የእስራኤል እና የኢራን ግጭት የዓለም ነዳጅ ዋጋን እንዴት ሊጨምር ይችላል?

ለመኪና ነዳጅ የሚሞላ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መፈፀሟን እና ኢራንም ለጥቃቱ ምላሽ መስጠቷን ተከትሎ በዓለም ገበያ ላይ ድንጋጤ ተፈጥሯል። በተለይ በዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ የታየው ወዲያውኑ ነበር።

ሆኖም ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በሁለቱ አገራት መካከል የሚሳዔል እና የድሮን ጥቃቶች ከተፈፀሙ በኋላ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ቅናሽ አሳይቷል።

ቢሆንም የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከአንድ ወር በፊት ከነበረው በ10 ዶላር ጨምሯል። ይህም በመላው ዓለም የቤንዚን እና የምግብ ዋጋን ጨምሮ በሌሎች ፍጆታዎች እና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ንረት ያስከትላል የሚል አዲስ ስጋትን ፈጥሯል።

ከሦስት ዓመታት በፊትም ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ስትፈፅም የሆነውም ይኸው ነበር።

ከፍተኛ የነዳጅ ምርት በሚገኝበት መካከለኛው ምሥራቅ እና ፋርስ ባሕረ ሰላጤን በሚያካልለው አካባቢ የተፈጠረው የእስራኤል እና የኢራን ግጭት እስከመቼ እንደሚቆይ እንዲሁም ምን እንሚያስከትል እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

የነዳጅ ዋጋ ምን ያህል ነው የጨመረው?

የእስራኤል ጥቃት ያስከተው ምላሽ እና ለቀናት የቀጠለው አጸፋ በዓለም ገበያ ላይ ለውጥን አስከትሏል።

አርብ ዕለት የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከ78 ዶላር በላይ ደርሶ ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን ወደ 74.50 ዶላር ዝቅ ብሏል። ነገር ግን ባለፈው ወር ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር በ10 ዶላር ጨምሯል።

በዓለም ላይ በሚከሰቱ ትላልቅ ክስቶች እና ቀውሶች ምክንያት የነዳጅ ዋጋ እንዲሁም የዓለም ኢኮኖሚ በየጊዜው ይዋዥቃል።

በመሆኑም የእስራኤል እና የኢራን ግጭትን ተከትሎ በነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ ቢከሰት የሚያስገርም አይደለም።

አሁን ላይ ያለው ዋጋ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረውም በጣም ያነሰ ነው። ከሦስት ዓመት በፊት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ጦርነት ሲቀሰቀስ ከነበረው ዋጋም ዝቅተኛ ነው። ያኔ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ወደ 130 ዶላር ይጠጋ ነበር።

ነዳጅ መቅጃ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቤንዚን እና ሌሎች ፍጆታዎች ዋጋ ሊጨምር ይችላል?

በርካቶች የነዳጅ ዘይት የጅምላ መሸጫ ዋጋ ከፍ ማለቱን የሚያስተውሉት በቤንዚን ላይ ጭማሪ ሲያስከትል ነው።

ሆኖም በኃይል ዋጋ ላይ ጭማሪ ሲከሰት ከግብርና እስከ ፋብሪካ ምርቶች ድረስ በሁሉም ነገሮች ላይ ንረትን ያስከትላል።

በምግብ ፍጆታዎች ላይም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የዋጋ ለውጥን ያስከትላል። የግብርና መሣሪያዎችን ለማንቀሳቀስ፣ ምርትን ለማጓጓዝ እና ምግብን አቀናባብሮ እና አሽጎ ለማቅረብ ያለውን ሒደት ውድ ያደርገዋል።

ይህ የሚሆነው ግን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው ለረጅም ጊዜ ከቆየ ነው።

በካፒታል ኢኮኖሚክስ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ዴቪድ ኦክስሌይ "በነዳጅ ዘይት ዋጋ ላይ 10 ዶላር ሲጨምር በአጠቃላይ ምርቱ ላይ የ7 በመቶ ጭማሪ ሊያስከትል ይችላል" ሲሉ የዋጋ ሰንሰለቱን ተያያዥነት አስረድተዋል።

ይህ ስሌት ከነዳጅ ዘይት ጋር የሚገናኝ ብቻ እንዳልሆነ ባለሙያው ያሰምራሉ።

በዩክሬን ጦርነት መጀመሪያ ላይ በፍጆታዎች ላይ የታየውን አስደንጋጭ ጭማሪ በርካቶች እንደሚያስታውሱት የሚገልጹት ኦክስሌይ፣ይህም በአብዛኛው በጋዝ ላይ የታየው ዋጋ መናር ውጤት መሆኑን ያስረዳሉ።

"በርካቶቻችን ቤቶቻችንን የምናሞቀው በጋዝ ነው። በመሆኑም በዩናይትድ ኪንግደም የኤሌክትሪክ ዋጋ ከጋዝ ዋጋ መናር ጋር ተያይዟል" ብለዋል።

የጋዝ ዋጋም ካለፈው ሳምንት ጥቃት ወዲህ ጭማሪ አሳይቷል።

ሆኖም ተፅዕኖው ወደ እያንዳንዱ ቤት ሰተት ብሎ የሚገባው ቀስ እያለ እንደሆነና ይህም ዋጋዎችን በመቆጣጠር ረገድ የተቆጣጣሪዎችን ሚና ጨምሮ ገበያው በሚሳለጥበት መንገድ ላይ ይመሠረታል ብለዋል ባለሙያው።

የነዳጅ ዘይት ዋጋ ሊያሻቅብ ይችላል?

