የህወሓት ሽኩቻ፡ “ለካ መሪዎቻችንን አናውቃቸውም ነበር”

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እና ጌታቸው ረዳ

የፎቶው ባለመብት, TPLF/DW/TIG TV

ባለፈው ወር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመሩት የህወሓት ቡድን በከፍተኛ አመራሮቹ ክፍፍል መካከል በተደረገው በ14ኛው የህወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን እና አመራሮችን ማንሳቱን አስታውቋል።

የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች በዚህ ጉባኤ ሳይገኙ መቅረታቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያላገኘው ይህ አወዛጋቢ ጉባኤን ተከትሎ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ህወሓትን አይወክሉም በማለት ከሥልጣን እንደተነሱ የእነ ደብረጽዮን ቡድን ገልጿል።

ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ጦርነት የቋጨው ግጭትን በዘላቂነት የማቆም የፕሪቶሪያው ስምምነትን ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በይፋ የተሾሙት አቶ ጌታቸው ረዳን ከኃላፊነት ለማንሳት ህወሓት ሥልጣን አለው ወይ የሚለው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው አስተዳደር በበኩሉ መግለጫውን “ይፋዊ መፈንቅለ መንግሥት” ሲል አውግዞ በቡድኑ ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ እና በዚህ ምክንያት ለሚደርስ “ጉዳት” ተጠያቂ እንደማይሆን አስታውቋል።

ትክከለኛው የህወሓት ተወካዮች ነን በሚሉት የህወሓት ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ሽኩቻ የፀጥታ ችግር ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ታዛቢዎች አመራሮቹን እየከፋፈለ ያለው አጀንዳ ሕዝባዊ ጉዳይ እንዳልሆነ እና በዚህም ለሕዝቡ ፈታኝ ሁኔታ መፈጠሩ እንደማይቀር አዝማሚያዎች ታይተዋል ይላሉ።

እየሰፋ የመጣው ልዩነት

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የትግራይ ደም አፋሳሽ ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት በከበባ ውስጥ የነበረውን ሕዝብ እፎይታ እንዲያገኝ እንዲሁም አፈሙዞች ጸጥ እንዲሉ አስችሏል።

መሠረታዊ የሚባሉት የትራንስፖርት፣ የባንክ፣ ውሃ፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋርጠውበት የነበረው ሕዝብ እንደገና አገልግሎቶች እንዲያገኙ ሆኗል።

ሕዝቡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ ልጆቹን፣ ወዳጅ፣ ዘመዶቹን ለመቅበር፣ ዕርም ለማውጣት ዕድል አግኝቷል።

አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የፈጀው ነው የተባለው ጦርነት መዘዝ አሁንም በክልሉ ውስጥ እየተስተዋለ ነው።

በጦርነቱ የወደሙት መሠረተ ልማቶች እስካሁን አልተጠገኑም፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች እስካሁን ወደቀያቸው ያልተመለሱ ሲሆን፣ በጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ኑሮን ለመግፋት እንደተገደዱ ይናጋራሉ።

በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት በጦርነቱ ወቅት በቁጥጥር ስር የዋሉ አንዳንድ የትግራይ አካባቢዎች አሁንም ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ውጪ በሆኑ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ናቸው።

የትግራይ ሕዝብ መከራ እና ችግር ባልተቃለለበት ወቅት “እርስ በርስ እየተሻኮቱ የሚገኙ የህወሓት መሪዎች በፕሪቶሪያ ውል ስም ነጋ ጠባ ቢምሉም የትግራይ ሕዝብ ቀዳሚ ጉዳያቸው አይደለም” ሲሉ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

በጦርነት የተጎዳውን ሕዝብ እና ክልሉን ለመታደግ ከመሯሯጥ ይልቅ ከስምምነቱ ማግስት ጀምሮ በመካከላቸው ያለው ቅራኔ እየሰፋ እና እየተፈራቀቁ መጥተዋል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ውስጣዊ ልዩነት ጊዜያዊ ጥምር መንግሥት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተፈጠረ እንደሆነ ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።

ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እና ጌታቸው ረዳ

የፎቶው ባለመብት, TIGRAY TV

“መሪዎቻችንን አናውቃቸውም ነበር”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ህወሓት መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ እና ኢንተርኔት በሌለበት አጋጣሚ በካድሬዎች ለመደበቅ እየተሞከረ ያለውን የአደባባይ መረጃ ሲያጋልጥ የነበረው እና ህወሓትን በመተቸት የሚታወቀው የፖለቲካ አክቲቪስቱ ፍፁም ብርሃነ “አመራሮቹን አላውቃቸውም ነበር ማለት” ነው ይላል።

