በአሜሪካ "አደገኛ ወንጀለኞች" ተብለው ይፋ የተደረጉት ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን

ኢትዮጵያውያኑ

የፎቶው ባለመብት, dhs.gov

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተደዳር በስደተኞች ላይ እየወሰደ ካለው ጠንካራ እርምጃ ጋር በተያያዘ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት "ከሁሉም የከፉ አደገኛ የውጭ ዜጋ ወንጀለኞችን" ዝርዝር ይፋ አድርጓል።

"ከሁሉ የከፉ አደገኛ ወንጀለኞች" ተብለው በመጡበት አገር ተለይተው ማንነታቸው ይፋ የሆኑት ስደተኞች በተለያዩ ወንጀሎች ውስጥ ተሳትፈዋል በሚል በስደተኞች እና የጉምሩክ ሕግ አስከባሪ በሆነው አይስ በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ናቸው።

በዚህ ዝርዝር ውስጥ ከተለያዩ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች የተያዙ ስምንት ወንዶች እና አንዲት ሴት ኢትዮጵያውያን ፎቶግራፍ፣ ስም፣ የፈጸሙት ወንጀል እና ከየትኛው የአሜሪካ ግዛት እንደሆኑ ይፋ ተደርጓል።

ኢትዮጵያውያኑ በግድያ፣ በዕጽ ዝውውር፣ የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት፣ በዘረፋ እና በሌሎችም ወንጀሎች ላይ የተገኙ መሆናቸውን የወጣው ዝርዝር ያመለክታል።

አደገኛ ተብለው የተለዩት ዘጠኙ ኢትዮጵያውያን ከአንዱ በስተቀር የሁሉም ፎቶ ፈጽመዋቸዋል ከተባሉት ወንጀሎች ጋር ለሕዝብ ይፋ ተደርጓል።

እነዚህም ሄኖህ ፈቃዱ፣ በረከት መኮንን፣ ብሩክ ታምራት፣ አዳን ዩሱፍ፣ መስፍን ሁሴን፣ ንግሥቲ በየነ፣ ጳውሎስ ኪዳኔ፣ ሳምሶን ኪዳኔ እና ቤዛ ከበደ ናቸው።

በሕግ አስከባሪው ባለሥልጣን አደገኛና ከሁሉ የከፉ ተብለው በቁጥጥር ሥር የዋሉት እና ከአሜሪካ ይባረራሉ ተብለው የተለዩት የሌላ አገር ዜጎች ትኩረት እንዲደረግባቸው ያደረጓቸውን የወንጀል ድርጊቶችን ዘርዝሯል።

ከተጠቀሱት መካከልም የቤት ውስጥ ጥቃት፣ በተደጋጋሚ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ ዘረፋ፣ ልጆችን ማገት፣ የሽብር ማስፈራሪያ፣ በጦር መሳሪያ ጥቃት መፈጸም፣ የተሰረቁ ንብረቶችን መቀበል፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን አለማበክር፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ይገኙባቸዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአገር ውስጥ ደኅነንት መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ወንጀሎች ፈጽመው "እጅግ የከፉ አደገኛ ስደተኞች" በማለት በመላው ዓለም ከሚገኙ አገራት የመጡ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ያወጣው ዝርዝር ያመለክታል።

የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ክሪስቲ ኖም አሁን ይፋ የተደረገው ዝርዝር በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ ከባድ የወንጀል መዝገብ ያለባቸው የውጭ ዜጎችን ዒላማ በማድረግ የሚካሄደው ዘመቻ ለመጠናከሩ ማሳያ ነው ብለዋል።

ከሁለት ሳምንት በፊት አንድ አፍጋናዊ ስደተኛ ዋሽንግተን ውስጥ በሁለት የአሜሪካ ብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ በፈጸመው አደገኛ ጥቃት አንዷን ሲገድል ሌላኛውን ደግሞ ክፉኛ ካቆሰለ በኋላ የትራምፕ አስተደዳር ከሕገ ወጥ ስደተኞች ባሻገር ሕጋዊዎቹን የሚመለከት እርምጃ እየወሰደ ነው።

በጥቃቱ የተነሳ ከአፍጋኒስታናውያን የቀረቡ ሁሉም የስደተኛ እና የጥገኝነት ጥያቄዎች ተጨማሪ የደኅንነት እና የማጣራት ሥራዎች እስኪከናወኑ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ ተደርገዋል።

በተጨማሪም የትራምፕ አስተዳደር ሕጋዊ ሰነድ ያላቸው ኤርትራን እና ሶማሊያን ጨምሮ ከ19 አገራት ወደ አሜሪካ የገቡ ዜጎች የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ላይ እንደገና ምርመራ እንደሚደረግ አስታውቋል።

እንዲሁም ከየትኛውም አገራት ዜጎች የሚቀርቡ የጥገኝነት ጥያቄዎችን በአጠቃላይ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲታገድ የተደረገ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ "ከሦስተኛው ዓለም አገራት" ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚያደርግ "ቋሚ ዕገዳ" ለመጣል ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

በተለይ ደግሞ ሶማሊያውን ስደተኞችን በመወንጀል አሜሪካ ውስጥ እንዲኖሩ እንደማይፈልጉ እንዲሁም ትውልደ ሶማሊያዊቷን የአሜሪካ ምክር ቤት አባል በማንቋሸሽ ያደረጉት ንግግር ፕሬዝዳንቱ ለስደተኞች ጥላቻ አላቸው እንዲባል አድርጓል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባለፈው ዓመት ወደ ሥልጣን የተመለሱበትን የምርጫ ቅስቀሳ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ጥብቅ የስደተኞች ቁጥጥር እንደሚያደርጉ እና በአገሪቱ ታሪክ ያልታየ "ትልቁን ስደተኞችን የማባረር እርምጃ" እንደሚያካሂዱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲናገሩ ቆይተዋል።

ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈው ወደ ዋይት ሐውስ በተመለሱ ዕለት ነው ንግግራቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የጀመሩት። በዚህም ሕገ ወጥ ስደተኞችን መያዝ፣ ማሰር እና ከአሜሪካ ማባረርን ጨምሮ የቪዛ እና የጉዞ ክልከላዎችን ሥራ ላይ አውለዋል።

የአሜሪካ መንግሥት አገሪቱ የድንበር ጥበቃውን በማጠናከር በአገር ውስጥ ደግሞ መጠነ ሰፊ አሰሳዎችን በማካሄድ ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። በተጨማሪም ስደተኞቹን ወደ አገራቸው እና ወደ ሌሎች ሦስተኛ አገራት በወታደራዊ አውሮፕላኖች በማሳፈር እያባረረ ነው።

ባለፈው ዓመት ግንቦት የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት አማካሪ የሆኑት ስቴፈን ሚለር እንዳሉት የትራምፕ አተስዳደር በቀን ሦስት ሺህ ሰነድ አልባ የሆኑ ስደተኞችን ለመያዝ ዕቅድ እንዳለው አስታውቀው ነበር።

የሲራከስ ዩኒቨርስቲ መረጃ እስካለፈው ኅዳር ወር አጋማሽ ድረስ ከ65 ሺህ በላይ ሰዎች በስደተኞች እና ጉምሩክ ሕግ አስከባሪ (አይስ) ቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክቷል።