል ሳላሚ እንዳሉት እነዚህ ፈጣን ጀልባዎች፣ ከባድ የውጊያ መርከቦች እና ሚሳዔሎች በመከላከል ዘመቻዎች ላይ ጥቅም ላይ ይውላሉ።

በተጨማሪም የፀረ መርከብ ፈንጂዎችን "በባሕር ኃይል ጦርነት ውስጥ በጣም ወሳኝ ከሆኑ መሳሪያዎች አንዱ ነው" ሲል ተናግረዋል።

ሳላሚ እንደተናገሩት የባሕር ኃይል ሰው አልባ አውሮፕላኖች በባሕር ላይ "በሚሸፍኑት ክልል፣ በችሎታ እና በተልዕኮ ልዩነት" ሰፍተዋል።

በኢራን እና ኢራቅ ጦርነት (እአአ ከ1980-1988 ) ወቅት ኢራን ባጠመደችው ፈንጂ 210,000 ቶን በጫነ መርከብ ላይ የደረሰ አደጋ

የፎቶው ባለመብት, Norbert Schiller via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኢራን እና ኢራቅ ጦርነት (እአአ ከ1980-1988 ) ወቅት ኢራን ባጠመደችው ፈንጂ 210,000 ቶን በጫነ መርከብ ላይ የደረሰ አደጋ

ተንታኞች ምን ይላሉ?

በየወሩ ወደ 3,000 የሚጠጉ መርከቦችን ለማስቆም ኢራን ከምታደርጋቸው ውጤታማ መንገዶች አንዱ ፈጣን ጥቃት የሚያደርሱ ጀልባዎችን እና የባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን በመጠቀም ፈንጂዎችን ማጥመድ እንደሆነ ባለሙያዎች ይተነብያሉ።

የኢራን መደበኛ የባሕር ኃይል እና የእስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ የባሕር ኃይል በሌላ አገራት የጦር እና የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል።

ሆኖም ትላልቅ ወታደራዊ መርከቦች በቀላሉ የእስራኤል ወይም የአሜሪካ የአየር ጥቃቶች ዒላማ ሊሆኑ ይችላሉ።

የኢራን ፈጣን ጀልባዎች ብዙውን ጊዜ ፀረ መርከብ ሚሳዔሎች የታጠቁ ሲሆኑ፣ አገሪቱ ከፊል ሰርጓጅ መርከቦችን እና ሰርጓጅ መርከቦችንም ትጠቀማለች።

በአሁኑ ጊዜ የሳተላይት ምሥሎችን የኢራን ወታደራዊ መርከቦች በአገሪቱ ደቡባዊ የባሕር ጠረፍ አካባቢ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑን ያሳያሉ።

የበለጠ የሚጎዱት አገራት የትኞቹ ናቸው?

ቮርቴክሳ የተሰኘው ድርጅት ይፋ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው ሳዑዲ አረቢያ በቀን 6 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት በሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ በኩል ወደ ውጭ ትልካለች።

ይህም ከየትኛውም የጎረቤት አገር ይበልጣል።

ቻይና፣ ሕንድ፣ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ከሚያስገቡት መካከል ግንባር ቀዳሚዎቹ ናቸው።

የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር በ2022 ወደ 82 በመቶ የሚጠጋ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት እና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች በባሕር ሰርጡ አልፈው ወደ እስያ አገራት ተጓጉዘዋል ብሏል።

እስራኤል የኢራን ወታደራዊ እና ኒውክሌር ተቋማት ላይ ጥቃት ከመክፈቷ ሦስት ቀን ቀደም ብሎ የኢራን የዜና ወኪል የደቡብ ኮሪያን ፕሬዝዳንት ዩን ሱክ ዮልን ጠቅሶ እንደዘገበው 60 በመቶው የአገራቸው የነዳጅ ዘይት አቅርቦት በሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ በኩል የሚያልፍ ነው።

የአሜሪካ የኢነርጂ መረጃ አስተዳደር አሜሪካ በየቀኑ ወደ 700 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት እና ሌሎች ማዕድናትን በባሕር ሰርጡ በኩል ታጓጉዛለች ብሏል።