ኢነርጂ አስፔክትስ በተባለ የምርምር እና አማካሪ ተቋም ውስጥ የጂኦፖሊቲካዊ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት ሪቻርድ ብሮንዝ አሁን ላይ ያለው ሁኔታ "በጣም ወሳኝ እና አሳሳቢ ነው" ይላሉ።

ይህ ማለት ግን በዩክሬን ጦርነት ወይም ከዚያ በፊት በነበሩ የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭቶች ወቅት እንደነበረው ትልቅ ተፅዕኖ ያስከትላል ማለት አይደለም።

አሁን ላይ ዋናው ጥያቄ የሚሆነው የእስራኤል እና የኢራን ግጭት ምን ያህል ይቆያል? ሌሎች በቀጠናው ያሉ አገራት በግጭቱ ውስጥ ይሳተፋሉ ወይ? አሜሪካስ ግጭቱን ለማስቆም ምን እርምጃ ትወስዳለች? የሚለው ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ በኢራን ደቡባዊ የውሃ ዳርቻ ሆርሙዝ ሰርጥ ላይ ባለው የባሕር መስመር በሚያጋጥመው የትራንስፖርት መስተጓጎል ላይ ይወሰናል።

ሆርሙዝ አንድ አምስተኛ የሚሆነው የዓለም የነዳጅ ምርት ወደ ዓለም ገበያ የሚጓጓዝበት መስመር ነው።

በእርግጥ ከዚህ በፊት በነበሩ ግጭቶች በዚህ መስመር ላይ ችግር ሳይከሰት ቆይቷል። ሆኖም ኢራን ከዚህ ቀደም ይህንን ልታደርግ እንደምትችል ስትዝት ስለነበረ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ላይ ከጥቂት ቀናት በፊት ከነበረው አነስተኛ ጭማሪ ሊታይ ይችላል።

ሆኖም በትራንስፖርት ላይ የመስተጓጎል ችግር ካልገጠመ በስተቀር የነዳጅ ዋጋ ጨምሮ አይቆይም።

ከሦስት ዓመት በፊት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈፀመችውን ወረራ ተከትሎ ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ የዓለም ኢኮኖሚ እንደገና በመከፈቱ የነዳጅ ፍላጎት ከፍተኛ ሆኖ ነበር።

አሁን ላይ የዓለም ኢኮኖሚ ከባድ ጊዜ እያጋጠመው ቢሆንም ከሳዑዲ አረቢያ እስከ ብራዚል ያሉ የነዳጅ አምራቾች የነዳጅ አቅርቦትን የመጨመር አቅም ስላላቸው የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ ይረዳል።

ይህ ለዓለም ምጣኔ ሃብት ምን ማለት ነው?

የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና የሚያሳድረው ሰፊ ተፅዕኖ በእስራኤል እና በኢራን ግጭት ቀጣይ ሁኔታዎች ላይ የሚመሠረት ይሆናል።

ሆኖም የዓለም ምጣኔ ሃብት ላለበት ፈታኝ ሰዓት አስደንጋጭ ሊሆን ይችላል ብለዋል - የምጣኔ ሃብት አማካሪው መሐመድ ኤል ኤሪያን።

አማካሪው እንደሚሉት "በየትኛውም መልኩ ብትመለከቱት ለአጭር ጊዜም ሆነ ለረጅም ጊዜ የሚያስከትለው ውጤት አሉታዊ ነው።"

አሁንም በርካታ ጥያቄዎች በሚነሳበት አሜሪካ መር የኢኮኖሚ ሥርዓት መረጋጋት ላይም ተፅዕኖ ያሳድራል።

እንደ ካፒታል ኢኮኖሚ ስሌት ከሆነ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ከ100 ዶላር በላይ ከደረሰ ባደጉ ኢኮኖሚዎች ላይ 1 በመቶ ግሽበት የሚያስከትል ሲሆን፣ የወለድ ምጣኔን ለመቀነስ ተስፋ ያደረጉ ማዕከላዊ ባንኮችን ሕይወትም ፈታኝ ያደርገዋል።

ሆኖም በዴቪድ ኦክስሌይ አመለካከት ይህ ሊያጋጥም የሚችልበት ዕድል ዝቅተኛ ነው።

"በመካከለኛው ምሥራቅ አለመረጋጋት አዲስ ነገር አይደለም። ብዙ ክስተቶችን ተመልክተናል" የሚሉት ኦክስሌይ፤ "በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አስከፊ ሁኔታ ሳያስከትል ሊስተካከል ይችላል" የሚል ግምት አላቸው።