"የትኛውም ቦታ ደህንነት አይሰማንም" - የኢራናውያን ሕይወት በእስራኤል ጥቃት ስር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ቅርቃር"፤ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ብዙዎቹ ሰዎች አሁን ሕይወት በኢራን ምን እንደሚመለስል የገለጹበት ቃል ነው።
አንድ ነዋሪ፤ ከእስራኤል የሦስት ቀናት ጥቃት በኋላ "ሁሉም ሰው"፤ "አንድም ሆነ በሌላ መንገድ" ከቴህራን "ለማምለጥ እየሞከረ" እንደሆነ ለቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያን ተናግሯል።
እሁድ ዕለት በመላ ከተማው በሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች ረዣዥም ሰልፎች ታይተዋል።
በርካታ ሰዎች ከእስራኤል የጥቃት ዒላማዎች ለመራቅ ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ለመሸሽ እየሞከሩ ነው። ነገር ግን በተከሰተው ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ከነበሩበት አውራጃ እንኳ መውጣት አልቻሉም።
አንድ ነዋሪ፤ "በግልጽ ለመናገር ቴህራን ደህንነት ያለባት ቦታ አይደለችም" በማለት ተናግሯል።
"ስለ እስራኤል ጥቃቶች ምንም ማንቂያ እና ማስጠንቀቂያዎችን ከባለስልጣናት አናገኝም። ፍንዳታውን ብቻ እንሰማና የእኛ ስፍራ እንደማይመታ ተስፋ እናደርጋለን። ወደ የት መሄድ እንችላለን? የኛውም ቦታ ደህንነት አይሰማንም" ሲል ስጋቱን ይገልጻል።
ከቴህራን ወደ ሌላ አውራጃ ለመሄድ የቻለ አንድ ነዋሪ፤ "በጦርነት ቀጠና ውስጥ እየኖርኩ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ የተገነዘብኩት አይመስለኝም፤ መቼ ይህንን እውነታ መቀበል ላይ እንደምደርስ እርግጠኛ አይደለሁም" ብሏል።
"ይህ የእኔ ጦርነት አይደለም። ለየትኛውም ወገን አልደግፍም፤ የምፈልገው ከእነቤተሰቦቼ መትረፍ ብቻ ነው"
ከአርብ ጀምሮ እስራኤል በዓመታት ውስጥ ከፈጸመቻቸው ትልቁ በሆነው ተከታታይ የአየር ድብደባ ኢራንን መትታለች።
ኢራንን በአጸፋው በቴልአቪቭ ላይ የሚሳኤል ጥቃት እንድትፈጽም አድርጓል።
በእስራኤል ቢያንስ 19 ሰዎች መገደላቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
የኢራን ጤና ሚኒስቴርን የጠቀሱት ሀገሪቱ ሚዲያዎች ደግሞ እስከ እሁድ ምሽት 224 ሰዎች በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ዘግበዋል።
አንዲት ኢራናዊ፤ "ያለፍኩበት ሁኔታ በጣም ከባድ ነው" ስትል ለሁለት ቀናት እንቅልፍ ሊወስዳት እንዳልቻለ ገልጻለች።

የፎቶው ባለመብት, EPA-EFE
የአሁኑ ሁኔታ እ.አ.አ በ1980ዎቹ ሕጻን እያለች የኢራን እና ኢራቅ ጦርነት ሲካሄድ የነበረውን የቦንብ ድብደባ እና ወደ መጠለያዎች የመግባት ነገር እንዳስታወሳት ተናግራለች።
"ልዩነቱ፤ የዛኔ ቢያንስ ጥቃት ሲፈጸም የአየር ጥቃት ድምጽ ወይም ቢያንስ ከመድረሱ በፊት ማስጠንቀቂያ እንሰማ ነበር። አሁን ግን በድብደባውም ሆነ በአየር ጥቃት ጊዜ ምንም ድምፅ ወይም ማስጠንቀቂያ የለም።"
ከጦርነቱ በኋላ የተወለዱ ወጣቶች የያኔው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር እንደማያውቁ የቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያኑ ጎንቼ ሀቢቢአዛድ ትናገራለች።