ይህም በግምት በጠቅላላው ከምታስገባው ነዳጅ ዘይት 11 በመቶው ሲሆን፣ የፍጆታዋ ደግሞ 3 በመቶው ይሆናል።

በባሕር ሰርጡ በኩል የሚጓጓዘው የአውሮፓ አገራት ነዳጅ ዘይት ድርሻ በቀን ከ1 ሚሊዮን በርሜል ያነሰ ነው።

ከዚህ አንፃር ሲታይ የባሕር ሰርጡ ቢዘጋ በዋናነት የሚጎዱት ከአሜሪካ እና ከአውሮፓ አገራት ይልቅ የአረብ እና የእስያ አገራት ናቸው።

በርካታ የእስያ አገራት ከኢራን ጋር ጥሩ ወይም የቅርብ ሊባል የሚችል ግንኙነት አላቸው።

የቻይና ነዳጅ ዘይት ማጣሪያዎች በሆርሙዝ ባህር ሰርጥ ውስጥ የሚጓጓዘውን ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ዘይት ያጣራሉ

የፎቶው ባለመብት, CFOTO / Future Publishing via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቻይና ነዳጅ ዘይት ማጣሪያዎች በሆርሙዝ ሰርጥ የሚያልፈውን ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ ዘይት ያጣራሉ

የቻይና ተጽእኖ

ቻይና በሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ ከሚያልፍ የነዳጅ ዘይት ተጠቃሚ ከሆኑ አገራት መካከል አንዷ ነች። ከፍተኛ መጠን ያለውን የነዳጅ ዘይት ኢራን ከዓለም የገበያ ዋጋ በታች ትሸጥላታለች።

ይህም በአሜሪካ ማዕቀቦች የተሽመደመደውን ምጣኔ ሀብቷን ለማገዝ ረድቷታል።

ቤይጂንግ ዋነኛ የኢራን ነዳጅ ዘይት ተጠቃሚ እንደመሆኗ መጠን የነዳጅ ዋጋ መጨመርን ወይም የመርከብ መስመሮችን መቋረጥን አትቀበልም።

ቻይና የዚህን ወሳኝ መስመር መዘጋት ለመከላከል ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ አቅሟን እንደምትጠቀም ይጠበቃል።

የኢነርጂ አማካሪ የሆኑት አናስ አልሃጂ ለሲኤንቢሲ እንደተናገሩት የሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ መዝጋት ከጠላቶቿ የበለጠ የኢራን አጋሮችን ይጎዳል።

"መጀመሪያ ራሳቸውን [ኢራናውያንን] የሚጎዳ ነገር ማድረግ አይፈልጉም" ብለዋል።

የኢራን ባሕር ኃይል ፈጣን ጀልባዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢራን ባሕር ኃይል ፈጣን ጀልባዎች

አማራጭ የጉዞ መስመሮችን መጠቀም ይቻላል?

ለዓመታት የሆርሙዝ ባሕር ሰርጥ ይዘጋል የሚለው ስጋት በባሕረ ሰላጤው አካባቢ የነዳጅ ላኪ የሆኑ አገራት አማራጭ የጉዞ መንገዶችን እንዲያዘጋጁ አነሳስቷቸዋል።

ሳዑዲ አረቢያ በቀን እስከ 5 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ማጓጓዝ የሚያስችል 1,200 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የቧንቧ መስመር ዘርግታለች።

በ2019 ሳዑዲ አረቢያ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይትን ለማስተላለፍ እንድትችል የተፈጥሮ ጋዝ መስመሯን ለጊዜው መልሳ ጥቅም ላይ አውላለች።

የተባበሩት አረብ ኤሚሬትስ በቀን 1.5 ሚሊዮን በርሜል የሚይዝ የነዳጅ ማከማቻን በኦማን ባሕረ ሰላጤ ከምትገኘው ፉጃይራህ ወደብ ጋር አገናኝታለች።

በሐምሌ ወር 2021 ኢራን ድፍድፍ ዘይትን ወደ ኦማን ባሕረ ሰላጤ ለማሸጋገር የሚያስችለውን የጎሬህ ጃስክ የነዳጅ መስመርን መርቃለች።

ይህ የነዳጅ ማመላለሻ ቱቦ በአሁኑ ጊዜ በቀን ወደ 350 ሺህ በርሜል ማመላለስ ይችላል።

የሚወጡ መረጃዎች ግን ኢራን እስካሁን ጥቅም ላይ አለማዋሏን ያሳያሉ።

እነዚህ አማራጭ መንገዶች በቀን ወደ 3.5 ሚሊዮን በርሜል ዘይት በአንድነት ማስተናገድ የሚችሉ ሲሆን፣ ይህም በአሁኑ ጊዜ በባሕር ሰርጡ ከሚጓጓዘው ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት 15 በመቶው ይሆናል።