የትግራይን ጦርነት ስላስቆመው የፕሪቶሪያው ድርድር ያልተሰሙ ታሪኮች

ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የመንግሥት ተደራዳሪ የነበሩት ሬድዋን ሁሴን፣ አሸማጋይ ኡሁሩ ኬንያታ እና የህወሓት ተደራዳሪ የነበሩት ጌታቸው ረዳ

ከሁለት ዓመት በፊት በአሜሪካ እና በአውሮፓ ኅብረት ታዛቢነት እና በቀጥታ በአፍሪካ ኅብረት ሸምጋይነት በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ደም አፋሳሹን የትግራይ ጦርነት በማስቆም የሚወደስ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ አነጋገሪ ሆኖ ቀጥሏል።

ስምምነቱ በአንድ በኩል ለሁለት ዓመት ያህል በከባድ ጦርነት ውስጥ ለቆየው ለትግራይ ሕዝብ እፎይታን ሲፈጥር፤ በሌላ በኩል በጦርነቱ የተጎዱ ሰዎች አላገገሙም፤ የተፈናቀሉ ሙሉ ለሙሉ አልተመለሱም። እንዲሁም በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶች በአብዛኛው ተመልሰው ሥራ እንዳልጀመሩ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ከተደራዳሪው ልኡካን መካከል አንዱ እና በአሁኑ ወቅት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የኢኮኖሚ እና አስተዳደር አማካሪ የሆኑት አቶ አሰፋ አብረሃ (ኢንጂነር) ስምምነቱ የተካሄደበት መንፈስ እና በወቅቱ የነበረው አስጨናቂ ሁኔታን በተመለከተ ወደ ኋላ መለስ ብለው ለቢቢሲ አስታውሰዋል።

“በጭንቀት የተሞሉ ሰባት ቀናት”

ጥቅምት 2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ተነስቶ እስከ የአማራና የአፋር ክልሎች ደርሶ በተለይ በትግራይ ክልል ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እና ቀውስ አስከትሎ እንደነበረ የተባበሩት መንግሥታት አጣሪ ጉባኤ ሪፖርት ያመለክታል።

ጦርነቱን ለማስቆም በጅቡቲ እና ሲሸልስ የሰላም ጥረቶች ተደርገዋል። በመጨረሻ ግን መራራውን ጦርነት ያስቆመው ይሄው በዚህ ሰሞን ሁለት ዓመትን ያስቆጠረው የፕሪቶሪያ ስምምነት ነበር።

በዋናነት በአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር የተመራው ድርድር የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በጉጉት ሲጠብቀው የነበረ ሲሆን፣ ሂደቱን የተደራዳሪ ቡድኑ አባል የሆኑት አቶ አሰፋ አብርሃ እንዲህ በማለት ትዝታቸውን ያስታውሳሉ።

“እዚያ ለድርድር ስንቀመጥ መሬት ላይ የነበረው ሁኔታ በጣም አስጨናቂ ነበር። ምክንያቱም ከባድ ውጊያ ሲካሄድ ነበር። አንዳንዶቹ እዚያ ተቀምጠን ስንወያይ የተሻለ ወታደራዊ አቅም አለን ብለው ስላመኑ ከተቻለ ጨርሶ መደምሰስ፣ ካልተቻለም ውይይቱን ለማዘግየት ሲጥሩ የነበረ ይመስለኛል።

“በአንፃሩ በእኛ በኩል ሁኔታው ጥሩ አልነበረም፤ በየቀኑ ከባድ መስዋዕትነት ሲከፈል ነበር። ከሁሉም በላይ ‘ኮረም ገብተናል፣ መቀለ ደርሰናል’ የሚለው ፕሮፓጋንዳ ይረብሸን ነበር። ራሳቸው አስታራቂዎች ሳይቀር ፕሮፓጋንዳው ተፅዕኖ ይፈጥርባቸው ነበር” ይላሉ።

በወቅቱ ሲካሄድ የነበረው ሦስተኛው ዙር ጦርነት በሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮኖች) እና በከባድ መሳሪያዎች ታጅቦ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን፡ በሁለቱም በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ከፍተኛ ዝግጅት የተደረገበት ስለነበረ ከባድ እንደነበር ይነገራል።

