"ከአሜሪካ ይልቅ ዴንማርክን እንመርጣለን" - የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር

የግሪንላንድ እና የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በጋር ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሕዝባቸው "አሁኑኑ" ምርጫ ቢቀርብላቸው ከዩናይትድ ስቴትስ ይልቅ ዴንማርክን እንደሚመርጡ ተናገሩ።

የንስ ፍሬድሪክ ኒየልሰን ከዴንማርኳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው ጠንከር ያለ አቋማቸውን ያስታወቁት።

ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው የዴንማርክ ግዛት መሪ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድ ለመገንጠል ያላቸውን አቋም በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት።

ትራምፕ ሀገራቸው ግሪንላንድን "መጠቅለል" የሚፈልጉት ራሳቸውን ከሩሲያ እና ቻይና ለመጠበቅ እንደሆነ ይናገራሉ። ዋይት ሐውስ ደሴቷን ለመግዛት ዕቅድ እንዳለው ይፋ ቢያደርግም ኃይል መጠቀም የሚለውን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አላደረገም።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል-ኪዳን (ኔቶ) አባል የሆነችው ዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜተ ፍሬድሪክሰን ወታደራዊ እርምጃ የጦር ቃል-ኪዳኑ

መጨረሻ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

ኒየልሰን ስለሰጡት አስተያየት የተጠየቁት ትራምፕ "እሱ የነሱ ችግር ነው። በዚህ ሐሳቡ አልስማማም. . . ይህ ለሱ ትልቅ ጋሬጣ ይዞበት ይመጣል" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ከመሬት ስፋቷ አንፃር እጅግ ትንሽ ሰው የሚኖርባት ግሪንላንድ በሰሜን አሜሪካ እና አርክቲክ መካከል መገኘቷ የሚሳዔል ጥቃት ቢመጣ ቀድሞ ለማሳወቅ እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን ለመቆጣጠር ወሳኝ ሥፍራ ያደርጋታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ ደጋግመው ግሪንላንድ ለአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት አስፈላጊ ናት ይላሉ። "የቻይና እና ሩሲያ መርከቦች አካባቢውን ወረውታል" ቢሉም ለዚህ ማስረጃ አላቀረቡም።

አሜሪካ ሰሜን ምዕራብ ግሪንላንድ በሚገኘው ፒቱፊክ የጦር ካምፕ 100 ያክል ወታደሮች ያሏት ሲሆን ይህ ካምፕ ከሁለተኛ ዓለም ጦርነት ጀምሮ በአሜሪካ ሲመራ ቆይቷል።

አሜሪካ ከዴንማርክ ጋር ባላት ስምምነት መሠረት የፈለገችውን ያክል የወታደር ቁጥር ወደ ግሪንላንድ መላክ ትችላለች።

ነገር ግን ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ሀገራቸው የምትፈልገው የሊዝ ስምምነት ሳይሆን "ባለቤትነት" ብለው "ኔቶ ይህን መረዳት አለበት" የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።

በዴንማርክ ዋና ከተማ ኮፐንሀገን በተካሄደው የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ድሬድሪክሰን "ከቅርብ አጋራችን እየደረሰብን ያለው ጫና ፍፁም ተቀባይነት ያለው አይደለም" ሲሉ ፈርጠም ያለ አቋማቸውን አስታውቀዋል።

"በጣም አስቸጋሪ የሚባለው ጊዜ ከፊታችን መሆኑን የሚጠቁሙ በርካታ ጉዳዮችን እያየን ነው" ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

የግሪንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር "ጂኦፖለቲካዊ ቀውስ ተጋርጦብናል" ብለው ነገር ግን የደሴቷ አቋም ግልፅ መሆኑን አስረድተዋል።

"ዛሬውኑ ከዴንማርክ እና ከዩናይትድ ስቴትስ መካከል አንዱን መምረጥ ቢኖርብን ዴንማርክን እንደመርጣለን" ብለዋል።

"ለሁሉም ግልፅ እንዲሆን የምንፈልገው አንድ ነገር አለ። ግሪንላንድ በአሜሪካ ቁጥጥር ሥር መሆን አትፈልግም። በአሜሪካ መተዳደር አትፈልግም። የዩናይት ስቴትስ ግዛት መሆን አትፈልግም።"

የዴንማርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላርስ ራሰመሰን እና የግሪንላንድ አቻቸው ቪቪያን ሞትዝፌልድት ወደ አሜሪካ ተጉዘው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጄዲ ቫንስ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኔቶ አባል የሆኑ የአውሮፓ ሀገራት እና ካናዳ ለዴንማክር ያላቸውን ድጋፍ ገልፀዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት መወሰን የሚችሉት ግሪንላንድ እና ዴንማርክ ብቻ ናቸው ብለዋል።

ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በአውሮፓውያኑ 2019 ግሪንላንድን ለመግዛት ጠይቀው ደሴቷ እንደማትሸጥ ተነግሯቸው ነበር።

በተለይ በቅርብ ዓመታት የግሪንላንድ ተፈጥሯዊ ሀብት የሆነ ሚኒራሎች፣ ዩራኒየም እና አይረንን የመሳሰሉ ማዕደናት ተፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል። በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያቷ የደሴቷ በረዶ እየቀለጠ መምጣቱ ማዕድናቱን ለማውጣት ቀላል አድርጎታል። ሳይንቲስቶች ደሴቷ ከፍተኛ የሚባል የነዳጅና የጋዝ ክምችት እንዳላት ይናገራሉ።