ለዚህም እንደ ምክንያትነት የሰጠው በአሁኑ ወቅት የህወሓት አመራሮች እያጋለጡት ያሉ ምሥጢሮችን ዋቢ በማድረግ ነው።

“እስካሁን ድረስ የራሳቸውን ጉድ እስኪያወጡ ድረስ ማን እየመራኝ እንደነበር አላውቅም። እያወጡት ያሉት ምሥጢሮች የራሳቸው ብቻ አይደለም፤ የእኛም ነው፤ በፍፁም አናውቃቸውም ነበር” ይላል።

በሁለቱ የህወሓት ቡድኖች መካከል ያለው ቅራኔ መስፋትን ተከትሎ አንዱ ቡድን ስለሌላው እያጋለጠ ያለው “ምሥጢር” አስቀድሞ ለሕዝብ መታወቅ እንደነበረበትም ያስረዳል።

የተከፋፈሉት የህወሓት አመራሮች በተለያዩ ሚዲያዎች እየወጡ አንዳቸው ሌላኛቸውን የሚያጣጥሉ ምሥጢሮችን እንዲሁም ታማኝነትን ለመንጠቅ እየሞከሩ ይገኛሉ።

ከኤርትራ መሪዎች ጋር በምሥጢር የተደረገ ግንኙነት ነበር ሲሉ እርስ በርስ እየተወቃቀሱ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አጋር ሆኖ በትግራይ ጦርነት ተሳታፊ የነበረው የኤርትራ ሠራዊት የጦር ወንጀሎችን እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መፈጸሙን የተባበሩት መንግሥታት መርማሪ ቡድንን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በሪፖርቶቻቸው አጋልጠዋል።

የኤርትራ መንግሥት ይህንን ክስ አይቀበልም።

በጦርነቱ ወቅት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎች ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንዲሁም ሰለባዎች ፍትህ እንዲያገኙ እየተሟገቱ ያሉ አካላት ይህ ጉዳይ “እንዳሸማቀቃቸው” እየተናገሩ ይገኛሉ።

የሸረ እንዳሥላሴ ከተማ ነዋሪ እና የአገር ሽማግሌው አቶ አረጋይ አየለ ከተማቸው በኢትዮጵያ ጦር በተያዘችበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጦር አዛዦች ጋር ተገናኝተው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ስላንዣበበ አደጋ በመናገር ትልቅ ሚና የተጫወቱ የ87 ዓመት አዛውንት ናቸው።

“እያጋጠመን ያለው ሁኔታ ከበፊቱ ጋር ሲነጻጸር የከፋ ነው። እነዚህ ልጆች [የህወሓት አመራሮች] በትግሉ ወቅት ከሕዝባቸው ጎን ሲፋለሙ ከደረሰው ጠባሳ እና ውድመት ለማንሰራራት እንደሚሠሩ ተስፋ አድርገን ነበር” የሚሉት እኚህ አዛውንት “ለሕዝብ ግልጽ ባልሆነ መንገድ እርስ በርሳቸው እየተነካከሱ አደጋ ላይ ጥለውናል” በማለት ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በህወሓት ውስጥ የተፈጠረው መከፋፈል በእጅጉ እንዳሳዘናቸውም ይናገራሉ።

የህወሓት አመራሮች በተለያዩ አካካቢዎች ተዘዋውረው ኅብረተሰቡን በሚያናግሩበት ወቅት የአካባቢያችን አርሶ አደር ‘በዚህ ዓመት ጥሩ ምርት ተገኝቷል፣ አርሰን ለመብላት ነግደን ለመግባት ሰላም ፍጠሩልን’ ብሎ እየለመናቸው ነው። እነርሱ ግን ጀሮ ዳባ ልበስ እያሉ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ብርቱካን ሃፍቱ በበኩላቸው “ለበርካታ ህጻናት እና እናቶች እልቂት ወደ ሆነው ጦርነት እንደገና ልንገባ እንችላለን” የሚለው ሃሳብ ስጋት እንዳሳደረባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በጦርነት ጊዜ አንድ ሆነን አሁን በዚህ በተረጋጋ ሁኔታ ወደ እንደዚህ ዓይነት መከፋፈል እንገባለን ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር” ይላሉ።

ከቅርብ ቀናት በፊት መስከረም 27/ 2016 ዓ.ም. በሁለቱ የህወሓት ቡድኖች ከረር ያሉ መግለጫዎች እንዲሁም የትግራይ ኃይሎች ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ተከትሎ በከተማው ሕዝብ ላይ ፍርሃት እንደነገሰ ቢቢሲ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

አንዳንድ ነዋሪዎች ገንዘባቸውን ከባንኮች አውጥተው ከመቀለ ወደ አዲስ አበባ እያጓጓዙ እንዳሉም ከአንዳንድ ስፍራዎች የተገኘው መረጃ ያሳያል።

በደብረጽዮን የሚመራው ህወሓት ያደረገው ጉባዔ

የፎቶው ባለመብት, TPLF

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በፖለቲከኞቹ ላይ የሚታየው ሽኩቻ በሕዝቡ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እንዳሳሰባቸው ይናገራሉ።

ከምዕራብ ትግራይ ቃፍታ ሁመራ ወረዳ ተፈናቅለው ላለፉት 3 ዓመታት በሸራሮ በጊዜያዊ ጣቢያ ተጠልለው የሚገኙት አቶ አሰፋ ገብረሕይወት “እንዲህ ያለው በአመራሮች መካከል መከፋፈል ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው” ይላሉ።

ካለፈው ወር ጀምሮ አዳዲስ ተፈናቃዮች ከእነዚህ አካባቢዎች እየተፈናቀሉ ወደ ጊዚያዊ መጠለያው እየመጡ እንደሆነ ገልጸው በዚህም የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈጻሚ ይሆናል ብሎ ማሰብ “ዘበት” መሆኑን ያክላሉ።

የአክሱም ከተማ ነዋሪ አቶ ክብሮም ይትባረክ በበኩሉ አሁን ያለው ሽኩቻ “ትልቁ ውድቀት፣ የእኔ ጥፋት ያንተ ጥፋት ብሎ ከመተራረም እርስ በርስ መወቃቀስ በመሆኑ ሕዝብን ወደ ጭንቀት ከትቶታል” ይላል።

መጪው ጊዜ አስፈሪ የሆነበት ክብሮም “ዕጣ ፈንታችን ምንድን ነው? እንደገና ወደ መጥፎ ጊዜ ልንመለስ ነው?” ሲል ይጠይቃል።

አክሎም “የውጭ አካል ቢሆን ኖሮ ጠላት ነው ትላለህ። አመራሮቹ ዓላማቸው ምንድን ነው? ከሥልጣን ውጪ ሌላ ዓላማ ያላቸው አይመስለኝም” ይላል።

በጦርነቱ ለሞቱ ሰዎች የተደረገ ኃዘን

“ከተጠያቂነት ለማምለጥ ነው”

ፍጹም ብርሃነ በህወሓት አመራሮች መካከል መከፋፈልን የፈጠረው ጉዳይ የሕዝብ አጀንዳ ነው ብሎ አያምንም።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት መፈጸም የነበረባቸው ጉዳዮች መዘግየታቸውን ጠቅሶ “አሁንም ተኩስ ባይኖርም ጦርነት አለ” ብሎ ያምናል።

“የወደሙ ጤና ጣቢያዎች ሳይገነቡ እና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ሳይመለሱ ይህ ነገር መከሰቱ በጣም አሳዛኝ ነው” ይላል።

በተጨማሪም ወደ ጦርነት ያመሩ ሁኔታዎች፣ ጦርነቱ የተመራበት እና የተቋጨበት መንገድ እና ከጦርነቱ በኋላ ያለው ሁኔታ ተገምግሞ እያንዳንዱ ተጠያቂ እንዲሆን ፍጹም ጥሪ አቅርቧል።

ነዋሪዎቹ አሁን ያለው ሁኔታ ካለፈው ከበባ የበለጠ አደገኛ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።

የሁለቱም ቡድኖች ደጋፊ እንዳልሆነ የሚናገረው ፍጹም “ሁለቱም ሥልጣን ላይ እንዲቆዩ ሳይሆን ለፍርድ መቅረብ ይገባቸዋል” ይላል።

የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት በመማገድ የህወሓት አመራሮች ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ አጽንኦት የሚሰጠው ፍጹም፣ ከዚያም አልፎ አሁን ደግሞ ሕዝቡን በአውራጃዊነት እየከፋፈሉት ነው ይላል።