የመንግሥት ጦር ሽሬን ጥሶ አክሱምን እና አካባቢውን ተቆጣጥሮ ነበር፤ በአድዋ ተራሮች የእጅ-ለእጅ ትንቅንቅ ሳይቀር እየተካሄደ ነበር።

በተጨማሪም በአፋር በኩል ከፍተኛ ውጊያ እየተካሄደ ‘መቀለ ከተማን ተቆጣጥረናል’ የሚል ወሬ በመንግሥት ደጋፊዎች በኩል በስፋት ይነገር ነበር።

አቶ አሰፋ በጣም ‘አስጨናቂ’ ብለው የሚገልፁት ግንባር ላይ የነበረው ሁኔታ በውይይቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደነበረ ያምናሉ።

“እነዚያ አስር ቀናት በየቀኑ መሻሻሎች (መስማማቶች) እየተያባቸው ወደፊት የምንራመድበት ሳይሆን፤ በጣም የተካረረ እና እርባና ቢስ ጭቅጭቅ ውስጥ ገብተን ነበር ያሳለፍናቸው” ይላሉ።

በተለይም መደበኛዎቹ ሰባት የመጀመሪያ የድርድር ቀናት ያለ ውጤት ከተጠናቀቁ በኋላ ደስ የማይል ስሜቶች ተፈጥረው እንደነበርም ተናግረዋል።

የኬንያታ ጫና

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የመጀመሪያዎቹ ሰባት የድርድር ቀናት ያለ ውጤት ከተጠናቀቁ በኋላ “ተጨማሪ ሦስት ቀናት እንሰጣችኋለን” በማለት የሰላም ድርድሩ መቀጠሉን አቶ አሰፋ ያስታውሳሉ።

በሦስት ተጨማሪ ቀናት ውስጥ ተስፋ ሰጪ እና የአደራዳሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት እንደታከለበት ያስታውሳሉ።

“የመጀመሪያው የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪው ‘ጉዳይ አለኝ’ ብለው ሄደዋል። [በቀድሞው የናይጄርያ] ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ፈንታ ፕሬዝዳንት ኬንያታ እሳቸውን ተክተው ጉዳዩን ይዘውታል፤ እና ጠንካራ እና ቆራጥነት ያለው ድርድር ተጀመረ።

“ፕሬዝዳንት ኬንያታ ከሁለታችን ወገን ሁለት ሁለት ዋና ተደራዳሪዎች ጐትተው በመውሰድ፣ ወደ አዲስ አበባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዐብይ ጋር በቀጥታ በመደወል ‘በሦስት ቀናት ውስጥ ውጤት ማምጣት አለብኝ’ በማለት ፈርጠም ብለው ተናገሩ።”

ዕለቱ አርብ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ አሰፋ፤ አደረዳሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ድርድር የሚካሄድበት ቦታም ቀድሞ ከነበረው ተቀይሯል።

“ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ያረፉበት [ሂልተን ሆቴል] አንድ አዳራሽ ተዘግቶ፤ ‘በእነዚህ ጉዳዮች ላይ መስማማት አለባችሁ፣ መግባባት አለባችሁ፤ ያ ሳይሆን መውጣት አይቻልም’ ብለው እስከ ሌሊቱ 9 ሰዓት አሳድረውናል” ይላሉ።

እሳቸው እንደሚሉት፣ ከቀድሞው በተለየ መልኩ እውነተኛ እና ጠቃሚ ውይይት በሁለቱም ወገኖች በኩል ተካሂዶ ነበር። “ኬንያታ ጉዳዩን አጥብቀው ሲይዙት፤ እንደገና ‘በሰላማዊ መንገድ መጨረስ እንችላለን’ የሚል ተስፋ እንድንሰንቅ አደረገን።”

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በመሬት ላይ የነበረው ሁኔታ እጅግ እየተባባሰ መምጣቱ፣ ጦርነቱ እጅግ እየተፋፈመ የሰው ዕልቂት እና ጭንቀት እየጨመረ መሄዱን ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት በቀጥታ ከአዛዦቹ ያገኙት መረጃ እንደሚያመለክተው የመንግሥት ኃይሎች ስምምነቱ ከመቋጨቱ በፊት መቀለ ለመግባት ያላቸው ፍላጎት ከፍተኛ ነበር። በአራት እና በአምስት አቅጣጫዎች በተመሳሳይ ጊዜ ከፍተኛ ውጊያዎች ሲካሄዱ ነበር።

