'አሜሪካዊ ለመሆን ጫፍ ላይ እንደደረስን ነው ትራምፕ ዜግነታችንን የምንፈፅምበትን ሥነ ሥርዓት የሰረዙት'

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
ከአስር ዓመት በፊት ወደ አሜሪካ የተሰደደችው ኢራናዊቷ ሳናም የአሜሪካ ዜግነት ለማግኘት ጫፍ ላይ ደርሳ ነበር።
ለዓመታት ያሰባሰበቻቸው ሰነዶች፣ ያገኘቻቸው ማረጋገጫዎች፣ ምርመራዎች እና የደኅንነት ማረጋገጫዎች ነበሩ ዜግነት ለማግኘት ወደ ሚያስችለው የመጨረሻው ደረጃ ያደረሳት።
ሆኖም ኅዳር 22/ 2018 ዓ.ም. ቀን ቃለ መሃላ ለመፈፀም ሁለት ቀናት ሲቀራት የአሜሪካ መንግሥት ይህንን ሁሉ ልፋቷን ውድቅ አድርጎባታል።
ሳናም መጀመሪያ ላይ ደንግጣ እና ግራ ተጋብታ ነበር። ምንም የተሰጣት ማብራሪያ የለም። ምንም ዓይነት ስህተት ሳትሰራ ሥነ ሥርዓቱ ለምን እንደተሰረዘ እንዳልገባት ለቢቢሲ ተናግራለች።
በኋላ ላይ ግን ምክንያቱ የተወለደችበት ቦታ እንደሆነ ደርሳበታለች።
" ዜግነት ለማግኘት ስለፋ ዓመታት ተቆጥረዋል። አቅሜ እንደተሟጠጠ ነበር የሚሰማኝ። ይህንን ሂደት መቀጠል እችል ይሆን የሚል ዓይነት ስሜት ሁሉ ይሰማኝ ነበር። ምክንያቱም ከባድ ነበር" ስትል የምታስታውሰው ሳናም ውሳኔው ልብ ሰባሪ እንደሆነ ተናግራለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በደኅንነት ምክንያት ትክክለኛ ስሟ እንዲገለጽ ያልፈለገችው እና ቅፅል ስሟን እንድንጠቀም የጠየቀችው ሳናም፣ የአሜሪካ ዜግነት ካለው ባሏ ጋር በኦሪገን ነው የምትኖረው።
ቢቢሲ የሳናም ማንነት ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጧል።
ያጋጠማት ጉዳይም በርካቶችን የሚያጋጥማቸው ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የትራምፕ አስተዳደር የጉዞ እገዳ ከተጣለባቸው19 አገራት የሆኑ ስደተኞችን ዜግነት ለማግኘት የሚያካሂዱትን የመጨረሻ ሥነ ሥርዓት ሰርዟል።
ይህ አወዛጋቢ ውሳኔ እንደ ሳናም ያሉ የአሜሪካ ዜግነት ለማግኘት እያንዳንዱን ሂደት ያለፉ እና የመጨረሻውን ሥነ ሥርዓት ብቻ እየጠበቁ ያሉ አንዳንድ ሕጋዊ ቋሚ ነዋሪዎችን ምንም የማይታወቅ ሁኔታ ላይ ጥሏቸዋል።
" ሕይወታችን ያልታወቀ አጣብቂኝ ውስጥ እንደገባ ነው የሚሰማኝ" የምትለው ሳናም፣ እርሷ እና ባለቤቷ መንግሥት በሚያደርገው ምህረት ላይ የሚወሰን እንደሆነ አንደሚሰማቸው ተናግራለች።
ይህም በአሜሪካ ስለመቆየት ዋጋ እንደገና ማሰብ እንድትጀምር አድርጓታል።ሳናም በኢራን አረጋውያን ወላጆቿን ጨምሮ ቤተሰብ ያላት ሲሆን መቼ ሄዳ ልታያቸው እንደምትችል ግን አታውቅም።
" በዚህ ሁኔታ ላይ ሆኘ ስለ ተስፋ ማሰብ ከባድ ነው" ትላለች ሳናም።
" በጣም አስጨናቂ ጊዜ ነው። ወደ በዓላት እየተቃረብን ቢሆንም እንደ አለመታደል ሆኖ ሰዎች በዚህ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሲያልፉ ማየት ያሳዝናል። የደስታ እና ከቤተሰብ ጋር የመሰባሰቢያ ወቅት ነበር መሆን የነበረበት።" ብላለች።
በአሜሪካ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸው 19 አገራት
የቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓቱ የኢሚግሬሽን ሕጎችን ለማጥበቅ በትራምፕ አስተዳደር ከተወሰዱ ጥብቅ እርምጃዎች አንዱ አካል ነው።
የ19 አገራት ስደተኞች ቀድሞውኑ የጉዞ እገዳ የተጣለባቸው ሲሆን የትም፣ በምንም ሁኔታ፣ በየትኛውም ደረጃ ላይ ቢሆኑም የኢምግሬሽን ሂደታቸው ተቋርጧል።
ይህ ውሳኔ የተላለፈው አንድ አፍጋኒስታናዊ ከሦስት ሳምንታት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ በብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ተኩስ ከፍቶ አንዷን ከገደለ እና ሁለቱ ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ ነው።
የትራምፕ አስተዳደር ጥቃቱን ተጨማሪ 500 የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን ማሰማራትን፣ የሥራ ፈቃድን ጊዜ ቀድሞ ከነበረው አምስት ዓመት ወደ 18 ወራት ማሳጠርን እና ሁሉንም የጥገኝነት ጥያቄዎችን ማቆምን ጨምሮ በርካታ የኢሚግሬሽን ሕጎችን ለማጥበቅ በምክንያትነት ተጠቅሞበታል።