“እነሱ እየተከተሉት ያለው መንገድ አደገኛ ነው። የሠሯቸው ስህተቶች ወደ ሕዝቡ እየወረደበት ያለበት አውራጃዊነት ሆን ተብሎ እየተሠራ እንደሆነ የሚያሳይ ነው” ይላል።

አክሎም “ተጠያቂ መሆን ካለባቸው ሰላም ሊኖር ይገባል። ይህንንን ስለሚያውቁ ነው ሕዝቡን በአካባቢ እና በአውራጃ ለመከፋፈል እና እርስ በርስ ለማጋጨት እየጣሩ ያሉት።ከተሳካላቸው ደግሞ ወደ ከበባው ተመልሰን እንገባለን” የሚል ስጋት አለው።

አቶ አረጋይ አየለ በበኩላቸው የህወሓት መሪዎች “ልዩነቶቻቸውን አጥብበው አንድ ላይ ሊመሩን ከቻሉ ምኞታችን ነው። በአንድነት መምራት ካልቻሉ ግን በበለጸጉ አገራት እንደሚደረገው ሥልጣናቸውን ያስረክቡ” ይላሉ።

ተመሳሳይ አስተያየት ያለው ፍፁምም “ሕዝቡ አካሌ ጎድሎ ድሌን ያንቋሸሸው ማን ነው? ልጆቼ የተሰዉበትን ዓላማ ከንቱ ያስቀረው ማን ነው? ብሎ ሊጠይቅ ይገባል” ሲል አጽንኦት ይሰጣል።

“ነዋሪው ያለፈው ይበቃናል ማለት አለበት ካልሆነ ሁኔታው ወዴት እንደሚሄድ ማወቅ አለበት። ከነበረው የከፋ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል” በማለት ስጋቱን ገልጿል።

ጌታቸው ረዳ ፣ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እና ፈትለወርቅ ገብረእግዚኣብሄር

የፎቶው ባለመብት, TPLF

መፍትሄ

ክብሮም የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች ጉዳዩን በአግባቡ እንዲከታተሉ በማሳሰብ መፍትሄ ያቀርባል።

“ተስማምተው ከቀጠሉ ጥሩ ነው፤ ካልሆነ ግን የፀጥታ ኃይሎች ከላይ ሆነው በሕዝቡ ላይ ችግር በማይፈጥር መንገድ እርምጃ መውሰድ አለባቸው” ይላል።

ፍፁም ብርሃነ በበኩሉ መፍትሄው ሁሉን አቀፍ መንግሥት መመሥረት ብቻ እንደሆነ ያምናል።

የጥምር መንግሥት ጉዳይ ውዝግብ ማስነሳቱ እና የትግራይ ክልላዊ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከሂደቱ ማግለላቸው የሚታወስ ነው።

ፍፁም በትግራይ ውስጥ “ህወሓት ያልነካው ነጻ ማኅበረሰብ እንደሌለ እና ጊዜያዊው የጥምር መንግሥት 99 በመቶው እራሱ ህወሓት” እንደሆነ ይጠቅሳል።

የትግራይ ዓለም አቀፍ ምሁራን ማኅበርን ጨምሮ በጊዜያዊ መንግሥት የተሳተፉ ሁሉ የህወሓት ተጽእኖ አለባቸው ሲል የሚተቸው ፍፁም፣ እያንዳንዱ የትግራይ ተወላጅ ይወክለኛል የሚለውን አካል ያካተተ ሁሉን አቀፍ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲቋቋም ይጠይቃል።

“ሌላ ማንም ሊያድነን አይችልም” ሲልም ይደመድማል።

“የተከፋፈሉት የህወሓት አመራሮች የውስጥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት ሲቸገሩ እና የችግራችን ምንጭ ከሆነው ኃይል መፍትሄ ሲጠይቁ ማየት ይቅር የማይባል ነገር ነው” የሚሉት ደግሞ አረጋይ አየለ ናቸው።

አክለውም “መሪዎቹ የአገር ሽማግሌዎችን ሃሳብ ሰምተው መግባባት ከቻሉ ጥሩ ነው፤ ካልሆነ ግን ሥልጣን ይልቀቁ በሌሎች ምሁራን ልጆቻችን እንመራለን እስከሚል ድረስ አቋም እንወስዳለን” ይላሉ።

ነገር ግን “ወደ ጦርነት እንግባ የሚል መሪ ካለ እኛ እንደ አገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎች እንቃወማለን” በማለት የሕዝቡን የሰላም ፍላጎት አንጸባርቀዋል።