“በሁለቱም በኩል ሰው እንደ ቅጠል ሲረግፍ ነበር፣ አብዛኛው መስዋዕትነት ሲከፈል የነበረው በእኛ በኩል ይመስለኛል። ከኤርትራ እና ከየአቅጣጫው ብዙ ኃይሎችን ገፍተው ስለገቡ ሁኔታው አስቸጋሪ ነበር።

“ያም ሆኖ በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አደራዳሪነት በመሠረታዊ መርሆዎች ስምምነት ላይ ተደርሶ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜ እና እሁድ የስምምነቱ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ሰነድ ተዘጋጅቷል። በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ሊፈረም የሚችል አንድ ረቂቅ ለሰኞ ተዘጋጅቶ አድሯል።”

ስምምነቱን ልታፋርስ የነበረችው አንቀጽ

በመጨረሻም የሁለተኛው ዙር ድርድር መጠናቀቁን አስመልክቶ ጋዜጠኞች ተጠርተው ስምምነቱ ሊፈረም በቀረበበት ወቅት ያልተጠበቀ መሰናክል ገጠመ። ይህም አንድ የተጨመረ ነጥብ በሰነዱ ላይ መገኘቱ ነበር።

የተጨመረው አንቀጽ ምን ነበር?

የድንበር ወይም ሌሎች አለመግባባቶች ሕገ መንግሥቱን ታሳቢ በማድረግ እንዲፈቱ በስምምነቱ ዋና መርሆች ላይ ተስማምተናል የሚሉት አቶ አሰፋ በሰነዱ ላይ አዲስ የተጨመረው አንቀፅ ከዚህ ዓውድ የወጣ እንደነበር ይናገራሉ።

እሱም “ሕዝበ ውሳኔ ተደርጐ አንድ ዕልባት እስኪደረግ ድረስ እነዚህ አወዛጋቢ ግዛቶች በፌዴራል መንግሥት እጅ እንዲቆዩ ተስማምተናል” የሚል ነበር።

“በመካከላቸው አንዳንድ አለመግባባቶች ነበሩ” ያሉት አቶ አሰፋ፣ በፌዴራል መንግሥት ተደራዳሪዎች መካከል አንዳንድ ልዩነቶች እና አለመግባባቶች እንደነበሩ ማስተዋላቸውንም ይናገራሉ።

አቶ ሬድዋን ሁሴን እና ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስን ጨምሮ ሰባት አባላት ያሉት የመንግሥት ተደራዳሪዎች የተደራዳሪዎቹን የተለያዩ ፍላጎቶች ለማንፀባረቅ ሲሞክሩ ነበር ይላሉ አቶ አሰፋ።

የአፋር እና የአማራ ክልሎች በተለይም በቀደመው የሁለተኛው ዙር ጦርነት ተጎድተዋል። በዚህም ምክንያት በድርድሩ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ ነበራቸው የሚልም እምነት እንዳላቸው አቶ አሰፋ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተለይ የአማራ ኃይሎች የጦርነቱ መጀመሩን ተከትሎ የይገባኛል ጥያቄ የሚያነሱባቸውን ምዕራብ ትግራይን ጨምሮ ሰፋፊ ቦታዎችን በመቆጣጠራቸው በውይይቱ ላይ ከፍተኛ ስጋት ሲንፀባረቅ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

“ስለዚህ ‘ነገ ፈርመን በሰላም ወደ አገር ቤት እንሄዳለን’ ብለን ተስፋ እያደረግን ሳለ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ አንድ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ተፈጠረ።”

አቶ አሰፋ አብረሃ በወቅቱ የተፈጠረውን ድብልቅልቅ ያለ ስሜት እንዲህ በማለት ይገልጹታል።

“በተለይ ጌታቸው እና (ጄኔራል) ጻድቃን እኛ የመጣነው ሰላማዊ ጉዳይ ፈልገን እንጂ የትግራይ ተወላጆችን ማንነት እና ግዛት ላይ ለመወሰን አይደለም። ያንን ለማድረግ ሥልጣን [ማንዴት] የለንም፤ ‘የፈለጋችሁት ይህ ከሆነ ሰላሙን አትፈልጉም ማለት ነው፤ ወደ እየመጣንበት እንለያይ’ ብለው፤ ልብሳቸውን ለብሰው መንቀሳቀስ ጀመረው ነበር።”

ስለ ድርድሩ አካሄድ እና የተፈጠረውን ሁኔታ በተመለከተ ደግሞ. . .

