የልደት ምስክር ወረቀት ወይም መታወቂያ ባለመኖር የሚከሰት አገር አልባነት

አርኖልድ ንኩብ መኪና እያጸዳ

የፎቶው ባለመብት, Christian Parkinson / BBC

የምስሉ መግለጫ, አርኖልድ ንኩብ ደቡብ አፍሪካዊ መሆኑን ማረጋገጥ ባለመቻሉ ትምህርቱን ማጠናቀቅ አልቻለም

ብዙ ሰዎች የልደት የምስክር ወረቀታቸውን ወይም ተመሳሳይ ማስረጃዎቻቸውን እንደ ቀላል ነገር ሊቆጥሩት ይችላሉ። ካስቀመጡበት መሳቢያ ሳያወጧቸው እና ብርሃን ሳያያቸው ኖረውም ይሆናል።

ነገር ግን ምንም እንዲህ ዓይነት ማስረጃ ለሌላቸው ሰዎች ሕይወታቸውን ጥላ እንዲያጠላበት ወይም እርግጠኝነት እንዲጎድለው ሊያደርግ ይችላል።

ይህ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን እንደሚጎዳ የሚታሰብ ሲሆን እነዚህም አገር አልባ እንደሆኑ ይገለጻል።

የ25 ዓመቱ ደቡብ አፍሪካዊ አርኖልድ ንኩብ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ነው።

አርኖልድ በመንግሥት የተሰጠ አንድም ሰነድ ስለሌለው፣ በጆሃንስበርግ አቅራቢያ በሚገኘው የቴምቢሳ ከተማ መኪና በማጠብ ሕይወቱን ይገፋል።

የተወለደው በጆሃንስበርግ ሲሆን አባቱም ደቡብ አፍሪካዊ በመሆኑ ዜግነት ለማግኘት ብቁ ነው። ነገር ግን ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመመዝገብ ሲሞክር የልደት የምስክር ወረቀት እንደሌለው ተገነዘበ።

አባቱ ከመወለዱ በፊት እና እናቱ ደግሞ 14 ዓመት ሲሆነው ጥለውት ስለሄዱ ደቡብ አፍሪካዊ መሆኑን ማረጋገጥ አልቻለም።

"በጣም የሚረብሽ ነገር ነው" ይላል። "መኖርህ የማይታይ ነው። የለህም። ልክ በጥላ ውስጥ እንደመኖር ነው። የባንክ አካውንት የለህም፤ የምትተዳደርበት ጥሩ ሥራ ለማግኘት ማመልከት አትችልም።"

አክሎም በጎውን እያሰበ ለመቆየት እንደሚሞክር ነገር ግን ፈታኝ እንደሆነበት ይናገራል።

"እኩዮቼን ሳያቸው ትምህርታቸውን ጨርሰዋል። እኔ ግን ከዚህ በላይ መማር አልቻልኩም። ብዙ ነው። ጭንቀት በአንድ ወቅት ጓደኛዬ ነበር።"

አርኖልድ በደቡብ አፍሪካ ቢወለዱም ዜግነታቸወን አረጋግጠው የሕዝብ አገልግሎቶችን ለማግኘት ካልቻሉ 10,000 ያህል ዜግነት የሌላቸው ሰዎች አንዱ ነው።

እዚህ አገር አልባ ስለሆኑ ሰዎች ይፋዊ መረጃ የለም፤ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች ሕይወታቸውን ለማሸነፍ ባገኙት ውስጥ ሁሉ ስለሚሰማሩ ነው።

ስለዚህ እነሱን በሚመለከት ያሉት መረጃዎች ሁሉ እንደ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ እና የሲቪል መብቶች ድርጅቶች ያሉ ድርጅቶች በሚያደርጉት ግምት ላይ የተመሰረተ ነው።

ዜግነት ከሌላቸው፣ አገር አልባ ሰዎች ሰነዶችን ማግኘት አይችሉም፤ ከዚህ በተጨማሪም እንደ ትምህርት እና የጤና እንክብካቤ ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ይቸገራሉ።

የአገር አልባነት የሚከሰተው በብዙ ምክንያቶች ሲሆን ከእነዚህም መካከል የአስተዳደር እንቅፋቶችና ደካማ የመዝገብ አያያዝ ይገኙበታል። በዚህም ምክንያት በብዙ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ አገር አልባ ሰዎች ቁጥር ለመለካት አስቸጋሪ ነው።

ክሪስቲ ቺተንጉ

የፎቶው ባለመብት, Ed Habershon / BBC

የምስሉ መግለጫ, ክሪስቲ ቺተንጉ አገር አልባ መሆኗን ያወቀችው በ17 ዓመቷ ነው
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሰብዓዊ መብት ጠበቃ የሆነችው ክሪስቲ ቺቴንጉ በአንድ ወቅት አገር አልባ ነበረች።

የደቡብ አፍሪካ ዜግነት ያገኘችው የሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሰሩ ጠበቆች በነጻ ጉዳይዋን ይዘው ከተከራከሩላት በኋላ ነው።

"በ17 ዓመቴ አገር አልባ መሆኔን ተረዳሁ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህሬ ወደ ቢሮዋ ጠራችኝና ምንም ዓይነት ሰነድ እንደሌላት እና እንዴት ትምህርት ቤት እንደገባሁ እንዳልተረዳች ነገረችኝ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

