በትግራይ ክልል የማዕከላዊ ዞን አስተዳዳሪ ስለተፈጸመባቸው ‘የግድያ ሙከራ’ ምን አሉ?

የትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሰለሞን መዓሾ

የፎቶው ባለመብት, DW

የምስሉ መግለጫ, የትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሰለሞን መዓሾ

በትግራይ ክልል የማዕከላዊ ዞን አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን መዓሾ ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች ‘የግድያ ሙከራ’ እንደተደረገባቸው ለቢቢሲ ትግርኛ ተናገሩ።

አስተዳዳሪው እሁድ ኅዳር 8/2017 ዓ.ም. ከሰአት በኋላ በሥራ ምክንያት ከአክሱም ወደ ክልሉ ርዕሰ መዲና መቀለ በሚጓዙበት ወቅት ነው ጥቃቱ የተፈጸመባቸው።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉ ማዕከላዊ ዞን አስተዳዳሪ ሆነው የተሾሙት አቶ ሰለሞን ላይ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ በተመለከተ እስካሁን ድረስ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።

በተቃጣባቸው የግድያ ሙከራ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ዝርዝር አስተያየት ለቢቢሲ የሰጡት አቶ ሰለሞን ከዞኑ ዋና ከተማ አክሱም ተነስተው በጉዞ ላይ ሳሉ መኪናቸው በጥይት መመታቱን አረጋግጠዋል።

አቶ ሰለሞን ለቢቢሲ ትግርኛ በሰጡት ቃለ ምልልስ ድርጊቱ መፈጸሙ ምናልባትም በእርሳቸው ላይ ያነጣጠረ “የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ሊሆን እንደሚችል” ተናግረዋል።

አቶ ሰለሞንም ሆነ ከእርሳቸው ጋር በመኪናው ውስጥ የነበሩት የግል ጠባቂያቸው እና ሹፌራቸው ምንም ዓይነት ጉዳት ባይደርስባቸውም፣ መኪናቸው አራት ቦታ ያህል በጥይት እንደተመታ አረጋግጠዋል።

አቶ ሰለሞን ጥቃቱ የተፈጸመው እሁድ ከሰዓት በኋላ በግምት 8፡00 ሰዓት ላይ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ጥቃቱን በሚመለከት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚወጡ አንዳንድ መረጃዎች በአስተዳዳሪው ላይ ያነጣጠረ የግድያ ሙከራው እንዳልተፈጸመ ገልጸው ነበር።

ይህንን አስመልክቶ አቶ ሰለሞን ሲናገሩ “ምንም እንዳልተከሰተ የሚቀርቡ ነገሮች ሕብረተሰቡን ለማደናገር ያለሙ ናቸው” ብለዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመባቸው ጊዜ አቶ ሰለሞን ከአክሱም ወደ መቀለ ለሥራ እየተጓዙ እንደነበር ገልጸው፣ ማይቅነጣል የሚባል አካባቢ ሲደርሱ “ከፈላፍል አካባቢ ወደ ዕዳጋ ዓርቢ ስንዞር ነው ጥይት የተተኮሰብን” ብለዋል።

አቶ ሰለሞን ወደ ስፍራው የተንቀሳቀሱት በአክሱም፣ በማይቅነጣልና በዓብዪ ዓዲ ስብሰባዎችን የማካሄድ ዕቅዶች ተይዘው እንደነበር ተናግረዋል።

“ፖሊስ ጥበቃ እንዲያደርግልን በደብዳቤ አሳውቀናል። ስብሰባው እሁድ ነበር የሚካሄደው፤ ነገር ግን በተለያዩ መንገዶች ከሸፈ። ከዚህ በኋላ ወደ መቀለ በምጓዝበት ወቅት ጥቃቱ ተፈጸመ።” ብለዋል።