“በእኛ በኩል አቀራረቡ የተቀናጀ ነበር፤ አስተያየት ቢኖረን ለልዑካኑ መሪ አንዳንድ ማስታወሻዎች እንልክ ነበር፤ ነገር ግን የአቋም ልዩነት አልነበረም። በሌሎቹ በኩል ግን እንደሱ አልነበረም። ከአማራ ነበሩ፤ ከአፋርም ነበሩ፣ ከኦሮሞም ነበሩ። ምክንያቱም የፌደራል ብዝኃነትን የሚያንፀባርቅ ቡድን በመሆኑ እንዲፈርም የሚፈልጉ ኃይሎችም ነበሩ፤ በየጊዜው አንዳንድ ... ምክንያት እየፈጠሩ እንዳይፈረም የሚያስተጓጉሉም ነበሩ” ይላሉ።

እንዴት መቋጫ ላይ ደረሰ

ለቀናት የተካሄደው ድርድር ሰላም ሳያመጣ ሊጠናቀቅ ይችላል በሚል “በወቅቱ በጣም አዝኜ ነበር” የሚሉት አቶ አሰፋ ኬንያታ በመጨረሻ ላይ ፈርጠም ብለው መናገራቸውን ያነሳሉ።

“እኛ ብዙ ጊዜ ሰጥተናችኋል፤ አሁንም ሁለት ሰዓታት አላችሁ፤ ሚዲያዎች ተጠርተው ተዘጋጅተዋል፤ እየጠበቁን ነው፤ ስለዚህ ውይይቱ ማብቃት አለበት፤ የሚያበቃ ከሆነ ግን ‘ተስማምተው ነበር፤ የትግራይ ተደራዳሪዎች ሰላም ይፈልጋሉ፤ በመጨረሻም በእናንተ ምክንያት (በፌዴራል መንግሥት) ድርድሩ ፈራርሷል’ ብዬ አወግዛችኋለሁ” ማለታቻውን አቶ አሰፋ ተናግረዋል።

ኋለ ላይ ያለመግባባት ምንጭ የሆነው እና የተጨመረው አንቀጽ፤ “ለድርድርም የማይቀርብ ነበረ” በማለት ከመጨረሻው ሰነድ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ መደረጉን ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላም ከየአቅጣጫው በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው ሰላም ያወረደው ሰነድ ተፈረመ። ከዚያም ወዲያው ተግባራዊ መሆን መጀመሩን “ተኩስ ለማቆም ሰዓታት አልፈጀም። ይህም ከሁለታችንም በኩል የሰላም ፍላጎት እንደነበረ ያሳያል። ሁለታችንም ተዳክመን ነበር” ሲሉ ስምምነቱ እፎይታን እንደፈጠረ ያስታውሳሉ።

ፕሪቶሪያ ለህወሓት መከፋፈል ምክንያት ይሆን?

የስምምነቱ ፈራሚ የሆነው ህወሓት ከሽብርተኝነት ፍረጃ ቢወጣም እስካሁን ሕጋዊ እውቅናን አላገኘም፤ እንደ አዲስ እንዲመዘገብ የተሰጠው ውሳኔንም አልተቀበለውም።

የፓርቲው አመራሮች በሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እና [ዶ/ር] በምክትላቸው አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ድርጅቱ ለሁለት ተከፍሎ እርስ በርስ እየተካሰሰ ይገኛል።

አቶ አሰፋ በፕሪቶሪያ ‘አዲስ ጊዜያዊ አስተዳደር’ ሊቋቋም ነው የሚለው አንቀጽ ለህወሓት አመራር መለያየት ዋና ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