የአሜሪካ የዜግነት እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት፣ የተጣለው ገደብ ብሔራዊ ደኅንነትንና የአሜሪካውያንን ሕይወት ለመጠበቅ እንዲሁም የማኅበረሰብ ደኅንነትን ለማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ብሏል።
ሆኖም በመቶዎች የሚቆጠሩ የመብት ተሟጋች ቡድኖችን የሚወክለው ኒው ዮርክ የኢሚግሬሽን ጥምረት የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ምክትል ፕሬዚደንት ማሪዮ ብሩዞን፣ ገደቦቹ ከለላ የሚያስፈልጋቸውን በርካታ ስደተኞች አደጋ ላይ መጣሉን ተናግረዋል።
ብሩዞን ለቢቢሲ ሲናገሩ " ላልታወቀ ጊዜ የተቀመጠ ገደብ እገዳ መሆኑን መረዳት ቀላል እና ግልጽ ነው። በዲሲ የተፈፀመውን የቅርብ ጊዜ ጥቃት ስደተኞችን ዒላማ ለማድረግ እንደ ምክንያት እየተጠቀሙበት ነው" ብለዋል።
አንድ ጆርጅ የተባለ ቬንዙዌላዊ ስደተኛም የአሜሪካ ዜግነት ለማግኘት የመጨረሻውን ሥነ ሥርዓትን ከመፈፀሙ ከ24 ሰዓታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ያለምን ማብራሪያ ፕሮግራሙ መሰረዙ እንደተነገረው ገልጿል።
" በሥነ ሥርዓቱ ላይ ከልጄ ጋር መታደምን ጨምሮ በሁሉም ነገር ተዘጋጅቼ ነበር።ይህ ያለ ግልጽ ምክንያት ከአንድ ቀን በፊት መሰረዙ ቀጣዩ እርምጃችን ምን ሊሆን እንደሚችል እንዳናውቅ አድርጎናል" ብሏል።
ጆርጅ ትክክለኛ ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ሲሆን ማንነቱ ግን በቢቢሲ ተረጋግጧል። እርሱ እንደሚለው በአውሮፓውያኑ 2017 "በከፍተኛ የሙያ ደረጃ ላይ በመገኘት" በሚሰጠው ዘርፍ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ አግኝቷል።
የትራምፕ አስተዳደር የስደተኞችን ጉዳይ በጥብቅ መመልከቱን እንደሚደግፍ የጠቀሰው ጆርጅ፣ በርካታ ስደተኞች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ በመፍቀድ የባይደንን አስተዳደር ተጠያቂ አድርጓል።
ጆርጅ ጨምሮም ባይደን በተመረጡበት ምርጫ ወቅት መምረጥ ቢችሉ ኖሮ ትራምፕን ይመርጡ እንደነበር ተናግረዋል።
ሆኖም አሁንም የሚያሳስባቸው ጉዳይ አለ።ይህም ለረጅም ጊዜ በአገሪቱ የኖሩ እና ምንም የወንጀል ታሪክ የሌላቸው ነዋሪዎች፣ ጥብቅ ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል ካሏቸው ስደተኞች ጋር በጅምላ እየተፈረጁ መሆናቸው ነው።
"ሁሉንም ሕጎች ተከትለን ጉዳያችንን ይዘን መቀጠል እንድንችል እና ሌሎች ማጭበርበር ወይም ወንጀል የፈፀሙ ደግሞ ተገቢ የሆነ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው እፈልጋለሁ" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የኒው ዮርክ የኢሚግሬሽን ጥምረት ምክትል ፕሬዚደንት ብሩዞን እንደሚሉት ከ19ኙ አገራት የሆኑ ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና እንደ ሳናም እና ጆርጅ ያሉ ሕጋዊ ቋሚ ነዋሪዎች ዓመታትን በፈጀ ከባድ የጤና እና የጸጥታ ምርመራ ሒደት ውስጥ አልፈዋል።
እንደ ጥምረቱ ከሆነ በኒው ዮርክ ግዛት ብቻ በ2023፣ 132 ሺህ ትውልደ ቬንዙላዊያን እንደሚኖሩ ይገመታል።
በመሆኑም ገደቡ በየትኛውም የኢሚግሬሽን ሒደት ደረጃ ላይ የሚገኙ በርካታ ስደተኞችን የሚያቃውስ ሲሆን "እርግጠኝነት በሌለው ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩም ማድረጉን" ብሩዞን ተናግረዋል።
ስሙን መግልጽ ያልፈለገው የሳናም ባለቤት በበኩሉ የሁኔታዎች የጊዜ መርሃ ግብር አስደንጋጭ ነው ብለዋል።
" የብሔራዊ ዘብ አባላት የተፈፀመው ጥቃት በዚህ ሳምንት ቢሆን ኖሮ ባለቤቴ አሁን ላይ ዜግነቷን ታገኝ ነበር" ሲሉ ባለቤታቸው ሳናም ዜግነት ለማግኘት የሚያስችላት ሥነ ሥርዓት ከተሰረዘ ከአንድ ቀን በኋላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
" ሁሉንም እነዚህን ፖሊሲዎች ለመለወጥ ዘዴዎቹ የተቀየሱበትን ፍጥነት ማሰብ ግራ የሚያጋባ ነው።በዚህ ውስጥ ማለፍም ከባድ ነው" ብለዋል።