በጥይት ጥቃት የተፈጸመበት የአቶ ሰለሞን መኪና

የፎቶው ባለመብት, Selemon Measho

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አቶ ሰለሞን በወቅቱ ክስተቱን ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማሳወቃቸውን ገልጸው “በመንግሥት ኃላፊነት ውስጥ ሆነው በግላቸው አጣርተናል፤ ጥቃት እንዳልተፈፀመ አረጋግጠናል በማለት ሁኔታውን ለማድበስበስ የሚንቀሳቀሱ አካላት አሉ” ሲሉ በደብረጽዮን (ዶ/ር) የሚመራውን ቡድን ወንጅለዋል።

አቶ ሰለሞን በህወሓት ሊቀመንበር የሚመራው ቡድን “የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም በእኛ ላይ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄደ ነው” ያሉ ሲሆን፣ “አሁን ያጋጠመው ክስተት ውሸት ነው እያሉ ያሉት እነሱ ናቸው” ብለዋል።

“እኔ ለፖሊስ፣ የሠራዊት አካል ወይም ሚሊሻ ጥቃት አድርሶብኛል አላልኩም። የተተኮሰብን ጥይት ግን መኪናው ላይ አርፏል፤ መስታወቱም ተሰብሯል። ስለዚህ ሁኔታው ተከስቷል፤ ጉዳዩንም ለመንግሥት ትቼዋለሁ” ሲሉም አክለዋል።

አቶ ሰለሞን የተፈጸመው ተራ ወንጀል ስላልሆነ እርምጃ መወሰድ አለበት ያሉ ሲሆን “ይህ ካልጸዳ እና መልክ ካልያዘ ግን ነገ ጠዋት ሁሉም ሰው ላይ ይደርሳል። በአንድ የመንግሥት አመራር ላይ ብቻ የሚቆም አይደለም። ስለዚህ ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ለፕሬዝዳንቱ ጥያቄ አቅርበናል” ብለዋል።

አቶ ሰለሞን ከዚህ ጥቃት በፊት በተለያዩ አካላት ላይ የተፈጸሙ ሙከራዎች መኖራቸውን አስታውሰው፣ “ከቢሮ ማህተም ለመውሰድ የመጡ ኃይሎች ነበሩ።መንግሥትም በወቅቱ መግለጫ አውጥቶበታል። ከዚያም በመዝገብ ቤት ላይ የደረሱ ጫናዎች ነበሩ። ይህም በምርመራ ሂደት ላይ ይገኛል” ሲሉ አስረድተዋል።

አቶ ሰለሞን በማዕከላዊ ዞን ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተም በአሁኑ ወቅት እጅግ አስቸጋሪ የፀጥታ ሁኔታ መኖሩን እና በበርካታ ሰዎች ላይ ጥቃት እና ግድያዎችም እንደሚፈጸሙ አመልክተዋል።

ለዚህም እንደማሳያ በአካባቢው በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ የግድያ ወንጀሎችን የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ “በአጠቃላይ በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር ከፖለቲካው የሚቀዳ ነው። የፖለቲካ ሁኔታው በመጥፎ ደረጃ ስለሚገኝ በዚህ ምክንያት የፀጥታው ሁኔታ በጣም ችግር አለበት” ብለዋል።

አቶ ሰለሞን የተፈጸመባቸው ጥቃት ተጣርቶ መፍትሄ ካልተሰጠው አደገኛ ውጤት ሊኖረው ይችላል በማለት “እንዲጣራ እና እንዲታወቅ እፈልጋለሁ። እኛ ላይ የደረሰው ጥቃት የፈጸመውን አካል ካላወቅን ነገ ዋስትና ሊኖረን አይችልም” ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በህወሓት ሊቀ መንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል እና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ለወራት የዘለቀ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥም ውጥረትን ፈጥሯል።

ሁለቱ ወገኖች በመግለጫ እየተካሰሱ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በደብረ ጽዮን (ዶ/ር) የሚመራውን ቡድን የክልሉ አስተዳደር ላይ መፈንቀለ መንግሥት ለመፈጸም መዘጋጀቱን እና ሥርዓት አልበኝነትን ለማስፋፋት በመክሰስ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።