"በጆሃንስበርግ ከሁለት የውጭ አገር ወላጆች [ሁለቱም ከዚምባብዌ የመጡ] ተወለድኩ፤ ስወለድም በእጅ የተጻፈ የደቡብ አፍሪካ የልደት የምስክር ወረቀት ተሰጠኝ።"

ነገር ግን በደቡብ አፍሪካ ያሉ ባለስልጣናት የታተመ የምስክር ወረቀት ይፈልጋሉ።

ክሪስቲ ዜግነት የሌላት መሆኗን ስታውቅ የወላጆቿን ዜግነት ለማግኘት እንደሞከረች ትናገራለች፤ ነገር ግን ያንን ለማድረግ በጣም ዘግይቷል።

"የዚምባብዌ ዜግነቴን መጠየቅ አልቻልኩም፤ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ የ16 ዓመት ልጅ እያለሁ የልደት ምዝገባ እንድጀምር አይፈቅዱልኝም ነበር። እንዲሁም የዚምባብዌ ፓስፖርት ለማግኘት ከደቡብ አፍሪካ መውጣት ነበረብኝ፤ ምንም ዓይነት ሰነድ ሳይኖረኝ ከአገሪቱ ከወጣሁ እንድመለስ አይፈቀድልኝም ነበር።"

ደቡብ አፍሪካ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰነድ አልባ ስደተኞች ያሏት ሲሆን ባለሥልጣናት ለዓመታት መደበኛ ያልሆነ ስደትን ለመግታት ሲሞክሩ ቆይተዋል።

ክሪስቲ ሰነድ አልባ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሲወልዱ እና አገር አልባ ለሆኑ ልጆቻቸው የደቡብ አፍሪካ ዜግነትን መስጠት እንደ ሽልማት እንደሚቆጠር ስትጠየቅ በዚህ አባባል አንደማትስማማ ትናገራለች

"ዜግነት ሽልማት አይደለም ብዬ አስባለሁ። አንድ ሰው የተከበረ ሕይወት መኖር የሚችልበት እና አንድ ሰው እንደ ሰው መታየት የሚችልበት መብት ነው። በዚህ መነጽር ብንመለከተው፣ ወደ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መሄድ ወይም የጤና እንክብካቤ ማግኘት የማይችል ልጅን ዜግነት በመስጠት የምናጣው ምንም ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን።"

የደቡብ አፍሪካ የልደት ምስክር ወረቀት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በደቡብ አፍሪካ 10,000 ሰዎች አገር አልባ ናቸው ተብሎ ይገመታል

ቢቢሲ በደቡብ አፍሪካ የኢሚግሬሽን ጉዳዮችን የሚያስተናግደውን የአገር አልባነትን ጉዳይ እንዴት እየፈታው እንደሆነ ለማወቅ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሙከራ ቢያደርግም ምንም ምላሽ አላገኘም።

የአገር አልባነት በደቡብ አፍሪካ ብቻ የተፈጠረ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፍ ትልቅ ችግር ነው።

በዓለም ዙሪያ 4.5 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜግነት የሌላቸው ሰዎች እንዳሉ ይገመታል። አንዳንዶች ይህ ቁጥር እስከ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይናገራሉ።

ባለሙያዎች ችግሩን መፍታት ስደተኞች ልጆቻቸው የተወለዱበት ቦታ እንዲመዘገቡ መፍቀድን እና እናቶች ዜግነታቸውን ለልጆቻቸው የማስተላለፍ መብት መስጠትን ጨምሮ የፖሊሲ ለውጦችን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያምናሉ።

"ለእኛ አገር አልባነት የሕግ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በልማት የመሳተፍ መብትን የሚመለከት ጉዳይ ነው" ሲሉ በዩኤንኤችሲአር ባልደረባ የሆኑት ጄሱስ ፔሬዝ ሳንቼዝ ተናግረዋል።

"አገር አልባ የሆነ ግለሰብ ለምታኖረው አገር ሙሉ በሙሉ አስተዋጽኦ ማድረግ አይችልም። ስለዚህ በማኅበረሰቡ ወደ ጥግ ተገፍተው ያሉ ሰዎች ለሕዝቡ እና ለኢኮኖሚው ሙሉ በሙሉ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ በማካተት አገር አልባነትን መፈታት አስፈላጊ ነው ብለን እናስባለን።"

አርኖልድ ወደ ቴምቢሳ ሲመለስ ከአካባቢው ልጆች ጋር እግር ኳስ እየተጫወተ ነው።

ለዓመታት ትግል ካደረገ በኋላ፣ አሁን ደቡብ አፍሪካዊ መሆኑን የሚያረጋግጡ ወረቀቶችን ለማግኘት የሚረዳው ጠበቃ አለው። የኮምፒውተር ሳይንስ ለመማር ወደ ትምህርት ቤት ተመልሶ መሄድ ይፈልጋል። ሕጋዊ ሰነዶች ማግኘቱ ብሩህ የወደፊት ሕይወት እንደሚያመጣለት ተስፋ ያደርጋል።