አቶ ጌታቸው ረዳ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ተግባራት በሚያደናቅፉ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ

የፎቶው ባለመብት, TPLF/FB
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የሹመኞች ምደባን ጨምሮ የአስተዳደራቸውን ተግባራት የሚያደናቅፉ አካላት ላይ “ህጋዊ እርምጃ” እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ።
አቶ ጌታቸው ረቡዕ፣ ነሐሴ 22/ 2016 በወጣው መግለጫቸው ይህንን ያሉት በህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው ቡድን በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሚደረግ ሹም ሽር ተፈጻሚ እንደማይሆን ለሁሉም የዞን እና ወረዳ ጽ/ቤቶች በላከው ደብዳቤ ማስታወቁ አወዛጋቢ መሆኑን ተከትሎ ነው።
አቶ ጌታቸው ህጋዊ እርምጃ የመውሰድ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያን የሰጡት በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ጎልቶ ክፍፍል በሰፋበት እና ወደ ኃይል እርምጃ እንዳይሸጋገር ስጋቶች በነገሱበት ወቅት ነው።
አቶ ጌታቸው በትናንትናው መግለጫቸው ሁሉንም ህጋዊ አሰራሮች በመጣስ ጉባኤውን ያካሄደው በደብረጽዮን የሚመራውን የህወሓት ቡድን “በክልሉ ስርዓት አልበኝነት ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ነው” ሲሉ ከሰዋል።
በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ እንቅፋት የሚፈጥር ማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል አቶ ጌታቸው አስጠንቅቀዋል።
“ይህንን የመንግሥት ውሳኔ የሚያደናቅፍ ማንኛውም አካል [ኃይል] ህጋዊ አሰራርን በመከተል ተጠያቂ የሚደረግበት እና ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ያለው ህዝባችን እንዲያውቅልን እንፈልጋለን” ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ ጌታቸው አስተዳደራቸው ሊወስድ ይችላል ስላሉት እርምጃ ምንነት ተጨማሪ መረጃዎችን አልሰጡም።
አክለውም “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ህዝባችንን ፈጣን፣ ቀልጣፋ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማገልገል ከላይ እስከታች ያለውን ክልላዊ የሹም ሽር ሂደቶችን አጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ ህዝቡ ይህንን ሊረዳ ይገባል የሚል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ለበርካታ አስርት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ጉልህ ሚና የተጫወተው ህወሓት በከፍተኛ አመራሮቹ መካከል የተፈጠረው ቅራኔ ጎልቶ ክፍፍል ውስጥ ገብቷል።
በከፍተኛ አመራሮቹ ክፍፍል መካከል የተደረገው የህወሓት 14ኛ ጉባኤ እንዲሁም ፓርቲው ህጋዊ ሰውነት ለማስመለስ ለምርጫ ቦርድ የቀረበው ጥያቄ በሁለቱ ቡድኖች መካከል መወዛገቢያ ሆነዋል።
ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን ድጋሚ ሊቀመንበር አድርጎ በመረጠው አወዛጋቢው የህወሓት ጉባዔ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር እና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የድርጅቱ ቁጥጥር ኮሚሽን፣ አብዛኞቹ የደቡብ እና የደቡብ ምሥራቅ ትግራይ ወረዳዎች እንዲሁም የመቀለ ከተማ ክፍለ ከተሞች ሳይገኙ መቅረታቸው ይታወሳል።
በአወዛጋቢው 14ኛው የሕወሓት ጉባኤ ያልተገኙ እና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያሉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ስራ አስፈጻሚዎች ድርጅቱን እንደማይወክሉ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ከሰሞኑ አስታውቀዋል።
ደብረጽዮን ከዚህ ቀደም ህወሓትን ወክለው በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የገቡ ህወሓትን ስለማይወክሉ ድርጅቱ ወካዮቹን ማስቀመጥ እንዳለበት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አቶ ጌታቸው ረዳ የደቡብ ምስራቅ እና የሰሜን ምዕራብ ዞኖችን አስተዳዳሪዎች በማንሳት አዳዲስ ሹመት መስጠታቸውን ተከትሎ በደብረጽዮን በሚመራው ህወሓት ተቃውሞዎችን እያሰማ ይገኛል።
በቅርቡ የሕወሓት ጽ/ቤት ዋና ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር ከሰሞኑ ለሁሉም የዞን እና ወረዳ ጽ/ቤቶች በላኩት ደብዳቤ "የፓርቲውን አሠራር እና ሕጋዊ አካሄድ ባልተከተለ መንገድ የስልጣን ሹምር ሽር እየተካሄደ ነው" በማለት ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ፈትለወርቅ ይህንን ደብዳቤ የጻፉት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የደቡባዊ ምስራቅ ዞን አስተዳዳሪ የነበሩትን ሊያ ካሳን እንዲሁም የሰሜን ምዕራብ ዞን አስተዳዳሪን ተኽላይ ገብረ መድህን ከስልጣን በማንሳት ሌሎች ሰዎችን መሾማቸውን ተከትሎ ነው።
በሁለቱም አመራሮች በኩል የህወሓት ህጋዊ ወኪሎች እኛ ነን የሚሉ እንዲሁም በጊዜያዊ አስተዳደሩ ያሉ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ስራ አስፈጻሚዎች ትግራይን የማስተዳደር ጉዳይ እያከራከራቸው ይገኛል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ በደብረጽዮን የሚመራውን ህወሓት “አፈንጋጭ ቡድን” ሲሉ የጠሩት ሲሆን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ስልጣን የመንጠቅ ስራ እንደሆነ ከሰሞኑ ከትግራይ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ኤርቪን ማሲንጋ በህወሓት እና የትግራይ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት እንዲሁም ከህወሓት አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል።
ለሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት ወደ ትግራይ መዲና መቀለ ያመሩት አምባሳደሩ የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን ሁኔታ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲሁም ከህወሓት አመራሮች ጋር መምከራቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ጦርነት የቋጨውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ውጤታማ አፈጻጸም፣ ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለስ እና እንዲሁም በክልሉ ዘላቂ ሰላም የሚመጣበትን መንገድ ላይ ውይይት እንደሚደረግ የኤምባሲው መግለጫ ጠቁሟል።
በአመራሮቹ እና በአባላቱ መካከል ክፍፍል በተፈጠረው የሕወሓት ፖለቲካዊ ክፍፍል ወደ ጸጥታ ስጋቶች እንዳይቀየር እየተሰራ መሆኑን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ከሰሞኑ መናገራቸው ይታወሳል።
የጸጥታ ኃይሉ ገለልተኛ እንዲሆን እና ፖለቲካዊ ልዩነቶች በውይይት እንዲቋጩ ጄነራል ታደሰ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ልዩነቶችን በኃይል አማራጭ ለመፍታት መሞከር ቀይ መስመር ናቸው የተባሉትን መተላለፍ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።