“በመሬት ላይ ከነበረው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር፤ ጥሩ ውጤት አምጥተናል ብለን እናስባለን፤ ሆኖም ጌታቸው እና (ጄኔራል) ፃድቃን ከፕሪቶሪያ ከመመለሳቸው በፊት የህወሓት ፖለቲካ ቢሮ ‘ክደውናል’ ሲል ከሰሳቸው። ለአንዳንዶቻችንም ሌላ ሌላ ስም ሰጡ። ይህ ውል ፈርሶ ሁለቱ በአገር ክህደት እንዲታሰሩ ለማዕከላዊ ኮሚቴ ሞሽን አቅርበዋል” ነገር ግን ተግባራዊ አልሆነም።

አቶ አሰፋ ‘የጊዜያዊ አስተዳደር’ የሚለው ስምምነት መቀለ በነበረው በተቀረው የህወሓት አመራር ላይ አንዳንድ ሥጋቶችን ፈጥሯል በማለት፤ “አሳታፊ ጊዜያዊ መንግሥት ይቋቋም ስለተባለ፣ ሥልጣኑን የተቀማ መስሎ የሚሰማው አመራርም አለ” ይላሉ።

“ያልተደሰቱ ወገኖች ነበሩ”

በስምምነቱ መሠረት በደቡብ ትግራይ እና በፀለምት ወረዳ የተወሰኑ ተፈናቃዮች የመመለስ እና መልሶ የማስፈር ጥረቶች ቢደረጉም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተፈናቀሉበት የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ እስካሁንም መፍትሄ እንዳላገኘ ይናገራሉ።

ይህ የአወዛጋቢ አካባቢዎች ጉዳይ ‘ከትግራይ ሕገ-መንግሥታዊ ሉዓላዊነት ማክበር’ እና ከፕሪቶርያ ስምምነት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ኃይሎች ምንም እንኳን ከባድ መሳሪያዎችን ቢያስረክቡም፤ ሙሉ በሙሉ ትጥቅ አለመፍታታቸው በሌላ በኩል የሚነሳ ጉዳይ ነው።

“እውነት ለመናገር በፌዴራል መንግሥት በኩል በጉዳዩ ላይ አንድ ዓይነት አቋም የለም፤ በዚሁ ምክንያት ያዘገዩበት ሁኔታዎች አሉ፤ በእኛ በኩል በጋራ ቆመን ለተግባራዊነቱ ከሠራነው ይልቅ እርስ በርስ በውስጣችን ላለው ሽኩቻ ብዙ ጊዜ እና ጉልበት አባክነናል” የሚሉት አቶ አሰፋ እንደገና ግጭት እንዳይቀሰቀስ እና ስምምነቱን እንዳይቀለበስ ስጋት አላቸው።

ፕሪቶሪያ ላይ ስምምነቱን ሊያደናቅፍ የነበረው አንቀጽ ከሰነዱ ላይ ባይኖርም በተግባር አወዛጋቢዎቹ ቦታዎች በፌዴራል መንግሥት እጅ መሆናቸውን በመጥቀስ የሚጠብቁት “ሕዝበ ውሳኔ እስኪደረግ ሳይሆን አሳልፈው እስኪሰጡን ድረስ ነው፤ የርክክብ ጉዳይ ዘግይቷል” በማለት ተናግረዋል።

አክለውም በአካባቢው የብዙ ኃይሎች ፍላጎት ያለ መሆኑን እንደሚገነዘቡ እና በፕሪቶሪያው ስምምነት ደስተኛ ያልሆኑ ወገኖች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።

“[ስምምነቱ] በተፈጥሮ ሁሉም ሰው የተቀበለው እና የሚደሰትበት ጉዳይ አልነበረም። የሻዕቢያ (የኤርትራ መንግሥት) ወዲያው ተቃውሞት እንደነበር ግልጽ ነው፤ በኋላ በመጀመሪያው ረቂቅ ላይ ስምምነት ላይ እንደተደረሰ ተረዳ፤ ነገር ግን ከዚያ በኋላ ‘ከዳችሁኝ’ በሚል ስምምነቱን ለማደናቀፍ ሲሠራ ቆይቷል” ይላሉ አቶ አሰፋ።