አንዲት የቴህራን ነዋሪ ከጥቃቶቹ ለማምለጥ ከከተማ ለመውጣት እያሰበች መሆኑን ገልጻለች።
"ሁላችንም ወደ ትናንሽ ከተማዎች እና መንደሮች መሄድ እንፈልጋለን። ነገር ግን እያንዳንዳች ጥለን የማንሄዳቸው የምንወዳቸው ሰዎች አሉ፤ ስለእነርሱ እያሰብን ነው" ትላለች። "አሁን እየደረሰብን ያለው ነገር ለሁላችንም የኢራን ሕዝቦች የሚገባ አይደለም"
"ሁላችንም እነዚህን ቀናት ለማለፍ እየሞከረን ያለነው በፍርሃት፣ በድካም እና በብዙ መጨነቅ ውስጥ ሆነን ነው። ይህ እጅግ ከባድ እና የሚያም ነው"
በዋና ከተማዋ የሚኖር ሌላ ነዋሪ፤ "እንዲሁ ቴህራንን ለቅቄ መውጣት አልችልም። ረዥም ርቀት መጓዝ የማይችሉ አረጋውያን ወላጆቼን ትቼ፤ ለራሴ ከከተማው መውጣት አልችልም። በዚያ ላይ ስራ መገኘት አለብን። አሁን ምን ማድረግ እችላለሁ?"
በኢራን የኢንተርኔት አገልግሎት የተረጋጋ አይደለም። በዚህም የተነሳ በአገሪቱ የሚገኙ ነዋሪዎችን ማግኘት ከባድ ነው።
በውጭ አገራት የሚገኙ በርካታ ሰዎች ምላሽ እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ ወደ ወዳጆቻቸው መልዕክቶችን እየላኩ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተወሰኑ ሰዎች፤ ሁሉም ኢራናውያን ከወታደራዊ ስፍራዎች በአቅራቢያ ከሚገኙ አካባቢዎች ለቅቀው እንዲወጡ የሚያሳስቡ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ማስጠንቀቂያዎችን ደርሰዋቸዋል።
አንድ ነዋሪ፤ "ወታደራዊ ስፍራዎች የት እንደሚገኙ እና የት እንደማይገኙ እንዴት ልናውቅ እንችላለን?" ሲል ይጠይቃል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔትያናሁ በጥቃቱ ሁለተኛ ቀን ለኢራናውያን ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢራናውያን በአንድነት "ለነጻነታቸው የሚቆሙበት"፤ "ጊዜው መምጣቱን" ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ በአገሪቱ የሚገኙ ነዋሪዎች እስካሁን ድረስ ምርጫቸው ያደረጉት በደህንነት መቆየት ነው።
የቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያኑ ዳርዩሽ ካሪሚ እንደሚናገረው የኔቴንያሁ ጥሪ የነዋሪዎችን ቀልብ መግዛቱን የሚያመለክት ይሄ ነው የሚባል ማስረጃ የለም።
ኢራን ውስጥ ምንአልባትም በኒውለክሌር ተቋማት እና የአየር ማረፊዎያዎች ላይ ከደረሰው ጥቃት ይበልጥ ሰዎችን ያስደነገጠው በመኖሪያ ሕንጻዎች ላይ የደረሰው ውድመት እንደሆነ የቢቢሲ ኒውስ ፐርሺያኑ ፖያን ካላኒ ይናገራል።
በርካታ ኢራናውያን ከኢራን እና ኢራቅ ጦርነት ወዲህ በተለይም በአገሪቱ ዋና ከተማ ጎዳናዎች ላይ ይህንን ዓይነት ጥቃት አይተው አያውቁም።
በቴህራን እና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ብዙዎቹ ነዋሪዎች አርብ ዕለት የተፈጠረባቸውን ግራ መጋባት ያስታውሳሉ።
አሁን በትክክል እየተፈጠረ ያለው ምንድን ነው? ምን ያህ ሰፊ ነው? እንዴት ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን መጠበቅ ይችላሉ? የሚሉት የተፈጠሩባቸው ጥያቄዎች ነበሩ።















