አብን "በአማራ ሕዝብ ስም የሚደረገው የነፍጥ እንቅስቃሴ ጠላፊ እጆች እየበዙበት ነው" አለ

መሣሪያ ያዘ ሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ በአማራ ክልል ውስጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ በሌሎች ኃይሎች እየተጠለፈ መሆኑን በመግለጽ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲፈለግ ጥሪ አቀረበ።

ፓርቲው ባወጣው መግለጫ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች በማገርሸታቸው "ዳግም ሰብዓዊ ቀውስ የሚዳርግ ሁከት" እየተከሰተ ነው ብሏል።

አብን በዚህ መግለጫው እንደ የአካባቢዎቹ ባለው ነባራዊ ሁኔታ "የተመጠነ ፀጥታ አካላት ስምሪት ያለመኖር እና የሕግ ማስከበር ሥራዎች መላላት" የክልሉን ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈሉት ነው ሲል ገልጿል።

የአብን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ካደረገው ውይይት በኋላ ባወጣው በዚህ መግለጫ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች፣ ለክልሉ ሕዝብ እንዲሁም ለአማራ እና የፌደራል መንግሥታት ጥሪ አቅርቧል።

አብን ማክሰኞ የካቲት 3/2018 ዓ.ም. በይፋዊ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል ባለፉት ጥቂት ጊዜያት ታይቶ የነበረው አንጻራዊ መረጋጋት ከሰሞኑ ወደ ተባባሰ የትጥቅ እንቅስቃሴ መቀየሩን ገልጿል።

በክልሉ የሚደረገው የትጥቅ እንቅስቃሴ የአማራን ሕዝብ ትግል "ማዕከል አልባ በማድረግ ጥያቄዎቹን ከሥርዓታዊ ማዕቀፍ የሚያወጣ" እንደሆነ ፓርቲው በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

ይህም የክልሉን ሕዝብ "የሃሳብ መሪ የሚያሳጣ ተቋም እና መንግሥት አልባ የሚያደርግ" መሆኑን አመልክቷል።

የግጭት እና የጦርነት ፖለቲካ ለአማራ ክልል ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች መልስ የማያስገኝ እንደሆነም አብን በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በክልሉ እንቅስቃሴ እያደረጉ ላሉ ኃይሎች በማለት ባስለተላለፈው መልዕክት "በአማራ ሕዝብ ስም የሚደረገው የነፍጥ እንቅስቃሴ ጠላፊ እጆች እየበዙበት" መሆኑን ገልጿል።

በዚህም የተነሳ በክልሉ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ኃይሎች "የሰላም አማራጭን እና የፖለቲካ መፍትሄን" እንዲቀበሉ ጥሪ አቅርቧል።

አብን በክልሉ ይንቀሳቀሳሉ ያላቸውን እነዚህን ኃይሎች በስም አልገለጸም።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በዚህ መግለጫው የክልሉ ሕዝብ "የተጋረጠውን አሁናዊ አደጋ በልኩ ተጋፍጦ ራሱን አርነት እንዲያወጣ" መልዕክቱን አስተላልፏል።

"ሕዝባችን ከዚህ ታሪካዊ ቀውስ ለመላቀቅ የሚያደርገው ትግል ከግብ እንዲደርስ ያላሰለሰ ጥረት እንደምናደርግ ለማረጋገጥ እንወዳለን" ሲልም አብን የፓርቲውን አቋም ይፋ አድርጓል።

አብን የፌደራል እና የአማራ ክልል መንግሥታት "የሕግ እና የፖለቲካ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ" ከዚህ ቀደም ሲያቀርብ የነበረውን ጥሪ አሁንም በድጋሚ ለማቅረብ መገደዱን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የፌዴራል እና የክልል መንግሥታት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ የጠየቀው አብን፤ ሕዝቡ የራሱን ሰላም እንዲያስከብር ተቋማዊ የማብቃት ሥራዎችን በማከናወን ሰብአዊ ደኅንነትን የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስቧል።

በክልሉ ባለው የፀጥታ ሁኔታ "ተዋናይ ከሆኑ አካላት ውስጥ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የተሰለፉ እና በሕዝቡ ላይ የማይሽር ክህደት የፈጸሙ" ኃይሎች አሉ በማለት አብን ወንጅሏል።

በአንጻሩ "ከጠላት ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻን የተጸየፉ ኃይሎች" እንዳሉም ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል።

በተያያዘ ዜና የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ማክሰኞ የካቲት 3 ዕለት በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ባሰፈረው አጭር መልዕክት በክልሉም ሆነ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱ ግጭቶች "አመራር የሚሰጣቸውና ሎጀስቲክ የሚቀርብላቸው ከመቀሌ እና አሥመራ" መሆኑን አስፍሯል።

ወልቃይትን፣ ጠለምትን እና ራያን ለመቆጣጠር ያቀደው ህወሓት፣ ለአማራ ክልል ጽንፈኛ ቡድን የሠጠው ተልዕኮ "ከውስጥ ግጭት በመፍጠር" ወደ ድንበር የሚጓዘው መከላከያ ሠራዊት በየዞኑ እና ወረዳው ተወጥሮ እንዲቆይ ማድረግ ነው ሲል ቢሮው ከስሷል።

አብን በበኩሉ በክልሉ እየተካሄደ ያለው የትጥቅ እንቅስቃሴ "በኢትዮጵያና በሕዝባችን ላይ የሚጋሩት ጠላትነት ያስተሳሰራቸው ኃይሎች" የተሳተፉበት መሆኑን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

አብን "ጠላትነት ያስተሳሰራቸው ኃይሎች" ያላቸውን አካላት በስም ባይጠቅስም "ታሪካዊ ጠላቶች" ሲል ግን ፈርጇቸዋል።

ፓርቲው በመግለጫው እነዚህ ኃይሎች "አንድም የአማራን ሕዝብ ዘላለማዊ ዕረፍት የመንሳት ዓላማቸውን ለማሳካት፣ በሌላ በኩል አገር ለማፍረስ የእጅ አዙር አመራር የሚሰጡበት እና የሚሳተፉበት እየሆነ መምጣቱን ተገንዝበናል" ብሏል።

የትጥቅ እንቅስቃሴውን "ለኢኮኖሚ ዓላማ የሚጠቀሙ" አካላት እንዳሉም አብን በመግለጫው ከስሷል።